ለንጹሐን የተረፈዉ እዳ

0
150

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1947 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንግሊዝ ይዛው የነበረውን የፍልስጤም ግዛት ወደ አረብ እና የአይሁድ መንግሥታት መከፋፈል በሚለው አጀንዳ ላይ ድምፅ በማሰጠት “ፍልስጤም ወደ ሁለት ትከፈል” የሚለውን በ181 ድምፅ አፀደቀ። በዚህ ውሳኔ መሠረትም ግንቦት 14 ቀን 1948 እ.አ.አ የእስራኤል ግዛት እንደ አዲስ ተፈጠረ፤ ይህም በውሳኔው ደስተኛ ያልሆኑትን ፍልስጤማውያንን እና አረቦችን በማነሣሣት ለመጀመሪያው የአረብ – እስራኤል ጦርነት መንሥኤ ሆነ።

እስራኤል እንደ ሀገር በተመሠረተች በዓመቱ በ1949 እ.አ.አ አረቦች ተባብረው የጀመሩት ጦርነት በእስራኤል ድል ሲጠናቀቅ 750 ሺህ ፍልስጤማውያን ተፈናቅለው እስራኤል ተጨማሪ ግዛቶችን ያዘች። በቀጣዮቹ ዓመታትም በአካባቢው በተለይም በእስራኤል እና በግብጽ፣ በዮርዳኖስ እና በሶሪያ መካከል ውጥረት ነግሦ ቀጠለ። በ1956ቱ የስዊዝ ቀውስ እስራኤል የሲናይ ባሕረ ገብ መሬትን ከወረረች በኋላ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ እና ሶሪያ የጋራ መከላከያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ሰኔ ወር 1967 በግብጽ ፕሬዝዳንት ገማል አብደል ናስር መሪነት መላው አረብ ተባብሮ እስራኤል ላይ ጦርነት ከፈተ፤ በዚህም የግብጽ እና የሶሪያ አየር ኃይሎች ላይ ቀድማ ጥቃት ያደረሰችው እስራኤል በስድስት ቀናት ጦርነት ስታሸንፍ ተጨማሪ የፍልስጤም ግዛቶችን መያዝ ቻለች። ከጦርነቱ በኋላ እስራኤል ከግብጽ በሲናይ ባሕረ ገብ መሬትን፣ ከፍልስጤም የጋዛ ሰርጥን፣ ዌስት ባንክን እና ምሥራቅ እየሩሳሌምን ከዮርዳኖስ እንዲሁም የጎላን ኮረብታዎችን ከሶሪያ ነጥቃ ያዘች። ከስድስት ዓመታት በኋላ ግብጽ እና ሶሪያ የተወሰዱባቸውን ግዛቶች ለማስመለስ በሁለት ግንባሮች የ‘ዮም ኪፑር’ ጦርነት ተብሎ የሚጠራውን የጥቅምት ጦርነት በድንገት ጀምረው እስራኤልን አጠቁ። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ለሦስቱም ሀገራት ትልቅ ጥቅም ያላስገኘ ሲሆን የወቅቱ የግብጽ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት ግብጽ እና ሶሪያ ቀድሞ በያዙት መሬት ላይ እንዲደራደሩ በማድረግ ጦርነቱን ግብጽ በድል አድራጊነት እንዳጠናቀቀች አወጁ።

በ1979 እ.አ.አ በአሜሪካ አደራዳሪነት በተከታታይ የተካሄደ የሰላም ንግግርን ተከትሎ የግብጽ እና የእስራኤል ተወካዮች የካምፕ ዴቪድ ስምምነትን ተፈራርመዋል። ይህም በግብጽ እና በእስራኤል መካከል የነበረውን የ30 ዓመት ግጭት የዘጋ የሰላም ስምምነት ተባለ። ግብጽ ራሷን ብቻ ከጦርነት ስታርቅ በስማቸው አረቦችን አስተባብራ ስታዋጋቸው የነበሩት ፍልስጤማውያን ግን ባዶ እጃቸውን ቀሩ። ነጻ ሀገር የመሆን እና ግዛቶቻቸውን መልሰው የማግኘት ጥያቄያቸውም ተዳፍኖ ግጭቱ በነሱ እና በእስራኤል መካከል ብቻ ሆኖ ቀጠለ።

በ1987 እ.አ.አ በዌስት ባንክ እና በጋዛ ሰርጥ የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የእስራኤል መንግሥትን በመቃወም የመጀመሪያው እና ‘ኢንቲፋዳ’ ተብሎ የሚጠራውን ከፍተኛ ተቃውሞ አደረጉ። በ1993 በተደረሰው “የኦስሎ አንድ” ስምምነት ፍልስጤማውያን በዌስት ባንክ እና በጋዛ ውስጥ እራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በተቋቋመው የፍልስጤም አስተዳደር እና በእስራኤል መንግሥት መካከል የጋራ ዕውቅና ተሰጠው።

በ1995 የተደረገው “የኦስሎ ሁለት” ስምምነት ከመጀመሪያው ስምምነት ሰፋ ያለ ሲሆን እስራኤል ከስድስት ከተሞች እና 450 የዌስት ባንክ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ እንድትወጣ የሚደነግጉ ስምምነቶችን አክሎ ተፈርሟል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2000 የወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በአረቡ ዓለም ሦስተኛው ቅዱስ ስፍራ እንደሆነ የሚታመንበትን የአል – አቅሳ መስጊድ መጎብኘት እና የእስራኤል በዌስት ባንክ መቆየት ባስነሳው ቅሬታ ሁለተኛው ‘ኢንቲፋዳ’ በመነሣቱ የሰላም ሂደቱ ተስተጓጎለ። ይህም የተፈረሙት የኦስሎ አንድ እና ሁለት ስምምነቶች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሆነ። ሁለተኛው ኢንቲፋዳም ከመስከረም 2000 ጀምሮ እስከ 2005 እ.አ.አ ድረስ ቆየ።

ነሐሴ እና መስከረም 2020 እ.አ.አ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ባሕሬን ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ ተስማሙ። ይህም በ1979 ግብጽ፣ በ1994 ዮርዳኖስ ከእስራኤል ጋር ካደረጉት ስምምነት ቀጥሎ ተመሳሳይ ስምምነቶችን ያደረጉ ሦስተኛ እና አራተኛ የአረብ ሀገራት ያደርጋቸዋል። በጥቅምት 2020 እ.አ.አ የእስራኤል ፍርድ ቤት ውሳኔ ለምሥራቅ እየሩሳሌም ቅርብ በሆነችው ሼክ ጃራህ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ፍልስጤማውያን ተገደው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በ2021 እ.አ.አ ቦታው ለአይሁድ ቤተሰቦች ተላለፈ። ፍልስጤማውያኑ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ይግባኝ ቢሉም ምንም ምላሽ ሳያገኙ ቀሩ።

በአረቦቹም ሆነ በምዕራባውያን በኩል ፍትሕ ያጡት ፍልስጤማውያን እንደዚህ እየተንገላቱ ባሉበት ጊዜ ጥቅምት 7 ቀን 2023 እ.አ.አ ሃማስ በርካታ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል በማስወንጨፍ ከባድ ጉዳት አደረሰ፤ ይህም እንደገና ፍልስጤማውያንን ሌላ እልቂት ውስጥ አስገባቸው። በሁለት ቀናት ብቻ ከስምንት መቶ በላይ አስራኤላዉያን እና ከአምስት መቶ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

በቅርቡ የሃማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬህ በኢራን እንዲሁም የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላ ከፍተኛ አዛዥ መገደላቸውን ተከትሎ በቀጣናው ውጥረት ነግሷል።

የሃማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬህ ሐምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት ስምንት ሰዓት ላይ በኢራኗ መዲና ቴህራን በቤት ውስጥ ሳሉ ተገድለዋል። ኢራንም በአስራኤል ላይ ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃት ዝታለች። ይህም ቀጣናዊ ውጥረቱን አባብሶታል።

በጋዛ የተኩስ አቁም ድርድር ላይ ትልቅ ሚና የነበራቸው የ62 ዓመቱ ሃኒዬህ በቴህራን የኢራን ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን በዓለ ሲመት ላይ ከታደሙ ከሰዓታት በኋላ ነው የተገደሉት።

የሃኒዬህ መገደል የተሰማው እስራኤል የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ የሆነውን ፉአድ ሹክርን መግደሏን ባሳወቀች በሰዓታት ውስጥ ነው።

የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ እስራኤል በሃኒዬህ ግድያ “ከባድ ቅጣት” እንደሚጠብቃት ዝተዋል፤ በሀገሪቱ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሃዘንም አውጀዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚሳኤል መከላከያ ኃይል ለማሰማራት ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጸው የአሜሪካው ፔንታጎን እስራኤልን ለመከላከል “የማያወላውል ቁርጠኝነት አለ” ብሏል። ፔንታጎን በመግለጫው የሚሰማራው አዲሱ ወታደራዊ ኃይል “የአሜሪካ ጥበቃን በማሻሻል ለእስራኤል መከላከያ የሚሰጠውን ድጋፍ የሚያሳድግ እንዲሁም አሜሪካ ለተለያዩ ድንገተኛ ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነቷን የሚያረጋግጥ ነው” ብሏል። የባሊስቲክ ሚሳኤል መከላከያዎችም እንደሚሰማሩ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ለእስራኤል 20 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ እጅግ ዘመናዊ የሚባሉትን ኤፍ 35 (F-35) ተዋጊ ጀቶችን ለመሸጥ ውሳኔ አሳልፋለች:: ኤፍ 35 ጀቶች አሜሪካ ከየትኛውም ሀገር መንግሥት እጅ ላይ እንዲገቡ የማትፈልጋቸው እና የምትሳሳላቸው ናቸው፤ ነገር ግን እስራኤል ለአሜሪካ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንጻር ሽያጩን መፍቀዷን አሶሺየትድ ፕሬስ አትቷል:: ጀቶቹ ቁጥራቸው ከ50 በላይ ነው፤ ከዚህ ባሻገር አየር በአየር ሚሳየሎች፣ ታንኮች፣ ሞርታሮች እና ሌሎች የውጊያ ተሽከርካሪዎች በሽያጩ ተካተዋል ተብሏል:: በዚህም እስራኤል ተባብሶ በቀጠለው ጦርነት ክንዷ ይፈረጥማል ተብሏል:: ይሁን እንጂ አንዳንድ ተንታኞች የሽያጭ ሂደቱ ጊዜ ስለሚወስድ ትርጉም አይኖረውም ብለዋል:: ሌሎች ደግሞ የጦር መሣሪያዎቹ እስራኤል እጅ ላይ ገብተው ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል::

በአሁኑ ወቅት የሁለተኛውን ሐሳብ የሚያጠናክር ክስተት ተፈጥሯል:: እስረኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት እየሰነዘረች ነው:: በደቡባዊ ጋዛ በደረሰው ጥቃት አያሌ ንጹሃን ተገድለዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል:: የአየር ጥቃቱ የተሰነዘረው እስራኤል እና ሃማስ በኳታር ዶሃ የተኩስ አቁም ውይይት ሊያደርጉ ዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው ተብሏል:: የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሙሐመድ ቢን አብድረህማን አል ታኒ ሁለቱ ኃይሎች የሰላም ስምምነቱን ሊጎዳ የሚችል ማንኛውንም ድርጊት እንዳይፈጽሙ አሳስበዋል::

የጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 40 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል፤ 92 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ቆስለዋል:: ሃማስ በእስራኤል ላይ በከፈተው ጥቃት ደግሞ ከ1300 በላይ ሰዎች ሲገደሉ 200 እስራኤላዊያን ደግሞ ታግተው ተወስደዋል:: የእስራኤል እና ሃማስ ግጭት ለንጹሐን የተረፈ እዳ ሆኖ ቀጥሏል::

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here