በአሜሪካ ደቡብ ምሥራቅ ስተኒግተን ኬንእና ሊሳ ኖጋሲክ በተሰኙ አሳዳሪዎቿ ቤት የምትኖር “ሜኒ” የተሰኘች ውሻ ሦስት ጫማ ከሁለት ኢንች በተለካ ቁመቷ ለክብረወሰን መበቃቷን ዩፒ አይ ድረ ገጽ አስነብቧል::
“ሜኒ” የሁለት ወር ቡችላ እያለች ነበር በስተኒግተን አሳዳሪዎቿ ኬን እና ሊሳ ኖጋሲክ ቤት የቤተሰቡ አባል ለመሆን የቻለችው:: እድገቷ ፈጥኖ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ሲሆናትም ቁመቷ እየገዘፈ በመሄዱ ቤተሰቡ “ሜኒ” ለክብረወሰን ልትበቃ ትችላለች የሚል ግምት እንዳደረባቸው ተናግረዋል- ለገምጋሚዎች::
የ “ሜኒ” አሳዳሪዎች ቁመቷ እየረዘመ፣ አካሏ እየገዘፈ ሦስት ዓመት ተኩል ሲሆናት በትክክል ለክብረወሰን መብቃቷን እርግጠኛ መሆን ችለዋል::
ከዚህ በኋላ ነበር ለዓለም ድንቃ ድንቃ መዝጋቢ ድርጅት ያስታወቁት፤ መዝጋቢ ድርጅቱም የተገለፀው እውነት መሆኑን ባለሙያዎቹን ልኮ አጣርቷል::
በድንቃድንቅ መዝጋቢ ድርጅቱ ባለሙያ ልኬታም “ሜኒ” ሦስት ጫማ ከሁለት ኢንች ቁመት ማስመዝገቧ ተረጋግጧል:: በዚህም ቀደም ብሎ በሴት ውሻ ቁመት ከፍሎሪዳዋ ውሻ “ሊዛ” ከተያዘው ክብረወሰን በአንድ ኢንች አብላጫ አስመዝግባ ለክብረ ወሰን መብቃቷን በማደማደሚያነት አስነብቧል- ድረ ገጹ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


