ለእርሻ ሜካናይዜሽን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን መምሪያዉ አስታወቀ

0
57

የአፈር ማዳበሪያ  ቀድሞ በመግባቱ  ፈጥነው የሚዘሩ ሰብሎችን በወቅቱ ለመዝራት አርሶ አደሮች ግብዓት እየወሰዱ መሆናቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አጉማሴ አንተነህ ለዞኑ ለ2017/18 የመኸር ወቅት ለአርሶ አደሩ የዘር ወቅት ሳያልፍበት የአፈር ማዳበሪያ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ በ2017/18 የመኸር ምርት ዘመን ከ305 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን እስካሁን 222 ሺህ 472 ሄክታር መሬት ታርሷል። ከዚህ ውስጥ 64 ሺህ 119  ሄክታር በሜካናይዜሽን ለማረስ የታቀደ ሲሆን 45 ሺህ 272 ሄክታሩ ታርሷል። ዘመናዊ የእርሻ ሥራን በመከተል ምርታማነትን ለማሳደግ በግብርናው ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱን መምሪያ ኃላፊው አቶ አጉማሴ ተናግረዋል።

በምርት ዘመኑ ለዞኑ ከሚያስፈልገው  አንድ ሚሊዮን 52 ሺህ 756  ኩንታል የአፈር ሚዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 442 ሺህ 878 ኩንታል በዞኑ ማዕከላት ገብቷል። እስካሁን ባለው መረጃ 182 ሺህ 173 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ የቀረበለትን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ በመውሰድ የዘር ወቅት ሳያልፍበት ጥቅም ላይ እንዲያውል በመሠራቱ  አሁን ላይ የስርጭት ሂደቱ ተሻሽሏል ብለዋል።

በዞኑ እስካሁን ወደ ዞን ማዕከላት የገባው ማዳበሪያ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች  በቂ መሆኑን የገለጹት ምክትል አስተዳዳሪው አርሶ አደሩ  የቀረበለትን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ  ወስዶ ጥቅም ላይ በማዋል የተሻለ ምርት እንዲያመርት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ መምሪያ ኃላፊው እንዳብራሩት 11 ሺህ 415 ኩንታል የበቆሎ  ምርጥ ዘር ለማቅረብ በዕቅድ ተይዟል። ከዚህ ውስጥ ስድስት ሺህ 11 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ነው ኃላፊው የገለፁት።

በ2017/2018 የምርት ዘመን ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ አጉማሴ አመላክተዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here