ለአዲስ ምዕራፍ መዘጋጀት

0
120

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር እያጋጠሙ የመጡ ግጭቶች በተለይ የወደፊት መዳረሻ መነጸር እንደሆነ የሚነገርለትን ትምህርት በእጅጉ እየፈተኑት መጥተዋል:: ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ መፍትሔ ርቋቸው የቀጠሉ ግጭቶች በተለይ የአማራ ክልል በተማረ ዜጋ የነበረውን ተወዳዳሪነት እንዳያሳጣው ተሰግቷል:: የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የቢሮውን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በገመገሙበት ወቅት ግጭቶች በትምህርቱ ዘርፉ እያደረሱት ያለውን ተጽእኖ የገለጹት ዛሬ ላይ ለችግሩ ምላሽ መስጠት ካልተቻለ ወደ ፊት የአማራ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስመረቅ ዩኒቨርሲቲ ላይገኙ ይችላሉ በማለት ነው::

ባለፈው ዓመት 58 በመቶ ተማሪዎችን ሲያስተምር የከረመው ክልሉ አንድም ተማሪ ለክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተና ሳያስፈትኑ የቀሩ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም ቀላል አልነበረም:: ዘንድሮም ችግሩ ቀጥሎ የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት እየተጠናቀቀ ባለበት ወቅት ለመማር የተመዘገቡት ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው:: ይህም በዓመቱ መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ ከነበረው ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች በአራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ያነሰ ነው:: እስካሁን ከተመዘገቡት ውስጥ 400 ሺህ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ አለመገኘታቸው ደግሞ የችግሩ አሳሳቢነት ማሳያ ሆኖ በቢሮዉ ተነስቷል::

የተማሪዎች ምዝገባ በልዩ ሁኔታ እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቀጥል ቢሮዉ ሲያስታውቅ፣ ተፈታኝ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ ግን በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል:: በተለይ የስድስተኛ፣ ስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የሚያስፈትኑ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው የተሻለ ውጤት አስመዝግበው ቀጣዩን የትምህርት ምዕራፍ እንዲገልጡ እየሠሩ ነው::

የስድስተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን ከሚያስፈትኑ ትምህርት ቤቶች መካከል በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የቁልቋል ሜዳ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው:: የትምህርት ቤቱ ተፈታኞችም ትምህርት ቤቱ አዘጋጅቶ በሰጣቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተዘጋጁ መሆኑን አስታውቀዋል:: መምህራን የተለያዩ ጥያቄዎችን እያዘጋጁ ተማሪዎች ራሳቸውን እንዲፈትሹ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል::

ከዚህ ጎን ለጎን ከሳምንቱ የእረፍት ቀናት አንዱ በሆነው ቅዳሜ ተማሪዎች በመረጧቸው መምህራን የማካካሻ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል:: ትምህርት ቤቱ የምገባ ፕሮግራም የሚሰጥ መሆኑ ደግሞ ጥናትን ከትምህርት ቤት ሳይርቁ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል:: እነዚህ ሁሉ የዝግጅት ሥራዎች ተፈታኞች በዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ውጤት እንዲጠብቁ ስንቅ እንደሚሆናቸው ተስፋን ጥለዋል::

በትምህርት ቤቱ የሥነ ምግባር እና ሥነ ዜጋ ትምህርት ክፍል መምህር አበባው ሽፈራው እንደነገሩን ተፈታኞች የተሻለ ውጤት አስመዝግበው ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ እንዲሸጋገሩ የማድረግ ሥራው በተደራጀ መንገድ ተጠናክሮ እየተሰጠ ነው:: ያለፉ ዓመታት የፈተና ጥያቄዎች ለዘንድሮ ተማሪዎች እንደ መነሻ ሆነው እንዲያገለግሉ መሥራት፣ ተማሪዎች የጥናታቸውን ደረጃ እንዲፈትሹ እና ይበልጥ እንዲዘጋጁ የሚያስችሉ ጥያቄዎችን ማዘጋጀት፣ አጋዥ መጻሕፍትን ማቅረብ በትኩረት እየተሠራ ነው::

ወይዘሮ  አገር  ነቃጥበብ የቁልቋል ሜዳ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተወካይ ርእሰ መምህር ናቸው:: በዓመቱ መጨረሻ ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ የስድስተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጠንካራ የቅድመ ማብቃት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል:: በትምህርት ቤቱ የተሻሉ የሚባሉ መምህራንን ከመመደብ ጀምሮ ሙሉ ጊዜያቸውን ለጥናት ብቻ እንዲያውሉ የተጠናከረ የምገባ ፕሮግራም እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል::  የቤተ መጻሕፍት አገልግሎትም በሳምንቱ የእረፍት ቀናት ክፍት መደረጉን አስታውሰዋል::

የጣና ኃይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም በ2017 ዓ.ም 994 ተማሪዎቹን ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያስፈትናል:: የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አቶ ሙጨ ባዝዘው ለአሚኮ እንደገለጹት ሁሉም ተፈታኞች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስገባቸውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ የቅድመ ማብቃት ሥራ በልዩነት እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል::

በቅድመ ማብቃቱም አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ እንዲደርስ፣ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በሳምንቱ ሁሉም ቀናት ክፍት ተደርጎ ተማሪዎች እንዲያጠኑ፣ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበሩ የፈተና ጥያቄዎችን ቤተ መጻሕፍት በማስቀመጥ እና መምህራንም እንዲሠሩላቸው በማድረግ ይበልጥ የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑ፣ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የማካካሻ ትምህርት አንዱ ቅድመ ሁኔታ ሆኖ መጀመሩ እና መምህራን ያላቸውን ትርፍ ጊዜ ተማሪዎችን በማብቃት ላይ እንዲያውሉ መግባባት ላይ መደረሱ ተጠቃሽ ናቸው::

ወላጆች እና የትምህርት ባለሙያዎችም ተማሪዎች ቀሪ ጊዜያትን በአግባቡ ተጠቅመው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የድጋፍ እና ክትትል ሥራ ሊያከናውኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here