ለኢትዮጵያዊ እሴቶች መመለስ

0
287

ቅዱስ ዮሐንስ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነው:: ከቅድመ መደበኛ /ኬጂ/ ጀምሮ አሁን እስካለበት የክፍል ደረጃ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው ብፁዕ አቡነ በርናባስ ቤዛ ብዙኀን ትምህርት ቤት ነው:: ከኬጂ ጀምሮ እየተሰጠ ባለው የግብረ ገብነት ትምህርት ብዙ ጥቅም እንዳገኘበት ነግሮናል::

ቅዱስ እንደነገረን ልጆች ከልጅነታቸው  ጀምሮ እናት እና አባታቸውን እንዲያከብሩ፣ ለታላላቆቻቸው አክብሮት እንዲኖራቸው፣ ጥፋት ከፈፀሙ  ይቅርታን እንዲጠይቁ፣ ፈጣሪያቸውን በፀሎት  እንዲያመሰግኑ  እንዲሁም የታዛዥነት እና ሰውን ሁሉ የማክበር ልምድ እንዲኖራቸው ተምረዋል::

ቅዱስ በሚሰጠው የግብረ ገብ ትምህርት  ሰፈር ውስጥ እንደ እርሱ የግብረ ገብነት ትምህርት የማይማሩ   ልጆች ሰውን ሲሳደቡ እና ወላጅን ሲያንጓጥጡ “ይሄ የጥሩ ልጅ ባህሪ ሊሆን አይገባም፤ ነውር ነው!” ብሎ እንደ ሚመክራቸው  ነግሮናል::

የግብረ ገብ ትምህርት ጥሩ እና መጥፎን ለይቶ ባህሪን የሚያስተካክል እና የሚያሳውቅ እንደሆነም ቅዱስ ገልፆልናል::

ለበርካታ ዓመታት በውስን ትምህርት ቤቶች ብቻ  ሲሰጥ የነበረው የግብረ ገብ ትምህርት በአሁኑ ወቅት በመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ ተደርጓል:: በእርግጥ የግብረ ገብ ትምህርት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሰጠት የጀመረው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ “የሥነ ዜጋ እና የሥነ ምግባር ትምህርት ለዴሞክራሲ ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ” በሚል የተሠራው ጥናታዊ ጽሑፍ ያስረዳል::

በዚያን ወቅት ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው የሞራል ትምህርት በሚል እንደነበር ጥናቱ ጠቁሟል:: በሥነ ምግባር የታነፁ ትውልዶችን መፍጠር የትምህርቱ ተቀዳሚ ዓላማ ነው:: ተማሪዎች የግብረ ገብ ወይም የሥነ ምግባር ትምህርትን መውሰዳቸው ታላላቆቻቸውን እንዲያከብሩ፣ ለሕግና ሥርዓት ተገዢ እንዲሆኑ በማድረግ የማይናወጥ ሀገራዊ ሰላምን ለመፍጠር የሚኖረው አበርክቶም ከፍተኛ እንደነበር ይታመናል::

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ሥነ ባህሪ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር የነበሩት መስከረም ለቺሳ (ዶ/ር) ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር ተያይዞ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ግብረ ገብ ትምህርት አስፈላጊነት አብነቶችን እያነሱ ያስረዳሉ:: አባታቸው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት እንደተማሩ የሚገልጹት ረዳት ፕሮፌሰሯ ትምህርቱ ለአለባበስ ትኩረት የሰጠ ነበር:: ፋብሪካ ውስጥ ሲገባ ምን መልበስ እና እንዴት መልበስ እንደሚገባ፣ ራሳቸውን እና ሰውነታቸውን እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው፣ የሚፅፉበት ደብተር፣ ለእጅ ጽሑፋቸው በጣም ጥንቃቄ ያደርጉ እንደ ነበር አባታቸው የነገሯቸውን አስታውሰው ተናግረዋል:: ቅልጥፍናቸው፣ ታዛዥነታቸው፣ አመጋገባቸው…በአጠቃላይ  ሁሉንም ሥነ ምግባር ይማሩ እንደነበር ገልጸዋል:: የዚያን ትምህርት ነፀብራቅም በአባታቸው ላይ መታዘብ እንደቻሉ አስረድተዋል::

ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር በተገናኘ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከበኲር ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ቢሻው በበኩላቸው ለሀገር በቀል ዕውቀቶች የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ጠቁመዋል::

ፕሮፌሰሩ ከሰላሳ ዓመታት በላይ የሚሆነውን ዕድሜያቸውን ያሳለፉት በሥርዓተ ትምህርት እና በትምህርት ዙሪያ መሆኑን ጠቁመዋል፣ “ብዙውን ጊዜ ስናስተምር የምንጠቀመው የውጭ አባባሎችን ወይም የውጭ ምሁራን ያሉትን ነው” ሲሉ ለሀገር በቀል ዕውቀቶች የተሰጠውን አነስተኛ ትኩረት ያስረዳሉ:: በሚገርም ሁኔታ ግን ታዋቂ ፈላስፎች እና የትምህርት ባለሙያዎች የሰጡት አባባሎች በአብነት እና በመድረሳ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተደራጅተው እንደሚገኙ ገልጸዋል::

የአብነት የትምህርት ተቋማት ከሁለት ሺህ  ዓመታት በላይ  ራሳቸውን ያቆዩ መሆናቸውን ያስታውሳሉ:: እነዚህ የትምህርት ተቋማት ሳይንገዳገዱ ወጥ በሆነ አቋም ለዓመታት የዘለቁት የትምህርት ሥርዓታቸው ግብ እና የማስፈፀሚያ ስልታቸው አስተማማኝ በመሆኑ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ አስታውሰዋል::

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት እየተከተለችው ያለው  የምዕራባውያን ሥርዓተ ትምህርት ግን የጠራ ግብ እና አሰተማማኝ የማስፈፀሚያ ስልት እንደሌለውም አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ:: በአጠቃላይ ከአብነት እና መድረሳ ትምህርት ቤቶች የሚወጡ ተማሪዎች አብዛኞቹ ጐበዞች ናቸው:: ይህ የሆነው ደግሞ በተቋማቱ ግብረ ገብን በአግባቡ ስለሚማሩ ነው ይላሉ:: ሀገራዊ እሴቶችን እንዲያውቁ ተደርገውም ይቀረፃሉ::

በተማሪዎች እና በአስተማሪዎቻቸው መካከል  መከባበር አለ:: ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚወጡ ተማሪዎች ዓላማ እና ግብ ስለሚኖራቸው በየትኛውም የትምህርት ዘርፍ ሆነ በሥራቸው ውጤታማ እና የመልካም ሥነ ምግባር  ባለቤት ሆነው እንደሚታዩ ተናግረዋል::

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሀዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ልማት ተቋም ዳይሬክተር መስፍን ፈቃዴ በበኩላቸው ሀገር በቀሉ ሥርዓተ ትምህርት ሥነ ምግባርን ከማረቅ አኳያ ሲታይ ጉልህ አስተዋፅዖ እንዳለው ይገልጻሉ። ለዚህም አስረጂ የሚያደርጉት አዲስ የቆሎ ተማሪ ወደ ትምህርት ቤቱ ሲቀላቀል ነባሩ ተማሪ እግሩን አጥቦ፣ ለምኖ በማብላት ዕውቀትን ተካፍሎ አብሮ ይዘልቃል። የዚህ ጠቀሜታው ሥርዓተ ትህትናን፣ ከሌሎች ጋር አብሮ መኖርን እና የመቻቻል እሴትን ይማርበታል::

ተማሪዎችም እንደ ዕውቀት ልካቸው እያስመሰከሩ ወደ ቀጣዩ ክፍል ይሸጋገራሉ:: እግረ መንገዳቸውንም የሀገራቸውን ቋንቋ፣ ባህል እና ትውፊት እያወቁ ስለሚሄዱ የተሻለ ነገር ለመፍጠር እየጓጉ ያድጋሉ፤ ይህ ሂደት ከነበረው የበለጠ ለመሥራት ያስችላቸዋል በማለት የግብረ ገብ ትምህርትን አስፈላጊነት አስረድተዋል::

በአጠቃላይ የግብረ ገብ ትምህርት ባለፉት ዓመታት ይሰጥ እንደነበረው ሁሉ ግቡን እንዲመታ አስፈላጊ ግብዓቶችን እና ብቁ የሰው ኀይል መመደብ ይገባል:: የትምህርት ሥርዓቱ በተቀረጸበት ልክ ትምህርቱን በውጤታማነት መስጠት ከተቻለ ምናልባትም ኢትዮጵያዊ እሴቶች ተመልሰው እና ጎልብተው ችግር ፈቺነታቸው ዳግም ይታይ ይሆናል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here