ስር የሰደደ የጀርባ ህመም ተጠቂዎችን በአቅራቢያቸው በሚገኝ ተፈጥሯዊ አካባቢ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ማስቻል አካልና አእምሯአቸውን በመቆጣጠር እፎይታን እንደሚያስገኝላቸው ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ከሣምንት በፊት አስነብቧል:: በአሜሪካ የኘሌይ ማውዝ እና ኤክስተር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እስከ 40 ዓመታት በጀርባ ህመም ተጠቅተው ህክምና የሚከታተሉ ህሙማንን በመጠየቅ ጥናት አካሂደዋል፡፡
ከውጤቱ የጀርባ ህመማቸውን መቋቋም እና የእፎይታ ጊዜ ማግኘት መቻላቸውን መገንዘብ ችለዋል – ተመራማሪዎቹ:: አብዛኛዎቹ በመጠየቅ ተካተው ምላሽ የሰጡ የጀርባ ህሙማን በቤት ውስጥ በተናጠል ጊዜ ማሳለፍ ህመማቸውን እያዳመጡ በከፋ የህመም ደረጃ እንዲጐብጡ ያስገድዳቸዋል፡፡ በመሆኑም ይህንን የተገነዘቡት ተመራማሪዎቹ ለችግሩ በማቀለያ መፍትሄነት በተፈጥሯዊ አካባቢ ማሳለፍን ማካተት እንደሚገባ ነው ያሰመሩበት:: በኒውጀርሲ የአከርካሪ ህመም ስፔሻሊስት ዶክተር ኤሪክፍሪማን ትክክል ባልሆነ ቴክኒክ እና ተገቢ ባልሆኑ መሣሪያዎች እገዛ የእግር ጉዞ ማድረግ የከፋ ተፅእኖ ሊያደርስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ይህን በማጤን በጥንቃቄ መንቀሣቀስ፣ የአከርካሪ አጥንት እና ማያያዣዎችን ያጠነክራል፤ አቀማመጥን በማሻሻል ህመሙንም ማቅለል ያስችላል:: ህሙማኑ ወደ ውጪ እንዲወጡ እና ወጣገባ ባልሆኑ ቦታዎች እንዲንቀሳቀሱ የመከሩት ባለሙያው ባልተደላደለ መሬት መንቀሳቀስ ሚዛንን አዛብቶ ህመምን እንደሚያከፋም ነው ያረጋገጡት:: ከተካሄደው ጥናት ማጠቃለያ ስር የሰደደ የጀርባ ህመም ያለባቸው ሰዎች እና ሀኪሞቻቸው ተፈጥሯዊ ከባቢ ለጤናቸው እና ለደህንነታቸው ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አምነው ትኩረት እንዲሰጡም ነው የመከሩት::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም