ለግቡ ስኬታማነት ተጨማሪ የካርቦን ተጠያቂነት

0
115

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

የዓለም የሙቀት መጠንን አንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ ለመገደብ የተጣለው ግብ ሊሳካ የሚችለው የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች 17 ሀገራት በተናጠል ከሚጠበቅባቸው ባለፈ “ተጨማሪ የካርበን ተጠያቂነት”ን መወጣት ሲችሉ መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

በስዊድን ስቶክሆልም ዩኒቨርስቲ የተካሄደ አዲስ የጥናት ውጤት በፓሪስ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ የጣለውን ግብ ለማሳካት የውሮፓ ህብረት እና 17 ሌሎች አገራት  “ተጨማሪ የካርበን ተጠያቁነት”ን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክቷል፡፡

በ”ተጨማሪ የካርበን ተጠያቂነት” የተመላከተው መፍትሄ የተጠቀሱት አገራት በራሳቸው አገር ከሚከውኑት ባሻገር ከአገራቸው ውጪ ሌሎች እንዲከውኑ የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስቀምጧል፡፡

የአውሮፓ ህብረት እና 17ቱ ሀገራት በአገራቸው አንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠንን ለመገደብ ከሚያወጡት ወጪ ባሻገር ለሌሎች አገራት የሚከፍሉትን ተመን አመላክቷል፡፡ አዲሱ የጥናት ውጤት በስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ እና በኡኘሳላ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተደረገው ጥናት  አገራቱ የካርበን ልቀትን ከአገር ውስጥ ቁርጠኝነት ባለፈ በሌሎች ምን ያህል መቀነስ ወይም መገደብ እንደሚኖርባቸው ድርሻውን በቁጥር አስቀምጧል፡፡

የአገራት ትክክለኛ የካርበን እዳ ማለትም ለብክለት ያሳደሩት ተፅዕኖ እንዲሁም የወደፊት ልቀቶች ዒላማን ተንተርሶ አመላክቷል – የጥናቱ ውጤት፡፡

በጥናቱ ውጤት 18 ከፍተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት  “ተጨማሪ የካርበን ተጠያቂነት” ግዴታ ተቀምጦላቸዋል፡፡ ከ18ቱ አገራት ውስጥ ደግሞ 14ቱ በራሳቸው አገር ከሚወጡት ግዴታ በተጨማሪ ሌሎች አገራት የሚለቁትን ለማስወገድ የሚውል ወጪን መሸፈን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመፍትሄነት በቀረበው የጥናት ማደማደሚያ መሠረት የጥናቱ ውጤት በማሳያነት እንዳቀረበው በ2030 እ.አ.አ የተጣለውን የሙቀት ገደብ አንድ ነጥብ  አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ ከማድረስ ባሻገር በ2050 እ.አ.አ ከብክለት ነፃ ለመሆን የአውሮፓ ህብረት 48 ቢሊዬን ሜትርክ ቶን ካርበን ማስወገድ ወይም ሌሎች አገራት እንዲያስወግዱ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግን ግድ የሚል ነው፡፡

በማጠቃለያነት የግዙፍ ምጣኔ ሀብት ባለቤት የሆኑት አሜሪካ 167 ጌጋ ቶን፣ ቻይና ደግሞ 150 ጌጋ ቶን ወይም ቢሊዬን ሜትሪክ ቶን ካርበን ማስወገድ ወይም  ሌሎች አገራት ቅነሳዎችን እንዲከውኑ በገንዘብ መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here