ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ኬኒያ በማሳይ ግዛት ካቲንጋላ ቀበሌ የተወለደው ሪቻርድ ቱረሬ አሁን ላይ 22 ዓመት ሞልቶታል:: ሪቻርድ ተወልዶ ባደገባት አካባቢ ልምድ መሠረት ዘጠኝ ዓመት ሲሆነው ነው የቤት እንስሳቱን የመንከባከብ እና ከአስፈሪዎቹ የዱር እንስሳት የመጠበቅ ኃላፊነት የወደቀበት::
የኬኒያ ደቡባዊ ብሔራዊ ፓርክ ክፍል የሆነው የነሪቻርድ መኖሪያ አካባቢ አንበሳ፣ ነብር፣ አቦሸማኔ እና ሌሎች ትልልቅ የዱር እንስሳት የሚንቀሳቀሱበት ነው::
በአፍሪካ ካሉ ግጭቶች ውስጥ ትልቁን ስፍራ የሚይዘው በሰዎች እና በዱር እንስሳት መካከል ያለው እንደሆነ ሪቻርድ ያምናል:: በአካባቢው እያደገ የመጣው የሰው ልጆቸ ቁጥር እና የቤት እንስሳት የማርባት ልምድ ነዋሪዎች የዱር እንስሳትን መኖሪያ በመጋፋት ያለውን ውጥረት አባብሶታል ይላል:: ይህን ተከትሎም ማሳይ አካባቢ በግዙፍ የዱር እንስሳት መኖሪያነት ቢታወቅም በዙሪያው የሚገኙ ነዋሪዎች የቤት እንስሳት ቁጥራቸው ከፍ እያለ መምጣቱ ደግሞ ለዱር እንስሳቱ መመናመን ትልቅ አደጋ ደቅኗል::
ዛሬ ላይ 22 ዓመት የሞላው ሪቻርድ በታዳጊነቱ በአካባቢው የቤት እንስሳቱን ሲጠብቅ የነበረውን ችግር ሲያስታውስ፤ “የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለሁ ከብቶችን እንድጠብቅ ኃላፊነት ተሰጠኝ:: አካባቢው ከናይሮቢ ብሔራዊ ፓርክ አጠገብ በመገኘቱ እንስሳቱ በዱር አራዊቱ እንዳይበሉ ከፍተኛ ጥበቃ አደርግ ነበር” በማለት ነው::
በአካባቢው እሱም ሆነ ሌላው ማህበረሰብ ከልጅነታቸው ጀምረው ተንከባክበው ያሳደጓቸው ከብቶች በምሽት በአንበሶቹ ታድነው ሲበሉ መመልከት ከፍተኛ ሀዘን የሚፈጥር ክስተት እንደነበርም ይገልፃል::
የያኔው ሪቻርድ የሁኔታው አሳሳቢነት በሰዎች እና በዱር እንስሳቱ መካከል ያለውን ችግር ሊፈታ የሚችል መፍትሔ እንዲያስብ አደረገው:: በየጊዜው እሳት በማንደድ እና ሰው የሚመስሉ ምስሎችን በማቆም የዱር አራዊቱ እንዳይጠጉ ለማድረግ ቢሞክሩም የቤት እንስሳቱን ማትረፍ አልቻለም::
አንድ ሌሊት ግን የእጅ ባትሪ መብራት ይዞ ዙሪያውን ለመመልከት ሲሞክር የባትሪውን መብራት ፍራቻ አንበሶቹ ሲሸሹ ተመለከተ:: ይሄኔ ነበር ሪቻርድ እንስሳቱን ለመታደግ ያስበው ለነበረው ሕልሙ መነሻ የሚሆን ሀሳብ ያገኘው::
ከአሮጌ ሬዲዮ እና የወደቀ የመኪና ባትሪ በመጠቀም የሠራው መብራት አንበሶች ወደ አካባቢው የቤት እንስሳ እንዳይቀርቡ በማድረግ ከብቶችን መጠበቅ አስቻለው ሙከራውም ተሳካ::
የ12 ዓመት ታዳጊ በነበረበት ወቅት ያገኘው የ“ላይዎን ላይት ቴክኖሎጂ“ ከእሱ እና ቤተሰቦቹ ውጭ ላሉ የማሳይ ማህበረሰብ የእንስሳት ጥበቃ ለማዋል መንቀሳቀስ ጀመረ::
የአካባቢው ማህበረሰብ የቤት እንስሳቱን ሲበሉበት ከተመለከተ አንበሶቹን ይገድላቸው ነበር:: በዚህም ጥፋቱ በሁለቱም መካከል ይሆናል:: የማሳይ ማህበረሰብ በየዓመቱ ቢያንስ 100 አንበሶችን በዚህ ግጭት ምክንያት ያጣል:: በሰዎች እና በዱር እንስሳቱ መካከል ያለውን ግጭት ማስቆም ካልተቻለ ደግሞ አንበሶች ከአፍሪካ ምድር ሊጠፉ ይችላሉ በሚል ጭምር ነበር ሪቻርድ ከታዳነቱ ጀምሮ ያስብ የነበረው::
ዛሬ ላይ የዱር እንስሳቱን መጠበቅ ተችሏል:: እ.ኤ.አ በ2013 ሪቻርድ ቱረሬ ላይዎን ላይት ፋውንዴሽን በመመስረት የባትሪ መብራት የመሰሉ በፀሐይ ኀይል የሚሠሩ መብራቶችን በማምረት የቤት እንስሳት ባሉባቸው አካባቢ ማብራት ጀመረ:: ይሄ ሂደት አንበሶችንም ሆነ የቤት እንስሳቱን መታደግ የሚቻልበት ውጤታማ መንገድ ሆነ::
ሪቻርድ እንደሚለው ሥራውን ወደ ተግባር የመቀየር ሂደቱ ቀላል እንዳልነበር ያነሳል:: በተለይ የአካባቢው እንስሳት አርቢዎች ቴክኖሎጂው ውጤታማ ይሆናል ብለው ለመቀበል ጊዜ የፈጀ እንደነበር ይናገራል:: ለቴክኖሎጂ ቅርብ ያልሆኑት አርሶ አደሮች ተጠራጣሪ መሆን ቢከብድም ከ10 ዓመት ድካም በኋላ ቴክኖሎጂው ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል::
በራስ የመተማመን እና ፈጠራን ሌላው ቀድቶ እንዳይሠራ በጥንቃቄ መሥራት ይጠይቃል የሚል እምነት ያለው ሪቻርድ እንስሳቱን ከዱር አራዊት ለመታደግ ባበረከተው የፈጠራ ውጤት በ2023 እ.ኤ.አ የዓለማችን ወጣት ፈጠራ ሽልማት በእውሮፓ ለማግኘተ በቅቷል::
የሪቻርድ የፈጠራ ሥራ በአራት ዓመት ውስጥ በአካባቢው ያሉ የ750 አርሶ አደሮችን እንስሳት ከሞት መታደግ እና መብራቱን ለሚተክሉ 50 የአካባቢው ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏል:: የወጣቱ የፈጠራ ውጤት ከአካባቢው በተጨማሪ በመላው ኬንያ ከ2ሺህ 300 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርጓል::
ዛሬ ላይ ከኬንያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘው ቴክኖሎጂው ቦትስዎና፣ ናሚቢያ፣ ታንዛኒያ እና ዚምባብዌን ተጠቃሚ አድርጓል:: ላይዎን ላይት አርጀንቲና እና ህንድ ጅብ ፣ ጥቁር አንበሳ እና ሌሎች የዱር እንስሳትን ወደ መኖሪያ አካባቢ እንዳይገቡ ተከላክሏል::
ባህል እና አካባቢን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባ የሚያምነው ሪቻርድ አሳሳቢውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ብዙ ሊሠራ እንደሚገባም ጽኑ እምነት አለው:: ማህበረሰቡንም በትምህርት መቀየር የሚቻል በመሆኑ ትምህርት ላይም በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ የቢዝነስ ደይሊ አፍሪካ ዊፖ መጋዚን ዘገባ ያመለክታል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም