ለጋራ ሀገር የጋራ ትርክትን መገንባት

0
171

ኢትዮጵያውያን የዘር የቀለም የቋንቋ እንዲሁም የእምነት ልዩነቶች ሣይገድቧቸዉ ከጫፍ ጫፍ ያሉ በሙሉ ለዘመናት በአንድነት ያኖራቸው፣ ያጋመዳቸዉ እና ያስተሳሰራቸዉ  በርካታ የጋራ እሴቶች  ባለቤቶች ናቸው። ይሁንና እነዚሕን እሴቶቻችን አዳብሮ እና ጠብቆ ወደ ገዥ እሴትነት ከማምጣት ይልቅ ነጠላ ትርክት ላይ በስፋት ሲሠራ ቆይቷል። ሃላፊነት በማይሰማቸዉ አካላትና ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ አንዳንድ ሚዲያወች መረጃወችን ሳያጣሩ  እና ማረጋገጫ ሳይኖራቸው በሚለቀቁ አፍራሽ የሆኑ መልዕክቶች እና ለፖለቲካ መጠቀሚያነት በመዋላቸዉ እሴቶቻችን ላይ የመሸርሸር ዝንባሌ ፈጥረዉ ሃገራችን ላይም ችግሮች የራሱን አሉታዊ ጫና አሳርፏል።

በተለይም ባለፉት ሰላሳ አመታት ውስጥ በተሳሳተ መንገድ በተቀነቀነ ብሔርተኝነት እንዲሁም በሐገራችን ታሪክ ላይ ባለ የተለያየ አረዳድ ምክንያት   ሐገራችን ለግጭት እና ቀውስ ከተጋለጠች ውላ አድራለች።  በመሆኑም ከተጋረጠው ችግር ለመውጣት እና እንደከዚህ ቀደሙ በመከባበር አብሮ ለመኖር የሚያስችሉ ሐገራዊ የወል ትርክቶችን ማጠናከር እና መፍጠር  ለነገ የማያድር ተግባር ነው።

ኢትዮጵያዊነት በመስዋዕትነት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ የብዝሃነት እና የሕብረብሔራዊነት እሴት መገለጫ ነው። እሴቶቻችን የማንነት መገለጫዎች ብቻ ሳይሆኑ ማሕበረሰቡን ያጋመዱና ያስተሣሠሩ በመሆናቸው ለገዥ ትርክት ግንባታ በመጠቀም ከገጠመን ችግር ለመውጣት የሚያስችሉ ድልድዮች  በመሆናቸው ልንጠቀምባቸው  ይገባል።

በተለይም አንድ የሚያደርገንን በማጉላት፣ ብዝሐነትን ደግሞ እንደ ጌጥ መጠቀም ለነገ የማይባል ጉልሕ ተግባር ነው ። የጋራ እና አንድ የሚያደርጉንን እሴቶች ሆን ተብሎ በመሸርሸር ነጠላ ትርክቶች ላይ ሲሰራ በመቆየቱ እሴቶቻችንን    በመሸርሸር ወደ ነጠላ ትርክት አሳድጎ አክራሪ ብሔርተኝነት ፈጥሯል። በመሆኑም ከነጠላ ትርክት በመውጣት ወደ አሠባሳቢ እና የጋራ ትርክት ለመምጣት የተጀመረውን መልካም ጅምር ማስቀጠል የሁላችንም ድርሻ ነው።

በሐገራችን የተከሰተውን ችግር ለመሻገርም ሐገራዊ ታሪክ ላይ ተግባቦትን መፍጠር እንደሚገባ በሐምሌ ወር 2016 ዓ/ም በተካሄደው ሀገራዊ ታሪክን እና ሰላምን የተመለከተ ምክክር ላይ የተሣተፉ የታሪክ ምሑራን  ታሪክን የማያውቅ ዜጋ መሠረት የሌለው በመሆኑ ታሪክን በማሳወቅ እና የወል ትርክትን በመገንባት ሐገርን ማሣደግ እንዲቻል አስፈላጊነቱን አሣይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሦሥት ሽህ አመታት በላይ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ባለታሪክ የሆነች ሐገር ስትሆን መሠረቷም የብዝሐ ባሕል፣ የብዝሐ ሀገር በቀል እውቀት፣የብዝሐ ወግ፣ ልማዶች አብሮ የመኖር እሴቶች እና ትውፊቶች ባለቤት በመሆኗ ረጅም አመታትን እንደሐገር እንድትቀጥል አስችለዋታል። እነዚሕ ፀጋወችም በዘመናት ሂደት ውስጥ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ከተፈጠሩ በሗላም የችግሮች መፍቻ ቁልፍ በመሆን ሊያገለግላት እንደቆዩ እና አሁንም እያገለገሉ ነው።

ኢትዮጵያውያን በአንድ እንድንተሳስር የሚያስችሉ በርካታ ትውፊቶች  እና መገለጫወች አሉን፡፡  እነዚሕ እና ሌሎች እሴቶቻችን በአገራችን በተለያየ ቦታ የሚኖሩ ማሕበረሰቦች እንዲተዋወቁ፣ ተቻችለው እንዲኖሩ እልፍ ሲልም በጋብቻ ተጣምረው ኢትዮጵያዊነትን በማስቀጠልና በመጠበቅ በኩል አስቻይ ሐብቶቻችን ናቸው።

ሂስትሪ ዶት ኮም ላይ ያገኘነው መረጃ     እንዳስነበበው ብሔርተኝነትን መሠረት አድርገው ሀገረ መንግስታቸውን ያዋቀሩ ሀገራት በርካታ ችግሮችን አስተናግደዋል። የዚሕን ጦስ ተረድተው ፈጥነው ከዚሕ መዋቅር የወጡ እና ሀገራዊ አንድነትን አስቀድመው የሠሩ ሀገራትደግሞ ወደ እድገት ጎዳና ተመልሰዋል።ለዚሕ  ምሳሌ ተደርጋ የምትጠቀሠውም ሩዋንዳ ናት።

‘’ጠባሳን ያየ በእሳት አይጫወትም’’ እንዲሉ አበው በብሔር  ፣ በዘር እና በሐይማኖት መለያየት ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዛኝ በመሆኑ  ልዩነታችን ውበታችን መሆኑን በማሣየት ሁሉም በየብሔሩ አጥር  ከመከለል እና ትልቁን  ኢትዮጵያዊ ስዕልን  እንዲደበዝዝ ከማድረጉ በፊት ሐገራዊ አንድነትን ማጠናከር ተገቢና ጠቃሚ ጉዳይ ነወ።

ሐገራችን ከገባችበት ችግር  እንድትወጣ የሁሉም አካላት ሐላፊነት ያለበት ቢሆንም በተለይም ምሁራን በማስረጃ የተደገፈ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ታሪክን በማሣወቅ የጋራ ትርክትን በመገንባቱ ሒደት ድርሻቸው የጎላ መሆን አለበት።

በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here