ኢትዮጵያ የዜጎቿን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማሳካት፣ የግብርና መር ኢንዱስትሪውን ምርታማነት በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምጣኔ ሐብት ለመገንባት እና ግብርናዉ የሚፈጥረውን የሥራ ዕድል ለመጨመር ከተለመደው የመኸር እርሻ በተጨማሪ መስኖ ልማት ላይ በስፋት እየሠራች ትገኛለች፡፡ የሜካናይዜሽን ጅምሮችን ማስፋት፣ የኩታ ገጠም አስተራረስን መተግበር፣ ምርጥ ዘርን በመጠን እና በጥራት ማሳደግ፣ የአፈር ማዳበሪያ ዓይነቶችን በበቂ መጠን ማሰራጨት እና የአርሶ አደሩን የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ማሻሻል ላይ በትኩረት መሥራት ለዘርፉ ውጤታማነት ዋና ጉዳይ ሆኖ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ከመኸር እርሻ በተጨማሪ መስኖ ላይ እያከናወነች ያለው ሥራ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡ ለማሳያም እንደ ሀገር በ2016/17 የምርት ዘመን 20 ሚሊዮን ኩንታል ግዢ ሲፈጸም አጠቃላይ ወጪው 930 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በ2017/18 የምርት ዘመን የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ፍጆታም ቀድሞ ከነበረው የምርት ዓመት አንጻር ሲታይ በአምስት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ ለ2017/18 የምርት ዘመን ለማቅረብ የታቀደውን የ25 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ወጪን ጠይቋል፡፡ በዚህ ዋጋ የተገዛው የአፈር ለምነት ማስጠበቂያ ግብዓት ቀጥታ ወደ አርሶ አደሩ ቢወርድ የአንድ ኩንታል ዋጋ እስከ 12 ሺህ ብር ይደርሳል፡፡ ይሁን እንጂ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር በአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ አሉታዊ ጫና እንዳይፈጥር መንግሥት ከግምት ውስጥ በማስገባት በአንድ ኩንታል የሦስት ሺህ 700 ብር ድጎማ አድርጓል፡፡ በዓመቱ ግዢ ለተፈጸመው በመንግሥት በኩል የተደረገው አጠቃላይ ድጎማም 84 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የግብርና ሚኒሥቴር መረጃ ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሚያስፈልጋትን ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያን ከውጭ ሀገር ስታስገባ እና ዓለማቀፋዊ ጫናው የፈጠረው የዋጋ ውድነት የአርሶ አደሩን የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም እንዳይቀንሰው በመንግሥት የተደረገውን ድጎማ ጨምሮ በጥቅሉ ከሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጋለች ማለት ነው።
የአማራ ክልልን የአፈር ማዳበሪያ ፍጆታ እንኳ ብንመለከት ከዓመት ዓመት ጭማሪ እየታየበት ይገኛል፡፡ በክልሉ በ2016/17 የምርት ዘመን ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያን መጠቀም መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው አስታውቀዋል፡፡ ዘንድሮም ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ ያለው ነው፡፡
የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ ምርታማነት በሄክትር አራት ኩንታል ጨምሯል፡፡ በተጠናቀቀው የምርት ዘመን የተገኘው የምርት መጠንም 160 ሚሊዮን ኩንታል ነው፡፡ አሁንም የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀምን ከሌሎች የግብርና ምርት ማሳደጊያ አሠራሮች ጋር በማጣመር ምርታማነትን በሄክታር 34 ኩንታል ለማድረስ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡ የ2017 የምርት ዘመን ተጠባቂ ምርትም 187 ሚሊዮን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ27 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ እንዲኖረው ታሳቢ ተደርጓል፡፡
መንግሥት ምንም እንኳ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የአፈር ማዳበሪያን እየገዛ ለማስገባት ጥረት እያደረገ ቢሆንም የዋጋ ውድነት እና መዘግየት በአርሶ አደሮች በኩል በችግርነት ይነሳል፡፡ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ አምሳሉ አያሌው ይህንን ችግር ያረጋግጣሉ፡፡ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ መጨመሩን ያነሳሉ፡፡ የጸጥታ ችግር በሚስተዋልበት እንደ አሁኑ ዓይነት ወቅት የተመረተውን ምርት ወደ ገበያ አውጥቶ በተሻለ ዋጋ መሸጥ ባለተቻለበት ነባራዊ ሁኔታ የዋጋው ጉዳይ ፈታኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡ “አመራሮች ‘የዋጋ ጭማሪው የታየው በእኛ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በዓለም ነው’ ይሉናል፤ እኛ እንደ በፊቱ የፈለግነውን ያክል ማዳበሪያ ገዝተን ለመጠቀም አቅም የለንም፤ የቻልነውን ገዝተናል፤ ምርታችን እንዳይቀንስ የተፈጥሮ ማዳበሪያ /ኮምፖስት/ እየተጠቀምን ነው” ብለዋል፡፡
የአርሶ አደሩን የየዓመት የራስ ምታት ለማስታገስ፣ ምርታማነትን በሚፈለገው ልክ በማረጋገጥ የምግብ ዋስትናን እና የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ለማሳካት ተስፋን የፈነጠቀ “የአፈር ማዳበሪያ ኢትዮጵያ ልትገነባ ነው” የሚል ብሥራት ከሰሞኑ ተሰምቷል፡፡ የአርሶ አደሩን ጥያቄ ይፈታል፣ ኢትዮጵያንም ከውጭ ምንዛሪ ያድናል ተብሎ ከናይጀሪያው ባለሐብት አሊኮ ዳንጎቴ ጋር በሶማሌ ክልል ይገነባል የተባለውን የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት መገንባትን ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግሥትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
የምክር ቤት አባላትም ፋብሪካው የኢትዮጵያ ሌላኛው ሕዳሴ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ካደረጉት የምክር ቤት አባላት መካከል ከፈና ኢፋ (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡ ኢትዮጵያ በሚዋዥቅ ኢኮኖሚ ውስጥ ትገኛለች ያሉት አባሉ፤ በመንግሥት በኩል በየዓመቱ የሚደረገው ድጎማ ግን የግብርናውን ከፍለ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እያሳየ ያለው እመርታ መልካም ነው ብለዋል፡፡ ይህ በራስ የማዳበሪያ ፋብሪካ የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያን ተደራሽ ማድረግ ሲጀመር ዘርፉ ምን ያህል ይነቃቃል? የሚለው የሚያነጋግር እንደማይሆን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ተባብሮ በቀላሉ ሊገነባው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ማዳበሪያን ከውጭ በምታስገባበት ወቅት ለከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ መዳረጓን ያነሱት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ዓለሙ ጎንፋ ናቸው፡፡ አሁን የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት የተያዘው ውጥን ሀገሪቱን በብዙ መንገድ አትራፊ እንደሚያደርጋትም ያምናሉ፡፡
በየዓመቱ እየጨመረ ከሚሄደው የውጭ ምንዛሪ ነጻ ያደርጋታል የሚለውን ቀዳሚው የፕሮጀክቱ ፋይዳ ነው፡፡ ለግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሌላ ልማት ማዋል ይቻላል፡፡ ግብዓቱን በወቅቱ አምርቶ ለሚፈለገው አርሶ አደር በሚፈለገው ጊዜ እና ቦታ ለማድረስም የፋብሪካው መገንባት ዘርፈ ብዙ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡ ይህም የሀገራችንን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋታል የሚል እምነት እንዳላቸው የምክር ቤት አባሉ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ምጣኔ ሐብታዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሚሆን ታምኖበት ይገነባል የተባለውን ፋብሪካ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ መንግሥት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“የዓለም አቀፍ ዋጋ እየጨመረ ነው፤ የአፈር ማዳበሪያን በቋሚነት ከውጪ እያስገቡ ምርታማነትን ማረጋገጥ አይቻልም” ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል ኑርአዝማል ጅብሪል (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ፣ ከምርት ውጪ የነበረ መሬትም ወደ ምርት እየገባ ባለበት በዚህ ወቅት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የተያዘው ውጥን የብዙኃኑ የሕልውና ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም ምርታማነትን በሚፈለገው ልክ በማሳደግ ሀገራዊ አበርክቶውን ከፍ ለማድረግ ማዳበሪያን ከውጭ ከማስገባት ወደ ማምረት መሸጋገር ይገባል የተባለውን ሐሳብ በቀናነት መደገፍ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያን ማቀነባበር የሚያስችሉ እንደ ፎስፌት፣ ፖታሽ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማዕድናት በበቂ መጠን እንዳላት የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የቀደሙ ዓመታት ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋት መሆኑን ያረጋገጡት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ “በአንድ ቀን 150 ሺህ ኩንታል ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ይጓጓዛል፡፡ ግዢው የሚፈፀመው ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ነው፤ ድጎማ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ ወደብ ስለሌላት ከወደብ ማጓጓዙ ፈተና ነው፤ ይሄ ሁሉ ወጪ ነው!” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ አንዱ መፍትሔ አድርጎ ለመሥራት ከፍተኛ ዕቅድ እንደነበረው ጠቅላይ ሚኒሥትሩ አስታውሰዋል፡፡ አሁን ወደ ተግባር የሚገባበት ወቅት መሆኑንም በብሥራት አንስተዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ሌላኛው ሕዳሴ” ሲሉ የጠሩትን ግዙፍ ፕሮጀክት ገንብቶ ለማጠናቀቅ እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡ በ40 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለውን ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ ከናይጀሪያው ባለሐብት አሊኮ ዳንጎቴ ጋር ንግግር ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በግል ተቋማት እና በኢንቨስትመንት መሳካት ካልቻለ መንግሥት የሚያሳካው ትልቁ ፕሮጀክት እንደሚሆንም ጠቅላይ ሚኒሥትሩ አረጋግጠዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም