ለውይይቱ ውጤታማነት የድርሻችንን  እንወጣ!

0
94

ግጭት እና  ጦርነት የዓለማችን የዘወትር ክስተቶች ናቸው፡፡  ውስን ሀገራት ከእነዚህ ሰው ሠራሽ ችግሮች ወጥተው በሁሉም ዘርፍ በሥልጣኔ እና በልማት ጎዳና ሲራመዱ ጥቂቶቹ  ለመጥፋት ተገደዋል።

በአገራችን ኢትዮጵያም በየጊዜው ግጭቶች እና ጦርነቶች ሲከሰቱ ይስተዋላሉ፡፡

ጥላቻ እና ሀሰተኛ ትርክት ደግሞ ኢትዮጵያ አገራችን ከግጭት እንዲሁም ጦርነት አዙሪት እንዳትወጣ አድርገዋት ቆይተዋል።

እነዚህ ግጭቶች  ሕዝቡ ለሞት፣ ለሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ለሀብት እና ንብረት ውድመት፣ ለስደት፣ ለእንግልት… እንዲዳረግ ምክንያት ሆነው ኖረዋል፤ ምክንያት እየሆኑም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎቱ ሠርቶ ከድህነት መውጣት ሆኖ  ሳለ በግጭቶቹ እንዲሁም ጦርነቶቹ የተነሳ ያለ ስጋት ተንቀሳቅሶ የዕለት ከዕለት ተግባሩን እንዳይከውን እና ኑሮውን እንዳያሸንፍ  እያደረጉት ነው፡፡   ብዙ ሀብት ፈሶባቸው፣ ብዙ ጊዜ ተደክሞባቸው፣ ብዙ ተስፋ ተጥሎባቸው የተሠሩ የመሠረተ ልማት አውታሮች፣ ሀብት ንብረቶች… በግጭቶች እና ጦርነቶች ሲወድሙ ኖረዋል፤ እየወደሙም ነው፡፡

እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች ተደማምረው ሕዝቡን ሰቀቀን የተሞላበት ሕይዎት እንዲገፋ፣ አገራችን ኢትዮጵያም በጀመረችው የእድገት ፍጥነት እንዳትጓዝ፣ በሥልጣኔ እና በልማት ጎዳና እንዳትራመድ፣ የቀደመ ክብሯ እንዳይመለስ  እንቅፋት ፈጥረውባታል፡፡

እነዚህ ግጭቶች እና ጦርነቶች  በጊዜ የጋራ  መፍተሔ በመፈለግ  ፈጥነን ከግጭት እና ጦርነት አባዜ መውጣት ይኖርብናል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ለመውጣት ደግሞ ከጥላቻ እና ሀሰተኛ ትርክት መውጣት፣ መልካም ሥነ ምግባርን መላበስ ያስፈልጋል፡፡

ከጥላቻ እና ሀሰተኛ ትርክት ስለመውጣት እና መልካም ሥነ ምግባርን ስለመላበስ ሲታሰብም የሃይማኖት አባቶች ሚና የማይተካ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ከዚህ እውነታ በመነሳት ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ከሰሞኑ ሰላምን ማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ   በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አድርገዋል፡፡ “ሰላም ለሀገራዊ አንድነት እና ለመልካም ወንድማማችነት በሃይማኖቶች አስተምህሮ”  በሚል የቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ለውይይት ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሆፎች እንደመነሻ በማድረግ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በጥናቱም ሰላም በፍቅር እና በመተሳሰብ እንጂ በጠመንጃ አፈሙዝ አይመጣም።

በውይይቱ እንደተጠቀሰው ሰላምን በፍቅር እና በመተሳሰብ በማስፈን ሂደት ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ  ባለድርሻ ነው፡፡

የሰላም እጦቱ የሥልጣኔ መነሻዋን፣ የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤቷን ኢትዮጵያ አገራችንን አይመጥንም። ስለሆነም ለሰላም መስፈን ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ ሲሉ ተወያዮቹ ጥሪ አቅርበዋል። ጥሪው ተግባራዊ ምላሽ የሚያስፈልገው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ የሰላም ውይይቱ በአዳራሽ ብቻ እንዳይቀር ሁሉም የበኩሉን አገራዊ ኀላፊነት መወጣት ይኖርበታል።

ሰላም ይሰፍን ዘንድ  ባሕላዊ የእርቅ መንገዶቻችንን መጠቀም፣ እስካሁን ከተጓዝንበት ጠማማ መንገድ መራቅ ግድ ይላል፡፡ ከሁሉም በላይ የሰላም መሠረቱ ግብረ ገብነት ነውና ሰላም እንዲሰፍን ግብረ ገብነትን ገንዘባችን ማድረግ አለብን፡፡ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ ሠርቶ እንዲያልፍለት፣ እንዲያድግ፣ እንዲበለጽግ፣ አገራችን በዕድገት እና በሥልጣኔ ጎዳና እንድትራመድ በውይይቱ የተነሱት  ጉዳዮች  ተግባራዊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከታሪክ እንደምንረዳው የግጭት  መጨረሻው መጠፋፋት፣ ከዓለም ካርታ መፋቅ ስለሆነ  ከግጭት ወጥተን ወደምንታወቅበት ታላቅነታችን መመለስ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ  የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም በቅንነት የየድርሻውን መወጣት አለበት። ይህ ሲሆን ከታሪክ ተወቃሽነት፣ በትውልድም ከመጠየቅ እንድናለን፣ ወደ ቀደመ   ታላቅነታችን እና  ክብራችን እንመለሳለን፡፡።

በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here