ለውጤት የተዘጋጀ ሥነ ልቦና

0
82

የአማራ ክልል በ2017 የትምህርት ዓመት ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ ነበረው፡፡ በተጨባጭ የተመዘገቡት ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ተመዝግበው ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡት 500 ሺህ ተማሪዎች እንደሆኑ የክልሉ ትምህርት ቢሮ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ባደረገበት ወቅት ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ላይ የሚገኙትን በማብቃት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ትኩረት መደረጉም ተመላክቷል፡፡ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ቤተ መጻሕፍት ቤቶችን ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ፣ በተመረጡ የትምህርት አይነቶች ተማሪዎች በመረጧቸው መምህራን በትርፍ ጊዜ የማካካሻ ትምህር መስት እና ሌሎችም ተማሪዎችን ብቁ የሚያደርጉ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወነ ነው፡፡

የአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም 99 ሺህ 880 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ፡፡ የአስፈታኝ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም 470 እንደሆነ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡

በክልሉ እያሽቆለቆለ የቀጠለው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት በዚህ ዓመትም እንዳይቀጥል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ለአብነት    የደብረብርሐን ከተማ አስተዳደርን ዝግጅት እንመልከት፡- ከተማ አስተዳደሩ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲገቡ ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ብዙነህ እንደሚሉት በከተማው ባሉ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጀምሮ ውጤታቸው የላቀ እንዲሆን  ከዓመት ዓመት አዳጊ ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚህም ውጤት መመዝገቡን ነው ያስታወቁት።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም በተለይ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ለማድረግ ከመስከረም ጀምሮ የተለያየ ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በትምህርት ዘመኑ አጋማሽ በተሠራ የውጤት ትንተና ጥራትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስገኝተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ የትምህርት አይነቶች ላይ አሁንም ልዩ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ በጥናት ተጠቁሟል፡፡ ሂሳብ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ  የሚጠበቀው ለውጥ ካልተመዘገበባቸው የትምህርት አይነቶች ተጠቃሽ  መሆናቸውን ጥናቱ ጠቆሟል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ አሥር የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የትምህርት ተቋማትም በተያዘው የትምህርት ዓመት አንድ ሺህ 965 ተማሪዎችን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ያስፈትናሉ።

ትምህርት ቤቶችም  ተፈታኝ ተማሪዎቻቸው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ትምህርት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የሥነ ልቦና ዝግጅት እና የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ናቸው፡፡ በትምህርት ዘመኑ ከሚፈተኑት መካከል ከስድስት የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተሻለ የቴክኖሎጂ እውቀት ያላቸው አንድ ሺህ 390 ተማሪዎችን በኦንላይን እንዲፈተኑ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ መምሪያ ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡ ባለፈው የትምህርት ዓመት በኦንላይን የተፈተኑ ተማሪዎች በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግር ሳይገጥማቸው  የተሻለ ውጤት ማምጣታቸውንም    ኃላፊዋ አረጋግጠዋል፡፡  በተያዘው ዓመትም እንደ አምናው ተማሪዎች ችግር ሳይገጥማቸው ፈተናቸውን አጠናቀው ለውጤት እንዲበቁ ከደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ አዲስ በመሆኑ መደናገጥ ተፈጥሮ እንደነበር ግን ተፈታኝ ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሰረት አሁን ላይ ስጋታቸው መወገዱን ነግረውናል። በሥነ ልቦና የተዘጋጀ ተማሪ በፈተናው ውጤታማ እንደሚሆን በመገንዘብ በተሻለ ጥንካሬ ፈተናውን ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

ተማሪዎቹ ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው በቡድንም ይሁን በተናጠል እያጠኑ መሆኑን ነግረውናል፡፡ በየትምሕርት ቤታቸው ትምህርት ቀድሞ መጠናቀቁ ደግሞ ለጥናት ሰፋ ያለ ጊዜ ሰጥቷቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ መምህራን ክለሳ በማድረግ እና  ያለፉ ፈተናዎችንም እንዲሠሩ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑ ተማሪዎችን አስደስቷል፡፡ በዚህም የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ተስፋ አድርገዋል፡፡

ይህንን ሀሳብ የፊትአውራሪ ገበየሁ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህሩ ሽመልስ አጥላው አጠናክረውልናል፡፡ በእርግጥ ፈተናው በኦንላይን እንደሚሰጥ የተነገረው ዘግይቶ መሆኑ የልምምድ ጊዜውን እንዳሳጠረው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ፈተናውን የሚወስዱት ተማሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር የተላመዱ በመሆናቸው የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ለመላመድ ብዙም  ጊዜ እንዳልወሰደባቸው ነው የነገሩን፡፡

እንደ መምህር ሽመልስ ማብራሪያ ግን በአመዛኙ የተማሪዎች ዝግጅትና የመማር ፍላጎት አበረታች ቢሆንም በአንዳንድ ተማሪዎች ዘንድ ቸልተኛ የመሆን፣ የትምህርት ፍላጎት ማጣት እና መሰል ችግሮች ተስተውለዋል፡፡ ይህ በፍጥነት መታረም እንዳለበት ያነሱት መምህሩ፤ በተለይ ወላጆች ልጆቻቸውን በጥብቅ መከታተል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ፈተናው የሚሰጠው በደብረብርሐን ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከደብረብርሐን ከተማ ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር ለተማሪዎች ስለፈተና አሰጣጡ  የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀግብር አዘጋጅቷል፡፡ በመርሀ ግብሩም ተማሪዎች በሥነ ልቦና ረገድ የተዘጋጁ እንዲሆኑ ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡ የኦንላይን ፈተናው የሚሰጥበትን አግባብ፣ ከተማሪዎች ምን እንደሚጠበቅ እና የአፈታተን ሥርዓቱ ከወረቀት መር ወደ ቴክኖሎጂ ከመቀየሩ ባለፈ የተለየ ነገር ሊኖረው እንደማይችልም ለተማሪዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

በደብረብርሐን ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተሯ ረዳት ፕሮፌሰር መቅደስ ጌራወርቅ በበኩላቸው ፈተናው ከወረቀት ተኮር ወደ ኦንላይን መቀየሩን ተከትሎ በተፈታኞች ዘንድ ምንም አይነት መደናገጥ እንዳይኖር በቅድሚያ የሥነ ልቦና ዝግጅት የማላበስ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል። ሂደቱ በቀሪ የዝግጅት ጊዜያት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነግረውናል፡፡

የተማሪዎች ውጤታማነት የአንድ ወገን ድርሻ ብቻ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሯ፤ መምህራን የጀመሩትን ብቁ ዜጋ የማፍራት ተልዕኮ ይበልጥ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ ቤተሰብም ልጆቻቸውን ከሥራ ጫና ነጻ በማድረግ ትኩረታቸው ትምህርት ላይ ብቻ እንዲሆን ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ዋናው ድርሻ ግን የተማሪዎች መሆኑን የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰር መቅደስ፤ ሊያዘናጉ ከሚችሉ ማናቸውም ነገሮች ራስን መቆጠብ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ የራሳቸውን የትምህርት ልምድ መነሻ በማድረግም እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል  ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ በተለይ በወጣትነት ጊዜ ሀሳብን የሚሰርቁ እና የትምህርት ጊዜን ሊሸራርፉ የሚችሉ ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ጠንካራ አቋም መያዝ ይገባል፡፡ የዳይሬክተሯ ሀሳብ ነው፡፡

የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህልም በቀጥታ ከትምህርት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡ የመፈተኛ ጊዜው እየተቃረበ በመሆኑም ተማሪዎች ትጋታቸውን በማሳደግ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር መቅደስ እንዳሉት ፈተናው ከወረቀት ንክኪ ነጻ መሆኑ ጉልህ ሀገራዊ አበርክቶ እንዳለው ታምኖበታል፡፡ ይህም ለወረቀትና ቀለም ይወጣ የነበረን ከፍተኛ ገንዘብ ከብክነት ይታደጋል፤ ተማሪዎችም ራሳቸውን ይበልጥ ለቴክኖሎጂ ቅርብ እንዲያደርጉ መሰረት በመጣል ተወዳዳሪነታቸውን ያሳድጋል፡፡

በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ሁሉም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በኦንላይን እንዲፈተኑ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል። ይህም ብቻ ሳይሆን አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ እንዲያሟሉ በማድረግ ፈተናውን በየትምህርት ቤታቸው መስጠት እንደሚጀመርም መረጃው ጠቁሟል፡፡

(ደጀኔ በቀለ)

በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here