ላልገባን ላንቲካችን  ለገባን ግን መዳኛችን

0
37

ጤና ይስጥልኝ የበኩር ስፖርት ቤተሰቦች! መቼስ “ነገርን ነገር ያነሳዋል” ይባል የለ! ሰሞኑን አንድ እድሜ ጠገብ ሙዚቃ ድንገት ወደጀሮዬ ዘለቀና ይችን መጣጥፍ ወደ እናንተ እንዳደርስ ጋበዘኝ::

ሙዚቃው የተስፋዬ ገብሬ ነው:: “እናት ኢትዮጵያ ውዲቷ ሀገሬ፤ በጣም ይወድሻል ተስፋዬ ገብሬ” በሚሉት የመዚቃ ስንኞቹ የምናውቀው ተስፋዬ በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ያዜመው “ስፖርት” የተሰኜ ዘፈኑም ሌላው መታወቂያው ነበር::

ስፖርትን በአዝማችነት በመደጋገም ፋይዳዎቹን እየዘረዘረ ሰዎች ሁሉ ስፖርትን እንዲያዘወትሩ በማራኪ ውብ ድምፅ የሚቀሰቅስበትን ይህንኑ ሙዚቃ በሰማሁ ጊዜ ታዲያ ለመሆኑ ስፖርት ምንድን ነው? ፋይዳውስ? የሚሉትን ጥያቄዎች አሰብኩና ለጥያቄዎቹ የስፖርት ሳይንስ የሚሰጠውን ምላሽ  እደ አንባቢ ለማድረስ ብዕር ከወረቀት ተገናኙ::

ከምንነቱ እንጀምር:: ከበርካታ የስፖርት ድረገፆች የቃረምነው መረጃ የሚያመላክተን ተመሳሳይ ብያኔዎችን ነው:: ሲጨመቅ “ስምርት የአካል ብቃት እና  ችሎታን የሚጠብቅ ወይም የሚያሻሽል አካላዊ እንቅስቃሴ ወይም ጨዋታ ነው” ይለናል::

ስፖርት በአጠቃላይ በአካላዊ አትሌቲክስ ወይም በአካላዊ ቅልጥፍና ላይ የተመሰረተ የእንቅስቃሴ ስርዓት ነው ከሚለው ብያኔ በመነሳትም የአውሮፓ ምክር ቤትን ጨምሮ አንዳንድ ድርጅቶች እንደቼዝ አይነት ጨዋታዎችን እንደ ስፖርት መቁጠርን ይከለክላሉ:: በአንፃሩ ደግሞ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን የሚቆጣጠረው ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ “ቼዝ” እና bridge የተሰኙ ሁለት ውድድሮችን የአእምሮ ስፖርት በሚል እውቅና ሲሰጣቸው ዓለም አቀፉ የስፖርት ፌዴሬሽን ማህበር በበኩሉ ከ’ቼዝ” እና “ብሪጅ” ጋር ድራውትስ፣ ጎ እና ዣንግኪ የተባሉትን ጨምሮ ለአምስቱ አካላዊ እንቅስቃሴ አልባ ጨዋታዎችና ውድድሮች እውቅና ሰጥቷል::

ክዋኔውን በተመለከተ ስፖርት በቤት፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እና በጐዳናዎች ጭምር በነጠላ አለያም በቡድን ሊካሄድ የሚችል ሆኖ ለተሳታፊዎች ደስታን፣ ለታዳሚ ደግሞ ተዝናኖትን የሚሰጥ ነው::

ብዙውን ጊዜ የተደራጀ እና ውድድር ያለበት ሲሆን ደግሞ ፍትሃዊ ውድድርን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ህጎች ወይም ልማዶች ያሉት እና ቴክኒካዊ አፈፃፀም ወይም ንብባዊ ግንዛቤን መሰረት ባደረጉ መላኪያዎች የሚመሩ ዳኞች የሚቆጣጠሩት ክዋኔ ነው::

ለስፖርት ለየት ያለ ትንታኔ ከሰጡ ባለሙያዎች መሀከል ጀርመናዊው የስፖርት ሳይንስ ሊቅ ካርል ዲም ስፖርትን “የስራ ተቃራኒ ነው” ይለዋል:: ሰዎች ስራ የሚሰሩት መኖር ስላለባቸው ነው፤ ይኼ ደግሞ ግዴታ ነው” ይልና “ስፖርት የሚሰሩት ግን ስለሚፈልጉት ብቻ ነው፤ ያለግዳጅ በፈቃደኝነት::” ይላል:: አያይዞም “እምቢተኛ ልጆች በወላጆቻቸው አለያም በመምህሮቻቸው ተገደው ኳስ ቢጫወቱ እሱ ስፖርት አይደለም” ይልና “ለደሞዝ ብሎ ብቻ የሚሮጥ አትሌትም ካለ እሱን ስፖርተኛ አንለውም” ሲል ስፖርት ያለ አንዳች አስገዳጅ ምክንያት በሙሉ ፈቃድ የምትፈፅመው አካላዊ እንቅስቃሴ፣ ጨዋታ ወይም ውድድር እንደሆነ ያሰምርበታል::

ወደ ፋይዳው እንሻገር:: ያለነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንደመሆኑ የስፖርትን ጥቅም ከማያውቀው ይልቅ የሚያውቀው ህዝብ ቁጥር እንደሚልቅ መገመት ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል:: ቢሆንም ግን ዛሬም ድረስ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን፣ ጨዋታ እና ውድድርን  “እዬዬም ሲደላ ነው” ከሚል ብሂል ጋር የሞላላቸው፤ የደላቸው አለያም መተዳደሪያቸው ያደረጉት ሰዎች ብቻ የሚሰሩት እና የሚታደሙበት አድርገው የሚቆጥሩ በርካታ ሰዎች መኖራቸው አሌ አይባልምና ከዘርፈ ብዙ ፋይዳው ጥቂቱን ማስታወስ ተገቢ ይመስለናል::

የመጣጥፋችን መነሻ ተስፋዬ ገብሬ

ስፖርት ለምርት

ለወዳጅት

ለአካል ማጐልመሻ

ለመንፈስ ማደሻ

ለአእምሮ ማንቂያ

ለጤና መጠበቂያ … እያለ የስፖርትን ጥቅሞች ይዘረዝርና እናት ኢትዮጵያን

እንደ አበበ ቢቂላ የስፖርት ሞያዋን

ባለም ላይ አስታውቃት

አንተም ተወዳደር

አሸንፍ ወጣቱ የሌሎችን ሀገር

ሲጋራ ከማጨስ ከመጣጣት አልኮል

ሀሺሽ ጫት ከመቃም ስፖርት ይሻልሀል:: ሲልም ይመክራል::

ተስፋዬ ገብሬ ለትግል እና ለድል ጭምር አስፈላጊ ነው ያለውን የስፖርትን ፋይዳ የሙያው ጠበብትም ይጋሩታል::

ጠበብቱ የስፖርት ጥቅሞች የሚሏቸው ነጥቦች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በባህልና ትውፊት፣ በጤና፣ በአካል ብቃት፣ በተዝናኖት እና በፖለቲካ ዘርፍ ጭምር የሚገኙ እና በቁጥር በርካታ ናቸው::

በዚህም ምክንያት ሁሉንም ጥቅሞች መዘርዘር ያዳግታልና ለዛሬ ስፖርት ከጤና አኳያ ብቻ የሚያበረክታቸውን ጥቅሞች እናያለን፤ ብዙ አይነት ጥቅሞች አሉት ይሉናል የዘርፉ ባለሙያዎች፡-

ጡንቻ እና አጥንትን ያጠነክራል፡-

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አጥንት እንዲወፍር /እንዲዳብር ያደርጋል፤ አጥንት እንዲሳሳ፣ ደካማ እና ተሰባሪ እንዲሆን የሚያደርገው አስቲዮፖሮሲስ የተሰኘ በሽታ እንዳይመጣ ያደረጋል:: ጡንቻዎቻችን ጠንካራ እና ተጣጣፊ እንደሆኑ፣ የሰው ነታችን መገጣጠሚያዎችም ጤናማ እንደሆኑ ያደርጋል::

ረዥም እድሜን ያጐናፅፋል፡- የአካል ብቃት እንቅስቃሴአችን የልብ እና የደም ቧንቧ ጤናን በማሸሻል ልብን ያጠነክራል፤ በዚህም ሳቢያ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የስኳር በሽታ፤ የደም ግፊት እና የከፍተኛ ኮሌስትሮል ህመሞችን ይቀንሳል፤ የህዋስ እርጅናን  ሂደት ይቀንሳል፣ በሰውነት ውስጥ ያለውን የኦክስጂን መጠን በመጨመር ረዥም እድሜ እንድንኖር ያግዛል::

የተሻለ ትኩረት እና የማስታወስ ችሎታ እንዲኖረን ያደርጋል፡-

በአንጐል ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የነርብ ሌሎች አሉ፤ ስፖርት ስንሰራ አእምሮአችንን የሚቆጣጠሩትን ዶፖሚን፣ ሴሮቶኒን እና ኢንዶርፊን የተሰኙትን ንጥረ ነገሮች እናበረታተለን:: ማንቸውም ስፖርት ትኩረትን፣ ትውስታን እና የአእምሮ ደህንነት ስሜትን ያሳድጋል፤ የእውቀት ችሎታንም ያሻሽላል:: ወደ አንጐል የኦክስጅን ፍሰት መጨመር የአንጎል ሴሎችን ስለሚያንቀሳቅስ እንደ ፓርኪንሰን ወይም አልዛይመርስ የመሳሰሉ የመርሳት በሽታዎች እንዳይከሰቱ ያደርጋል::

ያለጭንቀት ያስኖራል፡- በቀን 30 ደቂቃ ብቻ እንኳ ብትሰራ በቂ ነው፤ ያኔ ስጋትህ፣ ጭንቀትህ፤ ግዴለሽነትህ እና የንዴትህ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል፤ ድብርትን ያስወግዱልህና በነፃ ስሜት አእምሮህን ትቆጣጠራለህ፤ ጥሩ ስማት ሲሰማህ ለራስህ ያለህ ግምት ይሻሻላለ፤ ማህበራዊ ግንኙነትህ ይሻሻልና መገለልንህም ይቆማል::

የተሻለ እንቅልፍ ያስተኛል፡- በስፖርቱ ሰውነትህ ሲደክም የእንቅልፍ ጥራት ይሻሻላል፤ ጥሩ እንቅልፍ የሚያስገኙ ሆርሞኖችን በማምጣትም አእምሮህን በማዝናናት ለሽ! እንድትል ያደርግሀል – ስፖርት

መከላከያዎን ያጠናክራል፡- እንቅስቃሴህ መጠነኛም ቢሆን እንኳ በሽታ የመከላከል ስርዓትን ለማጠንከር ይረዳል::

ይህ ለየትኛውም ዓይነት ህመም በተለይም በወጣቶች እና አረጋዊያን ላይ የበለጠ የመቋቋም እድል ይፍጥራለ::

አተነፋፈስን በመጨመር በመተንፈሻ  አካላት ውስጥ ያሉ ባክቴሪያዎች ይወገዳሉ፤ ይህም በpulmonary infections የመያዝ እድልን ይቀንሳል:: ልክ እንደዚሁ በሽታን የመከላከል አቅምን ያካተቱት ፀረ እንግዳ አካላት እና ነጭ የደም ሴሎች በስፖርት ወቅት ለበለጠ ፍጥነት ስለሚጓዙ በፍጥነት እና በትክክል በሽታዎችን እንዲያውቁ ያስችላል::

 

ክብደትን መቆጣጠር ያስችላል፡- የኤሮቢክስ ልምምዶች ጤናማ ክብደትን ለማግኘት ወይም ለማቆየት ይረዳል:: ከመጠን በላይ ውፍረትን ለመከላከል ስፖርትን ከተገቢው አመጋገብ ጋር ማዋል ያስፈልጋል:: ጤናማ ክብደት ካለህ ለራስህ ያለህ ግምት እየጨመረ ይሄዳል፤ ይህም የእለት ተእለት ችግሮችን እንድትቋቋም ዋስትና ይሰጥሃል::

እንዚህን ለአብነት ያህል አነሳን እንጂ ስፖርት ከጤና አንፃር ብቻ እንኳ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ጤናማና ጥሩ ቆዳ እንዲኖረን፣ ስር የሰደዱ በሽታዎችን ለማከም እና አሁን አሁን ልጆችን እያጠቃ የሚገኘውን ቅጥ ያጣ ውፍረት ለማስቀረት እጅግ አስፈላጊ ነው- ስፖርት::

በአጠቃላይ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የተመጣጠነ አመጋገብን እና የእለት ተእለት ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ያጣመረ ነው:: የተሻለ ህይወት እና ኑሮ ከፈለጉ ታዲያ ከዚያ የማይንቀሳቀስ ልማዳዊ  የአኗኗር ዘይቤ ወጥተው ህይወትወን በእንቅስቃሴ ይሙሉ፤ ከሶፋዎም ይወረዱ! ይለናል የመረጃ ምንጫችን፡- https://gullon.co. uk /blog/sport ድረ – ገፅ

https: //www.britannica.com /sports/ም ሌላው ምንጫችን ነው።

 

(ጌታቸው ፈንቴ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here