ለፍጥረታት ሁሉ መሠረቱ

0
73

ጃሬድ ዳይመንድ (Jared Daimond) የተባለው ጸሐፊ ውድቀት (Colapes) በተሰኘው መጽሐፉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በተገቢው መንገድ የማይዙ እና ጥቅም ላይ የማያውሉ ማኅበረሰቦች ለተጎዳ (ለምነቱ ለጎደለው) ሥነ ምሕዳር እና ለአጥፍቶ መጥፋት አደጋ ይጋለጣሉ ይላል። ሚዛን ያልጠበቀ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ የደኖች መመናመን፣ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመር፣ የብዝኃ ሕይወት መቀነስ … ለተጠቀሰው አደጋ ምክንያቶች መሆናቸውን ከምድረ ገፅ የጠፉ ማኅበረሰቦች ታሪክ ዋቢ መሆኑን ጠቅሷል። ስለሆነም ከዚህ መሰል አደጋ ለመታደግ ተፈጥሮን መጠበቅ እና ችግኝ ተክሎ መንከባከብ አማራጭ የሌለው መሆኑን አስቀምጧል።

የተለያዩ ሀገራት ወደ ተሻለ የምጣኔ ሀብት ዕድገት መሸጋገር የቻሉት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን አጠናክረው በመቀጠላቸው ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። ለአብነትም ደቡብ ኮሪያ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ተጠቃሽ ሀገር ስትሆን  አርሶ አደሮቿ እርከንን በመሥራት፣ ችግኝ በመትከል፣ የተተከሉትን በመንከባከብ፣ የሚወጡ ሕግ እና ደንቦችን ተግባራዊ አድርገው በመሥራታቸው የአየር ንብረት ለውጥ እንዲስተካከል እና ምርታማነት እንዲጨምር መሠረት እንደሆነላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

በሀገራችንም በተለይ በነገሥታቱ ዘመን የተሻለ የደን ሽፋን እንደነበር ድርሳናት ያሳያሉ፤ በተመሳሳይ በአማራ ክልል ከ1970ዎቹ  ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ መከናወን መጀመሩን ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በክልሉ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ይበልጥ መነቃቃቱን መረጃው ያክላል። በመሆኑም የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ እና በማልማት፣ የአፈር ለምነትን በማሳደግ እና የምርት መጠንን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያስገነዝባል። የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ግብርናው መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ፣ የውኃ ምንጮች እንዲጎለብቱ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ የአፈር ለምነት እንዲጨምር፣ አረንጓዴ ልማት እንዲያድግ፣  ጤናማ እና የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲኖር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ጠቅሷል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምሕረት ለበኩር ጋዜጣ እንዳስታወቁት በክልሉ በ2017 ዓ.ም “የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ለዘላቂ ምርታማነት ዕድገት” በሚል መሪ ሐሳብ የተቀናጀ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ልማት ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል። 366 ሺህ 649 ሄክታር መሬት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፤ በዚህም 375 ሺህ 963 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሥነ አካላዊ ሥራዎች መሸፈን ተችሏል። ዘጠኝ ሺህ 87 ተፋሰሶች ላይ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራም ተከናውኗል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ (የተፋሰስ ሥራ) የአርሶ አደሩን የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፤ አርሶ አደሩ በባለቤትነት በመሥራቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ለውጥ መምጣቱን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። በክልሉ ባለፉት ዓመታት ተራራማ ቦታዎችን መሠረት ያደረገ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ሲከናወን መቆየቱንም ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ዓመቱን በሙሉ የሚሠራ በመሆኑ በቅንጅት መሥራትን ይጠይቃል።

በተመሳሳይ ከተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ጎን ለጎን የክልሉ ግብርና ቢሮ ለአረንጓዴ አሻራ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አቶ እስመለዓለም ገልፀዋል። የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ ሦስት በመቶ አሽቆልቁሎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ እስመለዓለም ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ኢትዮጵያ ፖሊሲ ቀርፃ ስትሠራ ቆይታለች፤ እየሠራችም ትገኛለች ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአረንጓዴ አሻራ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የተራቆቱ አካባቢዎች አገግመዋል፣ የአፈር መሸርሸር ቀንሷል፣ የኢትዮጵያ የደን ሽፋንም ወደ 23 ነጥብ ስድስት በመቶ ከፍ ማለቱን ከግብርና ሚኒስቴር ድረ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። በአማራ ክልል ደግሞ የደን ሽፋኑ 16 ነጥብ ሦስት በመቶ እንደደረሰ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል። የሚተከሉ ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎች፣ ለጥምር ደን እርሻ፣ ለደን ልማት እና ለአካባቢ ጥበቃ የሚያገለግሉ መሆናቸውንም አቶ እስመለዓለም ተናግረዋል። ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ኮሶ፣ ፅድ፣ ግራር፣ ግራቪሊያ፣ ባሕር ዛፍ፣ ዲከረንስ (ከሰል ለማምረት የሚጠቅም ዛፍ) እና መሰል ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል። በአጭር ጊዜ የሚደርሱ እና ምርታቸው የተሻለ የሆኑ የአትክልት ዝርያዎችን ለመትከልም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። በተጨማሪም አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያን ጨምሮ ሌሎች የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቅሰዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ልዩ ትኩረት ተሠጥቶት እየተሠራ ይገኛል። ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችም ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው። በክልሉ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የተከናወኑ ተግባራት በአካባቢ ሥነ ምሕዳር ላይ አወንታዊ ለውጥ ማምጣት እንደቻሉም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፤ በቀጣይ የክረምት ወራት (ለ2017 ዓ.ም) የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለማከናወን በተለያዩ አካባቢዎች አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ ባለሙያዎች እና አመራሮች ተናበው በሚሠሩበት መንገድ መግባባት ላይ ተደርሶ እየተሠራም ነው።

ችግኝ ጣቢያ ማዘጋጀት፣ ችግኝ ማፍላት (ማዘጋጀት)፣ የተከላ ቦታ መለየት፣ የሚስማማውን የአፈር አይነት መምረጥ፣ ለችግኙ የሚሆን ግብዓት (ፕላስቲክ) ማዘጋጀት፣ ደረጃውን የጠበቀ ጉድጓድ ማዘጋጀት፣ ከአየር ንብረቱ ጋር የሚስማማ ችግኝ መምረጥ፣ የትኛው ችግኝ ለየትኛው አካባቢ ያስፈልጋል የሚሉት እና መሰል ተግባራት በቅድመ ዝግጅት የተከናወኑ ተግባራት ናቸው።

ዳይሬክተሩ አክለውም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ተግባር ሥራው ለመግባት በዝግጅት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት። በመሆኑም በወቅቱ በመትከል መንከባከብ ማጽደቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ነው ያሳሰቡት፡፡

አቶ እስመለዓም እንደተናገሩት በአማራ ክልል በ69 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ ለማፍላት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፤ እስካሁንም አንድ ነጥብ 46 ቢሊዮን ችግኝ ተፈልቶ ዝግጁ ሆኗል። ከችግኝ ማፍላት ጎን ለጎንም የመትከያ ቦታ የመለየት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

በመርሐ ግብሩ 207 ሺህ 809 ሄክታር የመትከያ መሬት ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን ከ201 ሺህ ሄክታር በላይ የመትከያ ቦታ ተለይቶ ዝግጁ መደረጉን አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ለችግኝ መትከያ የሚውል 200 ሚሊዮን ጉድጓድ ተዘጋጅቷል፤ ለመትከያ አገልግሎት ለሚውሉ ቦታዎች የካርታ ልየታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነም ይገኛል፡፡ የመትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ በግንቦት ወር ለማጠናቀቅ እየተሠራ ስለመሆኑም ተመላክቷል።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የችግኞችን የጽድቀት ምጣኔ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፤ ለአብነትም ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ ችግኞች በችግኝ ጣቢያዎች እንዳሉ ውኃ ማጠጣትን በመቀነስ፣ ሥራቸውን በመግረዝ፣ ዳሱን በማንሳት እና ፀሐይ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ዕጥረትን እንዲቋቋሙ (ችግር የማላመድ) ሥራ የሚሠራ ይሆናል ነው ያሉት። ይህም የጽድቀት ምጣኔን የሚጨምር የማላመድ ተግባር ነው፡፡

የችግኝ ማፍላት ሥራው በአብዛኛው በግለሰብ የችግኝ ቦታዎች የተከናወነ ነው፤ በሌላ በኩል አፍልቶ ለማቅረብ ረዥም ጊዜ የሚወስዱ፣ ሀገር በቀል የፍራፍሬ ችግኞች፣ እየጠፉ ያሉ እና ኅብረተሰቡ የማያውቃቸው (አዳዲስ) ዝርያዎች ደግሞ በመንግሥት የችግኝ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በማኅበራት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በተቋማት የችግኝ ማፍላት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ከተከላ በኋላም የፅድቀት መጠኑን መከታተል፣ መኮትኮት፣ ማረም፣ ውኃ ማጠጣት፣ ግብዓት (ፍግ) መጨመር፣  ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ማድረግ፣ በበሽታ እንዳይጠቁ ክትትል ማድረግ እና በጠፉት ችግኞች ምትክ ተከታትሎ መተካት አስፈላጊ ነው።

በአጠቃላይ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ዓመቱን ሙሉ ክትትል እና ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል። ችግኝ መትከል የውኃ አካላትን ለማጎልበት (ምንጮች እንዲበራከቱ)፣ የመሬት ውኃ የመያዝ አቅም እንዲጨምር፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጎርፍ፣ ድርቅ እና መሰል አደጋዎችን ለመቋቋም፣ ለመድኃኒት መቀመሚያ፣ ለዱር እንስሳት መጠለያ፣ ለውጭ ምንዛሪ ማስገኛ፣ ንፁህ አየር (ኦክስጂን) ለማግኘት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣  የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና ለምነትን ለመጨመር፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚሰጥ አቶ እስመለዓለም አስረድተዋል። ትውልዱ አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ኅብረተሰቡ መኖሪያ አካባቢውን በዕፅዋት በመሸፍን ለኑሮ ተስማሚ እና አረንጓዴ ስፍራን መፍጠር ይኖርበታል ሲሉም ሙያዊ ምክረ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም በሚከናወነው የችግኝ ተከላ በክልሉ አሁን ያለውን 16 ነጥብ ሦስት በመቶ የደን ሽፋን ወደ 17 ነጥብ ሦስት በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here