ሌላኛዉ መስፈንጠሪያ

0
10

ክረምት ከበጋ በስንፍና ማሳውን በአግባቡ ሳያርስ፣ ሳያለሰልስ፣ ሳይዘራ…በቂ ምርት ያላገኘ አርሶ አደርን በሚያውቁት ሰዎች በሥነ ቃል፦

በበጋ እንዳይሠራ ፀሐይ እየፈራ፣

በክረምት እንዳያርስ ዝናብ እየፈራ፣

ልጁ “እንጀራ?” ሲለው በጅብ አስፈራራ። እየተባለ   ሸንቆጥ ይደረጋል፡፡

በትጋት ዝናብ፣ ብርድ፣ ፀሐይ… ሳይፈራ በሰፊው ያመረተ አርሶ አደርን ደግሞ ፦

ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፣

ወፍጮው እንዳገሳ መስከረም ዘለቀ፡፡  በማለት ያሞግሱታል፡፡

እኛም ከሰሞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚኖሩ አርሶ አደሮች ጋር በስልክ የመኸሩን ምርት ውጤት እና የበጋውን  ልማት አጀማመር  በምን ሁኔታ እያከናወኑ   እንደሆነ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ በስልክ ሐሳባቸውን ካጋሩን አርሶ አደሮች መካከል አቶ ፈጠነ ብርሐን አንዱ ናቸው። አርሶ አደሩ   በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ አለላ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢያቸው የሚገኘውን ወንዝ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር  በመጥለፍ በበጋ መስኖ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን እያለሙ ይገኛሉ። በተለይም የክረምቱን ዝናብ ብቻ ሳይጠብቁ በመስኖ ልማቱ  በመሳተፋቸው ተጠቃሚ እንደሆኑ ነግረውናል።

አርሶ አደሩ በ2017 በመስኖ ያለሙትን ሽንኩርት፣ ስንዴ፣ ድንች እና ቲማቲም በመሸጥ የግብርና ሥራቸውን የሚያቃልሉላቸውን    አስፈላጊ ዕቃዎችን እና በሬዎችን እንዳሟሉ ተናግረዋል።  ከዚህ በተጨማሪም ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እና ልጆቻቸውን ለማስተማር የሚያስችል ከፍተኛ ጥቅም እንዳገኙበትም ገልፀዋል።

አርሶ አደሩ ዘንድሮ በበጋ መስኖ እያለሙት ያለው  ስንዴ፣  ቀይ ሽንኩር፣ ቲማቲም እና ቃሪያ ከጅምሩ በጥሩ ቁመና ላይ በመሆኑ ልፋታቸውን እና ወጫቸውን የሚክስ  ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ ሰንቀዋል። በአሁኑ ወቅት 60 ኩንታል ቀይ ሽንኩርት አምርተው ለገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል። በቀጣይም በአራት ሄክታር መሬት ላይ በሚያለሙት ስንዴም ከ80 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሠሩ ነው።

ሌላው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደምቢያ ዳህና ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ሙሉጌታ ሰጤ ለበኵር በስልክ እንደተናገሩት በመስኖ ልማት ከተሰማሩ ጀምሮ ገቢያቸው በማደጉ ኑሯቸው ተሻሽሏል። በ2017/18 የመኸር ወቅት ሩዝ፣ ዳጉሳ፣ ስንዴ እና ጤፍ ዘርተው  በጥሩ ቁመና ላይ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህ ወቅትም ለመስኖ ስንዴ ግማሽ ሄክታር (ሁለት ጥማድ) መሬታውን አርሰው አዘጋጅተዋል። ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን ደግሞ በነጭ ሽንኩርት እንዲሁም ሩብ ሄክታሩን (አንድ ገመድ) በቀይ ሽንኩርት ሸፍነዋል።

እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች ከክረምት ዝናብ ጥገኝነት በመውጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ መስኖ የማልማት ልምዳቸው እየተሻሻለ መምጣቱንም መታዘባቸውን አጋርተውናል። ዘመናዊ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ተጠቅሞ ማልማት አስፈላጊ በመሆኑ መንግሥት በወቅቱ እንዲያቀርብላቸውም  ጠይቀዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ በ2018 ዓ.ም የበጋ ወቅት  51 ሺህ 762 ሄክታር መሬት በነባር እና በአዲስ በተለያዩ ሰብሎች በመስኖ ለማልማት ማቀዱን አስታውቋል። በምርት ዘመኑ በመስኖ ከሚለማው ሰብል ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በመኸር ተዘርተው ምርቱ በተሰበሰበባቸው ቆላማ አካባቢዎች ፈጥነው ወደ  መስኖ ልማት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ የመስኖ አግሮኖሚስት ባለሙያ አቶ አበበ ፈንታሁን ለበኩር ተናግረዋል። በተያዘው ዓመት ተጨማሪ ማሳ በአዲስ ለማልማት ትኩረት እንደተሰጠው የተናገሩት ባለሙያው፤ በዚህም 14 ሺህ 717 ሄክታር መሬት ይለማል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በበጋው በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ 34 ሺህ ሄክታሩ በስንዴ የሚሸፈን እንደሆነም ተመላክቷል። ባለሙያው በስልክ እንደተናገሩት እስካሁንም 22 ሺህ  684 ሄክታር ማሳ በስንዴ ዘር ተሸፍኗል። በአጠቃላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 51 ሺህ 762 ሄክታር ውስጥ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ 33 ሺህ 643 ሄክታሩ  በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን የማሟላት ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 113 ወንዞችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሠራ ነው። 103 ሺህ 523 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ (ዳፕ እና ዩሪያ) ለማቅረብ ታቅዶ  እስካሁን 39 ሺህ 476 ኩንታል ጥቅም ላይ ውሏል። በበጀት ዓመቱ አንድ ሺህ 266 ሞተር ፓምፕ ለማቅረብ የታቀደ ሲሆን ሦስት ሺህ 356 ነባር ሞተር ፓምፕ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

ባለሙያው እንዳሉት የመስኖ ልማት ዕቅዱን ለማሳካት የእርሻ ሥራ እና የቦይ ጠረጋን ጨምሮ ሰፊ ዝግጅትም ተከናውኗል። ለመስኖ ልማቱ በቂ ግብዓት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። የታቀደው ምርት እንዲገኝ በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ክትትል እና ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ሌላው በበጋ መስኖ ስንዴ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ለበኵር ያስታወቀው  የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ነው። በመምሪያው  የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ሐውልቱ ታደሰ እንደተናገሩት በበጋ መስኖ  33 ሺህ 585 ሄክታር መሬት በነባር እና 16 ሺህ 203 ሄክታር መሬት በአዲስ በማልማት አራት ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት ታቅዷል። በአዲስ እና በነባር ከሚለማው መሬት 28 ሺህ ሄክታር ስንዴ በማልማት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። እስካሁንም 19 ሺህ 330 ሄክታር መሬት ታርሶ 13 ሺህ 233 በዘር ተሸፍኗል። እስከ ታኅሳስ 30 ድረስ የዘር ሥራውን ለማጠናቀቅ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው።

በዞኑ ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ ወንዞችም ተለይተዋል። 92 የተገነቡ የመስኖ ቦይ (ካናል) ማፅዳት ሥራ ተከናውኗል። የባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍም ስምሪት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለልማቱ ስኬታማነትም ስድስት ሺህ 63 ነባር ሞተር ፓምፕ መኖሩን እና በዚህ ዓመትም 210 ሞተር ፖምፕ በአዲስ መሠራጨቱን ገልፀዋል። አርሶ አደሩም የበጋ መስኖ ስንዴ ጥቅሙን በመረዳት ግንዛቤው እያደገ ነው ብለዋል።

ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ ቀድመው ለሚዘሩ 30 ሺህ ኩንታል ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል። የአካባቢ ዝርያን ጨምሮ ምርጥ ዘርም እየተሠራጨ ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2018 ዓ.ም በበጋ መስኖ ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል። በክልሉ በመስኖ የሚለማ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ምቹ መሬት ቢኖርም እስካሁን ማልማት የተቻለው ግን ከ300 ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥ ነው የቢሮው መረጃ የሚያመላክተው።

የቢሮው የመስኖ ውኃ አጠቃቀም አግሮኖሚ ባለሙያ አቶ ንጋቴ አለማየሁ ለበኵር እንዳስታወቁት በዚህ ዓመት 502 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ነው። ከዚህም 55 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን አክለዋል፡፡ ክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ 350 ሺህ ሄክታር መሬት  በማልማት 13 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት። ለምርታማነቱ 900 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ባለሙያው  ገልፀዋል፡፡ እስካሁን 247 ሺህ 943 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 221 ሺህ 148 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል።  60 ሺህ ሞተር ፓምፕ ሥራ ላይ ያለ ሲሆን ተጨማሪ አንድ ሺህ ተገዝቶ እየተሠራጨ ነው። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት (ታኅሳስ 01 ቀን 2018 ዓ.ም) 247 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም ነው ባለሙያው የተናገሩት።

በበጋ መስኖ ስንዴ አማካይ ምርታማነትን በሄክታር 40 ኩንታል ለማሳደግ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር መግባባት ተፈጥሮ ወደ ሥራ ተገብቷል። የታቀደውን  ምርት ለማሳካት  አጋርና ባለድርሻ አካላት በቅንጀት እና በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው የውኃ አጠቃቀም ባለሙያው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አርሶ አደሩም ያለውን የውኃ አማራጭ ተጠቅሞ የእርጥበት ጊዜው ሳያልፍ እና የውኃ መጠኑ ሳይቀንስ ማሳውን ፈጥኖ በዘር መሸፈን እንዳለበት ባለሙያው አሳስበዋል። የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና የተበጠረ የአካባቢ ዘር እየቀረበ መሆኑም ተገልጿል። ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በተለይ መስኖ ላይ ሁሉም ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የግብርና ሚኒሥቴር መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ ወቅቱ የ2018 የበጋ መስኖ ልማት ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር የሚገባበት ነው፤ በኢትዮጵያ ከአራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዷል። ከዚህም ከ175 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ዜና

በመኸር ከተሸፈነው ሰብል ከግማሽ የሚበልጠው ተሰብስቧል

 

በደቡብ ወሎ ዞን በ2017/18 የምርት ዘመን 435 ሺህ 638 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። ከዚህም 15 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡

በዞኑ ምርታማነቱን ለማሳደግ 528 ሺህ ኩንታል ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ፣ 10 ነጥብ ሁለት  ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) እና 18 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል። ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ምርት ማግኘት የሚያስችል የቅድመ እና የተግባር ሥራዎች ተከናውነዋል።

የዞኑ  ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለበኵር በስልክ እንደተናገሩት በዞኑ 435 ሺህ 638 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል፤ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ታኅሳስ 01 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በ226 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ የነበረው ተሰብስቧል። ቀሪ የደረሱ ሰብሎች ብክነት እንዳያጋጥማቸው አርሶ አደሮች በደቦ   እንዲሰበስቡ ባለሙያው አሳስበዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የታህሣስ  6  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here