ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? በቅርቡ የመጀመሪያውን ወሰነ ትምህርት አጋማሽ ፈተና ትወስዳላችሁ አይደል? ለፈተናው ዝግጅት ይረዷችሁ ዘንድ አንዳንድ ነጥቦችን እናጋራችሁ::
ልጆችዬ! የመጀመሪያው የጥናት ስልት ለመረዳትም ሆነ ለማስታወስ የሚያግዘው ውጤታማ የአጠናን ሥነ ዘዴ ቅኝት ማድረግ ነው:: ይህም አንድን የትምህርት አይነት ምዕራፍ ለማንበብ ከመጀመር በፊት አጠቃላይ ይዘቱን እና ርእሶቹን ማየትን ያጠቃልላል:: ቀጥሎ የሚመጣው ራስን ጥያቄ መጠየቅ ነው:: ይህ ማለት ስለሚጠናው ይዘት ምንነት እና በምዕራፉ ውስጥ ጠቃሚ ሊባል የሚችለው ነገር ምን እንደሆነ ራስን መጠየቅ መልስ ለማግኘት ስለሚገፋፋ ውጤታማ ለመሆን ይረዳል:: ይህን ተከትሎ ወደ ማንበብ ወይም ማጥናት መግባት ይገባል:: በዚህ ወቅት ታዲያ የይዘቱ ዋነኛ ቃላትን እስከ ፍቻቸው ማስመር ወይም ማስታወሻ ደብተር ላይ ማስፈር በቀላሉ ለማስታወስ እንደሚረዳ ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የመረጃ ድረ ገጽ የተገኘው ጽሑፍ ያትታል::
ተማሪዎች መጻሕፍትን እያነበቡ በሚያጠኑበት ወቅት አንኳር ይዘቶችን እያሳጠሩ በማስታወሻ ደብተር እንዲይዙ ይመከራል:: ይህም በመጽሐፉ ውስጥ ያሉ ይዘቶችን በቀላሉ ለማስታወስ እና አይረሴነት እንዲኖራቸው የማድረግ ዕድሉ ሰፊ ነው::
ክለሳን ባሕል ማድረግ ሌላው ጥሩ እና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርግ እንዲሁም ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል የአጠናን ዘዴ ተደርጎ ተመላክቷል:: በተጨማሪም የማስታወስ ችሎታን ለማዳበር እና በራስ የመተማመን ክህሎትን ለማሳደግ ራስን በራስ መፈተን እንዲሁም ከሌሎች ተማሪዎች ጋርም መጠያየቅ ይመከራል::
በእያንዳንዱ የጥናት ጊዜ በቂ ረፍት መውሰድ ይገባል:: ይህም አዕምሮን ዘና በማድረግ የተሻለ የጥናት አቀባበል እንዲኖር ያስችላል:: የእግር ጉዞ ማድረግ፣ የተለያዩ አካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን መሥራት፣ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ አጫጭር ፊልሞችን እና ድራማዎችን ማየት ለአዕምሮ ዳግም ዝግጁነት ያግዛል::
ጥናቱ ግቡን እንዲመታ ፀጥ ያለ ቦታን መምረጥ፣ ከተንቀሳቃሽ ስልክ ነጻ መሆን፣ ጥናትን ይዘቱ ከባድ ነው ከሚባለው የትምህርት አይነት መጀመር፣ ያለፉ ፈተናዎችን እና መልመጃዎችን መሥራት ዓመቱን ብቁ ሆኖ ለማጠናማቀቅ የሚያግዙ የፈተና መዘጋጃ ዘዴዎች ናቸው::
ተረት
ኳሱ
በአባቴ አሮጌ ካልሲ የሰራሁትን ምርጥ ኳስ ከግድግዳው ጋር እያጋጨሁ እየተጫወትኩ ነው:: ግድግዳው የኔ ተጋጣሚ ነው:: “ኧረ ተው ግድግዳውን ታፈርሳለህ!” አለችኝ እናቴ በበሩ ብቅ ብላ:: አንድ ጊዜ እንደገና ኳሱን ከግድግዳው ጋር አጋጨሁት:: “ኧረ ተው እንተ ልጅ! ተው! ካለዚያ ኳሱን ነው የምቀማህ!” አለችኝ በድጋሚ በጣም ተቆጥታ:: “እሺ እተዋለሁ!” ብዬ አጉረመረምኩ:: ኳሱን ከግድግዳ ጋር ማጋጨቱን ትቼ ወደ ላይ እየወረወርኩ መቅለብና መጫወት ጀመርኩ:: ግን ወዲያው ሰለቸኝና ዞር ዞር ብዬ ስመለከት አሪፍ አጫዋች አገኘሁ፤ የቤታችን ጣራ:: ኳሱን ጣራ ላይ እየወረወርኩ ተንከባሎ ሲመጣ ልክ እንደ በረኛ ቀለብኩት፤ ልክ እንደ ተከላካይ ወደ ጣራው ጠለዝኩት:: ተንከባሎ ሲመጣ ቀለብኩት:: ‘ደስ ሲል’ አሁን ደግሞ ልክ እንደ አጥቂ ተጫዋች ሆኜ መታሁት:: ወይኔ! ተመልሶ አልወረደም:: ኳሱ ጣራው ላይ ቀረ::
“ይሄን ልጅ ምን ባደርገው ይሻለኛል? እባካችሁ! ለምንድን ነው የምነግርህን የማትሰማው? አምጣ ወዲህ ኳሱን! የታለ?” አለችኝ እናቴ በረንዳው ላይ ቆማ:: በጣም ተቆጥታለች:: “ጣራው ላይ ተሰቀለብኝ … እማ …” ለመግለፅ ተንተባተብኩ::
“ጎሽ! ግልግል ነው:: እኛም ሰላም እናገኛለን” አለችኝ ጭንቅላቷን እየነቀነቀች:: መጥረጊያችንን አመጣሁና ኳሱን ከጣራው ላይ ለማውረድ ሞከርኩኝ፤ አልደርስ አለኝ፤ እንዲረዝምልኝ በማሰብ ሌላ እንጨት መጥረጊያው ላይ ቀጠልኩበትና በእሱ ለማውረድ ሞከርኩኝ:: ግን ኳሱ አጠገብ እንኳን ሊደርስልኝ አልቻለም::
በነጋታው ኳሴ እንዴት እንዳደረ ለማየት በጠዋት ከቤት ወጣሁ:: እዚያው ጣራው ላይ እንዳለ ነው:: ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዴ በፊት በምልክት ተሰናበትኩት:: “ኳስህን ለምን አላመጣህም?” በማለት ጓደኞቼ ጠየቁኝ:: “ጣራ ላይ ተሰቀለብኝ” አልኳቸው:: ሁለት እንጨቶች ቀጣጥዬ ለማውረድ ሞክሬ እንዳልተሳካልኝ ሁሉ ነገርኳቸው:: “በድንጋይ ሞክረው!” አለኝ አንዱ ጓደኛዬ:: “እንደሱማ ማድረግ አልችልም:: እናቴ ትቆጣኛለች!” አልኩኝ እራሴን እየነቀነቅኩ:: ከሁለት ቀናት በኋላ ከየት መጣ ሳይባል እንድ ቁራ ጣራችን ላይ አረፈ:: ደስ በሚል ሁኔታ አየኝና ወደ ኳሱ ተመለከተ:: ቀስ እያለ ወደ ኳሱ አቅጣጫ ሄደና በመንቁሩ ኳሱን ነካ ሲያደርገው በመደነቅ ተመለከትኩት:: ኳሱ በቀላሉ ከጣራው ላይ እየተንከባለለ ወደ እኔ መጣ:: መሬት ላይ እንዲያርፍ አልፈለኩም:: እንደ አንድ ለአጭር ጊዜ ከቤተሰቡ ርቆ እንደተመለሰ ወንድም እቅፍ አደረግኩት፤ ተደስትኩም:: “አመሰግናለሁ!” አልኩት ያን መልካም ቁራ:: በአነጣጣሪው አይኑ ተመለከተኝና አንገቱን ነቅነቅ አደረገ:: ሊረዳኝ ፈልጎ እንደመጣ አምኛለሁ:: እናም ላመሰግነው ወደድኩ::
ምንጭ፡- ተረት ከቡቡ ጋር
ይሞክሩ
በኢትዮጵያ ትልቁ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ማን ይባላል?
የኢትዮጵያ የቀድሞ ስሟ ማን ይባላል?
ስልክን የፈጠረው ሰው ማን ይባላል?
መልስ
ንጋት
አቢሲኒያ
አሌክሳንድር ግራምቤ
ነገር በምሳሌ
- የዝንጀሮ ልጅ ከዛፍ የመምህር ልጅ ከመጽሐፍ ይውላል፤
ሰው ሁሉ በሚያውቀው (በሚችለው) መስክ ይሰማራል፡፡
- ከስብ ስም ይሸታል፤
አንዴ ስም ከጠፋ መመለስ ካባድ ነው፡፡
- ወፍ የሚፈራ ዘንጋዳ አይዘራም፤
ወደፊት የሚሆነው ተፈርቶ ሥራን (ተግባርን) ማቆም አያስፈልግም፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


