ለካንሰር የሚያጋልጠው

0
82

ለንቅሳት የሚውል ቀለም በቆዳ ውስጥ ከገባ በኋላ በደም ስር መገናኛ (ሊምፍኖድ) ያልተለመደ የህዋሳት ክምችት ወይም እብጠት እንዲፈጠር በማድረግ የካንሰር ተጋላጭነትን እንደሚጨምር ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::

የደቡብ ዴንማርክ ዩኒቨርስቲ ከአውስትራሊያው ሄልስንኪ ዩኒቨርስቲ ጋር በጥምረት ምርምር አካሂደዋል::  ካካሄዱት ምርምር  በተገኘው ውጤትም  የተነቀሱ ግለሰቦች ንቅሳት ከሌላቸው ጋር ሲነፃፀሩ በቆዳ እና በደምስር መገናኛ (ሊምፍኖድ) ካንሰር የመያዝ አጋጣሚው ከፍ ያለ መሆኑን ደርሰውበታል::

ተመራማሪዎቹ እንዳብራሩት ለንቅሳት የሚውል ቀለም በአካል ላይ በተወጋበት ቦታ ላይ ብቻ አይቆይም:: በጊዜ ሂደት ወደ ሌሎቹ የደምስር መገናኛ አምርቶ ያልተለመደ የህዋሳት ክምችትን አሳድሮ ለካንሰር ያጋልጣል::

የደቡብ ዴንማርክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከሄልሲንኪ ዩኒቨርሲቲ የቡድን አጋሮቻቸው ጋር ከ5900 መንትዮች መረጃ አሰባስበውም ውጤቱን ቀምረዋል:: ባደረጉት ፍተሻ እና ከተገኘው ውጤት ማጠቃለያ ንቅሳት ባላቸው ሰዎች ላይ የ “ሊምፎማ” እና የቆዳ ካንሰር ተጋላጭነት በእጅጉ ጨምሮ ማግኘታቸውን ነው ያስታወቁት::

ተመራማሪዎቹ በንቅሳት መጠኑ ማለትም ማነስ እና መስፋቱ ላይም ትኩረት አድረገው የሚያሳድረውን ውጤት መርምረዋል:: በዚህም የንቅሳት መጠኑ መስፋት የጤና እክልነቱን በእጥፍ ሊጨምረው እንደሚችል መገንዘባቸውን ነው ያመላከቱት::

የደቡብ ዴንማርክ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪው ረዳት ኘሮፌሰር ሲግ ቤድስተድ ክሊመንሰን እንዳብራሩት ንቅሳቱ   በአካል ላይ ሲሆን እና ረዘም ላለ ጊዜ ሲቆይ በደምስር መገናኛ (ሊምፍኖድ) ውስጥ ቀለም ያከማቻል:: የቀለሙ መከማቸትም በራሱ በተፈጥሯዊ የሰውነት በሽታ መከላከል ስርዓት ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል:: በዴንማርክ ንቅሳት ያለባቸው መንትዮች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱን ያረጋገጡት ተመራማሪዎቹ ለንቅሳት ወይም ለጤና የማይመከሩ ቀለሞች መኖራቸውን በመጠቆም ነው ያደማደሙት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here