ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱስ እንዴት አለፈ? የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ትምህርት ሊጠናቀቅ የቀሩት ግዜያት ጥቂት ናቸው:: ታዲያ ልጆች በነዚህ ግዜያት በርትታችሁ መማርና ማጥናት ይኖርባችኋል:: ያልገባችሁ ትምህርት ካለ ደግሞ መምህራኖቻችሁን፣ ወላጆቻችሁን እና አስጠኚዎቻችሁን መጠየቅ አለባችሁ::
ልጆች ለመሆኑ እናንተ በምን አይነት መንገድ ነው የምታጠኑት? በትምህርታችሁ የተሻለ ውጤት ለማምጣትስ የተለየ የአጠናን ዘዴ ትከተላላችሁ? መቼም መልሳችሁ ‹‹አዎ›› እንደሚሆን አንጠራጠርም::
ልጆች! ከዚህ በታች የተዘረዘሩት እና ትምህርትን በተሻለ ሁኔታ ለማጥናት የሚያስችሉ ደረጃዎች ናቸው ::
ልጆች እናንተም እነዚህን ደረጃዎች ተግባራዊ በማድረግ ብታጠኑ በትምህርታችሁ የተሻለ ውጤት እንደምታመጡ ተስፋ እናደርጋለሁ::
አስቀድማችሁ አቅዱ
ለዓርብ ፈተና ለማጥናት እስከ ሐሙስ ምሽት ድረስ መጠበቅ ሞኝነት ነው:: የተሻለ ውጤት ለማምጣትም አስቸጋሪ ይሆናል:: ስለዚህ ከፈተና በፊት አስቀድሞ ማቀድና ማጥናት አስፈላጊ ነው:: ፈተና የሚሰጥበትን ቀን መዝግባችሁ ያዙ:: ይህም በእያንዳንዱ ቀን ምን ምን ማድረግ እንዳለባችሁ እና በእያንዳንዱ ርዕስ ላይ ምን ያህል ግዜ ማጥፋት እንዳለባችሁ ለማቀድ ይረዳችኋል::
ከፋፍላችሁ ለማጥናት ሞክሩ
የምታጠኑት ትምህርት በርከት ያለ ከሆነ በየትምህርት አይነቱና እንደየርዕሰ ጉዳዩ በመከፋፈል ነጣጥሎ ማጥናቱ ይጠቅማችኋል:: ጠቅለል ባለው የትምህርት አይነት ላይ አተኩሮ ከማጥናት፤ በውስጡ የያዘውን ርዕሰ ጉዳይ በመነጣጠል ማጥናቱ ይመረጣል:: ሌላኛው ትምህርትን ከፋፍሎ ለማጥናት የሚያግዘው መንገድ በየቀኑ ማጥናት ነው:: ይህም ሁሌ ማስታወሻዎቻችሁን ለመከለስና የተማራችኋቸውን ምዕራፎች ለመቃኘት ያግዛችኋል::
ግርታ ከተፈጠረ እርዳታ ጠይቁ
ትምህርቱን ካልተረዳችሁ በአግባቡ ማጥናት አትችሉም:: ያልገባችሁ ነገር ካለ መምህራኖቻችሁን ከመጠየቅ ወደኋላ አትበሉ:: የተፈጠረውን ግርታ ማስታወሻዎቻችሁን ዳግም በማንበብም መፍታት ትችላላችሁ:: በቤታችሁ ሆናችሁ ያልገባችሁ ነገር ካጋጠማችሁ ደግሞ ወላጆቻችሁን በመጠየቅ መረዳት ይቻላል::
በተጨማሪም
ልጆች ለጥናት ዝግጅት ካደረጋችሁ በኋላ ከፈተና በፊት በቂ እንቅልፍ ውሰዱ፣ አዕምሮ ዘና የሚያደርጉ ነገሮችን አድርጉ እንዲሁም ስለፈተናው ላለመጨነቅ ሞክሩ፡፡ በፈተናው ጊዜ ደግሞ ራሳችሁን አረጋጉ፣ በመጀመሪያ ቀለል ያሉትን ጥያቄዎች ሥሩ፣ ቀጥሎ ከበድ የሚሉትን ሥሩ፡፡ ጊዜያችሁን በአግባቡ ለመጠቀም ሞክሩ፡፡ እነዚህን እና ሌሎች የምታውቋቸውን ስልቶች ከተጠቀማችሁ ጥሩ ውጤት ታመጣላችሁ፡፡ ሰላም ልጆች!
ተረት
ብልጧ አይጠ መጎጥ
በአንድ ወቅት አንዲት አይጠ መጎጥ ነበረች:: ታዲያ ይህች አይጠ መጎጥ በበጋ ወራት እኩለ ቀን በጠራራው ፀሐይ ላይ ቆማ የበረዳት በመምሰል ትንዘፈዘፍ ነበር:: እናም አንድ ሰው በየቀኑ ይመለከታታል። ይኸው ሰው ታዲያ ስለጉዳዩ ማወቅ ፈልጎ ወደ አይጠ መጎጧ በመሄድ “አንቺ አይጠ መጎጥ” ይላታል:: እርሷም እየተንቀጠቀጠች “ወ,,,,,, ,,ወ,,,,,ይ,,,,,,ወ,,,,,,ወ,,,,,ይ ምንድነው የምትፈልገው?” አለችው:: ሰውየውም “ላለፈው አንድ ሳምንት ሙሉ ስመለከትሽ ነበርና በየቀኑ ልክ በቀትር ሰአት ቀኑ እጅጉን በሚሞቅበትና ፀሐይዋም ከአናት ላይ ሆና ሙቀቱ በሚያቃጥልበት ሰዓት አንቺ ከቤትሽ ወጥተሽ ልክ እንደበረደው ትንቀጠቀጫለሽ:: ይህ ለምንድነው?” ብሎ ጠየቃት::
እርሷም “አይ አንተ የሰው ፍጡር! አንተ የምታስበው ስለ አሁን ብቻ ነው:: የወደፊቱን አሻግረህ ስለነገው አታስብም:: በጣም የቅርቡን ብቻ ነውና የምትመለከተው ለምን አሻግረህ ለማየት አትሞክርም?” አለችው::
ሰውየውም በመልሷ ተገርሞ “እባክሽ ለምን እንደምትንቀጠቀጪ ንገሪኝ፣ እባክሽ ንገሪኝ?” አላት:: እርሷም “አይ አንተ የሰው ፍጡር:: እንዲያው ምንም አይገባህም አይደል? እኔ እያደረኩ ያለሁት ሰውነቴን በማዘጋጀት ራሴን ከሚቀጥሉት ስድስት ቀዝቃዛ የክረምት ወራት ጋር ከአሁኑ እያላመድኩ ነው::” አለችው:: የዚህም ታሪክ መልዕክት አሻግሮ በመመልከት ወደፊት ሊመጣ ለሚችል ችግር ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል የሚል ነው::
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች መጽሐፍ
ሞክሩ
- ፊትና ጀርባ ያለው፤ አካል የሌለው ማን ነው ?
- ስምንት ሰዎች በአንድ ሰዓት የጨረሱትን ግንብ አራት ሰዎች በስንት ሰዓት ይሰሩታል?
- አንድን ጋዜጣ በግማሽ እኩል ማጠፍ የምንችለው ስንት ጊዜ ነው?
መልስ
- ሳንቲም (ዘውድ እና ጎፈር)
- ሥራው ስለተሰራ ምንም ጊዜ አይጠይቅም፡፡
- አንድ ጊዜ ምክንያቱም ከደገምነው ግማሽ ሳይሆን መጠኑ ሩብ ይሆናል፡፡
ነገር በምሳሌ
- ልጅ እንዳባቱ፣ ሰው እንደቤቱ- ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አያድርም፡፡
- መላ እንደ ሴት፣ ግርማ እንደ ሌሊት- ሴቶች መላ መፍጠር ይችሉበታል፡፡
- መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውላል- በህይወት እያለ መልካም የሠራ ሁሉ ሙቶም በስራዎቹ ሲታወስ ይኖራል፡፡


