ለዓላማ መጽናት

0
9

“በትምህርቴ የላቀ ውጤት እንዳመጣ መምህሮቼ እና ቤተሰቦች   ትልቅ ቦታ አላቸው!” በማለት ሐሳቡን የጀመረልን ተማሪ  ደግነት ታረቀኝ ይባላል፡፡ ትውልድ እና ዕድገቱ በደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ ዝሀ ቀበሌ የሆነው ተማሪ ደግነት ዕድሜው ለትምህርት ደርሶ ት/ቤት  እስኪገባ ድረስ የታላቅ እህቱን ደብተር እና  መጽሐፍ እየተቀበለ ፊደል መለየት እንደቻለ ያስታውሳል፡፡ ይህም በሰባት ዓመቱ አንደኛ ክፍል ሲገባ ፊደላትን ለማወቅ ቀላል ሆነለት፡፡ በትምህርት ዓመቱ ማጠናቀቂያም 8ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ 2ኛ ክፍል ተዛወረ፡፡ እስከ ስድስተኛ ክፍል በነበሩት የክፍል ደረጃዎችም 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን ለቆ አያውቅም፡፡

የመምህራን እና የቤተሰቦቹ ድጋፍ እንዳልተለየው የሚናገረው ተማሪ ደግነት በተለይ አጎቱ አጋዥ መጽሐፍትን እና ሌሎች ለትምህርቱ የሚያግዙትን ቁሳቁሶች ገዝቶ እንደሰጠው ያስታውሳል፡፡ ታዲያ ያኔ ደግነት ለሚወደው ትመህርቱ አቅም የሚፈጥርለት ግብዓት በማግኘቱ በደስታ ስሜት አጐቱን “ተምሬ ስጨርስ ያደረግህልኝን ውለታ ለመመለስ ያብቃኝ!” በማለት ምስጋናውን ቃል በመግባት ገለፀለት፡፡ አጐቱም በአፀፋው “የኔን ውለታ የምትመልስልኝ አንደኛ ስትወጣ ነው” በማለት ነገ ሳይሆን ዛሬ በትምህርት ውጤቱ እንዲያረጋግጥለት ቃል አስገባው፡፡

ከባድ አደራና ኃላፊነት የተቀበለው ደግነት የአጐቱን ቃል ጠብቆ ከድሮው በበለጠ ትመህርቱን በአግባቡ ተከታተለ፤ ሰባተኛ ክፍል በአንደኛው መንፈቀ ዓመት በዘጠኝ የትምህርት ዓይነቶች /ከ900 ውጤት/  840 በማምጣት ሁለተኛ ደረጃን ያዘ፡፡ ይሁን እንጂ ያጐቱን አደራ ባለመወጣቱ ይበልጥ ቁጭት ተፈጥሮበት የበለጠ በማንበብ 847 ውጤት በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃን በመያዝ ወደ 8ኛ ክፍል ተዘዋወረ፡፡ አደራውን የተወጣው ደግነት አጎቱን ጨምሮ የሌሎች ቤተሰቦቹ  ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ደግነት የሚደረግለትን ማበረታቻ  ምርኩዝ አድርጐ ደረጃውን አስጠብቆ  መገስገሱን ቀጠለ፡፡

ይሁንና በአማራ ክልል በተከሰተው የሰላም እጦት በ2016 ዓ.ም ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው ነበር፡፡ ከነዚህ ተማሪዎች መካከል ደግሞ ደግነት አንዱ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ትምህርት ቤት ሄዶ መማር፣ የናፈቁትን መምህራን ማግኘት ቀረ፡፡ ይህን ወቅትም ሲያስታውሰው “በተለይ የፈተና ወቅት እና ውጤት የሚሰጥበትን ጊዜ ሳስበው አዝን ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከዚህ በኋላ ትምህርት ባይቀጥልስ? የሚል ጭንቀት ይስማኝ ነበር” በማለት ነበር፡፡

ደግነት ትምህርቱን  ካቋረጠ ከአንድ ዓመት  በኋላ /በ2017/ ዓ.ም ከአጐቱ ወደ  ባሕር ዳር በማቅናት በግዮን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ1ዐኛ ክፍል ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ከት/ቤቱ እና ከጓደኞቹ  ቢርቅም፣ ከወላጆቹ ቢለይም  የነበረውን ብቃቱን አሳድጐ በአንደኛው መንፈቀ ዓመት 94 ነጥብ ሁለት በማምጣት አንደኛ ደረጃ እንዲሁም በሁለተኛው መንፈቀ ዓመት  95 ነጥብ አምስት በማምጣት 2ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ 11 ክፍል ተዛውሯል፡፡

“አንድ ዓመት በማቋረጤ ባዝንም ተስፋ አልቆረጥሁም ነበር፡፡ ቀን ተመልሶ እማራለሁ፡፡ አንድ ቀን ትምህርት እጀመራለሁ! የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡ ያልሁት አልቀረም አሁን ትምህርቴን በመቀጠሌ በጣም ደስተኛ ነኝ!” በማለት በደስታ ስሜት አስተያየቱን ሰጥቶናል፡፡

ለደግነት የጥናት እና የክፍል ውስጥ ትምህርት ተሞክሮውን እንዲያካፍለን ጥያቄ አንስተንለት ነበር፡፡ “በየዕለቱ  በክፍል ውስጥ የተማርሁትን ዛሬ ምን ተማርሁ? በማለት  አጠናለሁ፡፡ ጥያቄዬ ከተመለሰልኝ በኋላ ለቀጣይ ቀን የምንማረውን ደግሞ በቀላሉ እንዲገባኝ ቀድሜ አጠናለሁ” ብሎናል፡፡

“እኔ ፈተና ደረሰ ብዬ አልሯሯጥም፡፡ ‘ሙሽራ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ’ የሚለውን አባባል ሳይሆን ‘ሙሽራ ሳይመጣ በርበሬ ቀንጥሱ’ አይነት መንገድ ነው የምከተል” በማለት የጥናት ስልቱን አካፍሎናል፡፡

ደግነት በግል እንደሚያጠናው ሁሉ የጋራ ጥናትንም ያደርጋል፡፡ “ብቻዬን በቂ ግንዛቤ ላልይዝ እችላለሁ፡፡ ምክንያቴ ደግሞ መምህራን ሲያስተምሩ እኔ የእነሱን ሀሳብ በትክክል ላልረዳ  እችላለሁ፡፡ በጋራ ሳጠና ግን እኔ ባልተረዳሁበት መንገድ ሌሎች ጓደኞቼ ተገንዝበው ይሆናል፡፡ እናም በጋራ ስናጠና ነገሮችን በብዙ አማራጮች ልረዳ እችላለሁ” ብሎናል፡፡

ደግነት በክፍል ውስጥ ሲማርም ያልገባው ካለ መምህራንን በክፍል ውስጥ ጠይቆ እንዲሁም ማጣቀሻ መጻሕፍትን በማንበብ ይረዳል፡፡ “ማንኛው ሰው በትምህርቱም ሆነ በሥራ ዓለም ለውጤታማነት ተፎካካሪ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ካስቀመጠው ራእይ መድረስ ይቻላል” የሚል ጽኑ እምነት ያለው ደግነት፤ ዘንድሮ ከ98 በመቶ በላይ ለማምት አቅዷል፡፡

ደግነት በመጨረሻም ባለፉት ዓመታት ትምህርት በተቋረጠባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች  ሰላም ሰፍኖ እንደሱ የትምህርት ዕድል እንዲያኙ ተመኝቶላቸዋል፡፡

 

መረጃ

ለፈተና ለመዘጋጀት የሚጠቅሙ  ነጥቦች

ምናልባት ነገሮችን ቦታ ቦታ ለማስያዝና እቅድ ለማውጣት የምታጠፉት  ጊዜ የባከነ ሊመስላችሁ ይችላል። ነገር ግን እውነታው በተቃራኒው ነው። ምክንያቱም ምን ማጥናት እንዳለባችሁና መቼ ማጥናት እንዳለባችሁ እቅዳችሁ ይነግራችኋል።

ከዚህ በተጨማሪም ምን ያክል እንደተጓዛችሁ ለመመዝገብና ለመከታተል ይረዳል።

የትኞቹን ማስታወሻ ደብተሮች መቼ መመልከት እንዳለባችሁ፣ የትኞቹን መጻህፍት ለተጨማሪ ማብራሪያ እንደምትጠቀሙ እንዲሁም የፈተና ጥያቄዎችን መቼ መለማመድ እንዳለባችሁ በእቅድ ውስጥ ማስገባት ውጤታማ ያደርጋል።

እዚህ ጋር መርሳት የሌለብን ለእረፍትና አካላዊ እንቅስቃሴም ቦታ መስጠት እንዳለብን ነ

    ከፋፍሎ ማጥናት፦

በአንድ የትምህርት ዓይነት ላይ 10 ሰዓት ሙሉ ከማሳለፍ በየቀኑ አንድ ሰዓት በማጥናት በ10 ቀን መጨረስ ውጤታማ ያደርጋል።

ያጠናነውን ለማስታወስና በቀላሉ ለመሸምደድ ጭንቅላት ጊዜ ይፈልጋል። ከፋፍሎ ማጥናት ደግሞ ለዚህ ፍቱን መድሃኒት ነው።

    ራሳችሁን ቶሎ ቶሎ ፈትኑ፦

የሥነ አዕምሮ ጥናት ባለሙያዎች እንደሚሉት የማስታወስ ችሎታን ለማዳበርና በራስ መተማመንን ለመጨመር ራስን መፈተን ውጤታማ ያደርጋል።

ከዚህ በተጨማሪ እየተዘጋጀንበት ያለነውን ጉዳይ በደንብ እንድናውቀው ከማድረጉ በተጨማሪ የረሳናቸው አልያም የዘለልናቸው ርዕሶችን ለመለየት ይረዳናል።

    መምህር መሆን፦

ከባዱን የክለሳና ራሳችሁን የመፈተን ሥራውን ካከናወናችሁ በኋላ ጓደኞቻችሁን ሰብሰብ አድርጋችሁ ራሳችሁን በመምህር ቦታ አድርጋችሁ እውቀታችሁን ለማካፈል ሞክሩ።

ይህ ዘዴ ምን ያህል እንደምታስታውሱ ለማወቅ ከመርዳቱ በተጨማሪ ጓደኞቻችሁንም ትጠቅሟቸዋላችሁ።

    ከተንቀሳቃሽ ስልካችሁ ራቅ በሉ፦

ስልክ በጣም ብዙ ጥቅም አለው። ነገር ግን በጥናት ወቅት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። በተለይ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያዎችን የምትጠቀሙ ከሆነ።

ብዙ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ብዙ ጊዜያቸውን ስልካቸው ላይ የሚያሳልፉ ተማሪዎች የትምህርት ውጤታቸው ሁሌም ቢሆን ዝቅ ያለ ነው። እናም ብትችሉ ስልካችሁን ከአጠገባችሁአታድርጉ።

ውጤታማ የክለሳ ጥናት ማለት እረፍት አልባ ጥናት ማለት አይደለም። በጥናት  መሀል መሀል ላይ ጥሩ አየር ለማግኘትና ሰውነታችንን ለማፍታታት ወጣ ብሎ እንቅስቃሴ ማድረግ የማስታወስ ችሎታን በደንብ ከፍ ያደርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሰውነታችን እና ጭንቅላታችን በእጅጉ የተሳሰሩ በመሆናቸው እንቅስቃሴ ስናደርግ የደም ዝውውራችን ይስተካከላል፤ ይህ ደግሞ በቂ ኦክስጅን ወደ ጭንቅላታችን እንዲሄድ ይረዳል።

አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግም ጭንቀትን መከላከልና በራስ መተማመንን ይጨምራል፡፡

 

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here