በጃፓን የሾፌሩ ወይም “ካንቴን” ክፍል በከፊል በሉል ቅርፅ የተሰራው የጭነት ማጓጓዣ መርከብ የእቃ ማሸጊያ ሳጥኖችን በመያዝ ዓቅሙ፣ በፍጥነቱ እና በነዳጅ ቆጣቢነቱ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
በጃፓን ያማጉቺ ከተማ የሚገኘው የመርከብ ጣቢያ ኢሞቶ የተሰኘው መርከብ ማጓጓዣ ድርጅት በዓውሮፕላን የአብራሪ ክፍል አምሳያ (ቅርፅ) የመጀመሪያውን መርከብ በማዘዝ ማሰራቱ ተገልጿል:: መርከቡ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ በጃፓን ከተሰሩት በግዝፈቱ የመጀመሪያ ቢሆንም ከሁሉም የተለየ ያደረገው ግን የፊት ለፊት ቅርጹ ነበር::
በማጓጓዣ ድርጅቱ የታዘዘው ቀደም ብሎ ያልተሞከረ በአውሮፕላን የፊት ቅርፅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራ ሲሆን ከቅርጹ ባሻገር ሌሎች ተመራጭ መገለጫዎችን ማካተቱም ነው የተብራራው:: ከተሻሻሉ ገፅታዎቹ መካከል ፊት ለፊቱ በከፊል በቅንፍ ቅርፅ መሰራቱ የነፋስ ግፊትን 50 በመቶ ማስቀረት ወይም መግታት መቻሉ ተጠቅሷል:: ይሄ በራሱ ለኃይል አማራጭ ይውል ከነበረው ነዳጅ 5በመቶ እንዲቀንስ ማሳቻሉ በውጤትነት ተቀምጧል::
በከፊል በሉል ቅርፅ የዘመነው መርከብ ለኃይል የሚያውለው ነዳጅ መቀነሱ በቀጥታ ወደከባቢ ዓየር የሚለቀቅ በካይ ትነትን ከመቀነስ ጋር እንደሚዛመድም ነው የተጠቆመው – በድረ ገጹ::
በ2015 እ.አ.አ ከተመረተው የመጀመሪያው ባለ ቅንፍ ወይም ከፊል ሉል ቅርፅ መርከብ ጋር በተመሳሳይ በ2018 ናግራ የመርከብ ማጓጓዣ ድርጅት እንዲሁም በ2022 ኖጋሚ በተሰኙ ድርጅቶች ትእዛዝ ተሰርተው ለአገልግሎት መብቃታቸውም ተብራርቷል::
በመርከብ ስሪት ወይም አምራች ድርጅቶች መሠረታዊ ለውጥ ያመጣው ከኤርባስ የመንገደኞች አውሮኘላን አፍንጫ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ቀደም ብሎ ያልተሞከረው ንድፍ ያልተደፈረ እንደነበር እና የሰራው ድርጅትም “የዓመቱ መርከብ” የሚል ማእረግ መቀዳጅቱን ነው ለንባብ ያበቃው::::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም