በቤት መኪና የኋላኛው ክፍል ድንክ ፈረስ ጭና ስታሽከረክር በትራፊክ የተያዘች ጀርመናዊት የተወሰነባትን የ41 ዶላር ቅጣት ባለመቀበሏ አስተዳደራዊ ክስ የተመሰረተባት መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በመስከረም ወር መግቢያ በጀርመን አስደርፍ፣ አቸን አቅራቢያ የቤት መኪና ስታሽከረክር የነበረች ሴት በኋለኛው ጓዝ መጫኛ ድንክ ፈረስ ጭና በመታየቷ በትራፊክ ፓሊስ ተይዛለች፡፡ የተሽከርካሪዋን የኋለኛ ክፍል አስከፍቶ የተመለከተው ተቆጣጣሪም አሽከርካሪዋ ደንብ መተላለፏን በመግለጽ 41 ዶላር እንድትከፍል ቢያስታውቃትም ጥፋት አልፈፀምኩም በሚል ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች፡፡
ተቆጣጣሪ ፓሊሱ በበኩሉ በወቅቱ አሽከርካሪዋ ትጓዝበት ከነበረው ፍጠነት አንፃር 150 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ፈረስ የታሰረበትን መናኛ ገመድ በጥሶ ቢወረወር የከፋ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም ድንኩ ፈረስ ግዝፈቱ አነስተኛ ቢሆንም በቤት መኪና የኋላ ጓዝ መያዣ መጫኑ አግባብ አለመሆኑን ነው ያሰመረበት፡፡
አብዛኛዎቹ የቤት መኪና አሽከርካሪዎች የሚወዷቸውን የቤት እንስሳት ለአብነት ውሻ፣ ድመት፣ አዕዋፍ የመሳሰሉትን ጭነው መጓጓዝ እንደሚሹ የጠቆመው ትራፊክ ፖሊሱ የጀመርናዊቷ ሴት አድራጐት ወይም ድንክ ፈረስ መጫኗ ግን ያልተለመደ መሆኑን ነው አፅንኦት ሰጥቶ ያብራራው፡፡
ትራፊክ ፖሊሱ የአሽከርካሪዋ አድራጐት ራሷን እና ሌሎች የመንገድ ተጠቃሚዎችን ህይወት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል በማመንም ከጉዞዋ በመግታት በቁጥጥር ስር አውሏታል፡፡
በመጨረሻም በቀጣይ አስተዳደራዊ ክስ ተመስርቶባት ተገቢው ቅጣት እንደሚጠብቃት ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም