ሌላው የተማሪ ፈተና በአማራ ክልል

0
128

ድሮ ድሮ አከሌ “በአየር ሄደ” ሲባል አግራሞትን ይጭር ነበር። ኧረ ከዚያም አልፎ የኑሮ ደረጃን መለኪያም ጭምር ነበር። “ችግር በቅቤ ያስበላል” እንዲሉ በአየር መሄድ አሁን አሁን የአማራጭ እጦት ያመጣው አማራጭ ሆኗል። በክልሉ የቀጠለው ቀውስ የመጓጓዣ ፍሰቱን ለደኅንነት አስጊ እና አዳጋች አድርጎታል፡፡ ዜጎች ለከፍተኛ እንግልት፣ ዝርፍያ፣ እገታ እና ግድያ በመዳረጋቸው  ወደ ክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ ለሚደረጉ ጉዞዎች  የሰማዩን ባቡር መጠቀም እየተዘወተረ መጥቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች እና እካባቢዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉት እና አዲስ የተመደቡ ተማሪዎች የገፈቱ ቀማሽ ከሆኑት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። አዎ! ቀደም ባሉት ጊዜዎች “ድሮ በኛ ጊዜ “ እየተባለ ሲተረት ብዙ ዓመታት ወይም የአንድ ጎረምሳን የእድሜ ርዝመት የሚስተካከል የጊዜ ቆይታን በትውስታ ወደ ኋላ በመመለስ ትናንትን ከዛሬ ማነፃፀር የተለመደ ነበር። አሁን ላይ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ንፅፅሩ ወደ ወራት  እና ቀናት ተለውጧል።

ለምሳሌ እንድ ተማሪ ሁለተኛ ዓመት እያለ ከባህር ዳር አዲስ አበባ 550 ብር በአውቶቡስ ከፍሎ ይሄድ የነበረ ሲሆን ከወራት በኋላ ወደ ግቢ ሲመለስ ከባህር ዳር አዲስ አበባ በአውሮኘላን ለመሄድ ይከፍለው የነበረው ብር  ካረፈበት ሆቴል እስከ “አውሮፕላን ማረፊያ”ጃ በታክሲ  ለመጓዝ ብቻ እየዋለ ይገኛል።

የጉዞ ተመን፣የቁሳስ  እንዲሁም የአልባሳት ዋጋ ወዘተ.  በወራት አንዳንዴም በቀናት ሲጨምር ማየት የተለመደ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል  በቀጠለው ጦርነት ምክንያት የተፈጠረው የመንገድ ደህንነት ስጋት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች መጨመር ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህን ተከትሎም አየር መንገዱ የተሻለ ገቢ ማግኜቱ አያጠራጥርም።

ሀገራችን ከምትኮራባቸው ጥቂት ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞቹ ቢጨምሩለትም ሆነ ገቢው ቢያድግ የሚቃወም የለም፡፡ ሆኖም ተማሪዎችን ጨምሮ ብዙው  ሰው በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመረጠው የደኅንነት ስጋት ስላለበት እንጂ ገንዘብ ስለተረፈው አይደለም፡፡ በዚህ ሀገር በበርካታ ችግሮች ፍዳዋን እያየች ባለችበት ወቅት፤ የጭንቅ ቀን ደራሽ መሆኑ ቀርቶ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ አቅም ያላማከለ እና ነባራዊውን የክልሉን ሁኔታ  ከግምት ውስጥ ያላስገባ ክፍያ ማስከፈሉ ግን ትዝብትን የሚያጭር ነው።

ዓለም” በኮረና ወረርሽኝ “ለዜጎቿ ሳይቀር በሯን ዘግታ በቆየችበት  ወቅት፣ በተለይ በአፍሪካ ሀገሮች መድኃኒት እንኳን እንደልብ ማድረስ አዳጋች በሆነበት በዛ የጭንቅ ቀን፣  አየር መንገዱ ደጀን በመሆን ስሙን በበጎ ያስጠራ ተግባር እንደፈፀመ ሁሉ፣  በዚህ አስቸጋሪ ወቅትም ለዜጎቹ ይህንኑ መፈጸም በተገባው ነበር።

ክፉ ቀንን እና መከራን ተደጋግፎ ማለፍ  በሀገራችን ብቻ ሳይሆን ዘምነዋል በተባሉት እና የፈረጠመ ኢኮኖሚ ባላቸው አገራት ሳይቀር የተለመደ ተግባር ነው። የምንኮራበት  የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለዚህ አርአያ መሆን በተገባው ነበር፡፡ር

በተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ እና ከዩኒቨርሲቲ መውጫ ውቅቶች  ቢያንስ ቅናሽ ባያደርግ እንኳን  የታሪፍ ጭማሪ ማድረግ ባልተገባ ነበር። ሆኖም ግን ይህ መሆኑ ቀርቶ ሳምንታትን ቀደም ብሎ ትኬት ያልቆረጠ ከሶስት ሺህ አምስት መቶ እስከ አምሰት ሺህ ብር እንዲከፍል ይገደዳል። ይህን ማድረግ ያልቻለ ተማሪ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።

ጉዞውን  “እሱ ያውቃል” (እግዚአብሔር ያውቃል ) ብሎ  በአውቶብስ የሚሄደው ተማሪ እድለኛ ከሆነ ከብዙ እንግልት ጋር  ስልኩን አሊያም ሻንጣውን ወይም የያዛትን ብር ተቀምቶ ይገባል፤ ቀኑ የጠመመበት ደግሞ ይታገትና ክቡር ነፍሱ ለሽያጭ መደራደሪያ ትቀርባለች፤ ወይም ይገደላል፤ አሊያም ደብዛው ጠፍቶ” የውሃ ሽታ” ይሆናል።

ችግሩ በተለይ  ከዓባይ በረሃ አንስቶ እስከ አጐራባች የኦሮሚያ ከተሞች ባሉት ስፍራዎች ተደጋጋሚ የሚከሰት ሲሆን፣ ለዚህም ማሳያ የ2016 ዓ.ም የሁለተኛ ወሰነ ትምህርት ትምህርታቸውን አጠናቀው ለእረፍት ወደየቤታቸው ሲሄዱ የታገቱት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተፈፀመውን ይርጊት ክብዙ በጥቂቱ ማንሳት ይቻላል። ሌሎች ተመሳሳይ በርካታ  ችግሮች   የሚዲያ ሽፋን ሳያገኙ ተድበስብሰው ያለፉትን  እንስቶ መዘርዘሩ ያዳግታል።

ጠግቦ መብላት ቀርቶ  በቀን ሁለቴ በልቶ ማደር  እየከበደ የመጣበት ሀገር ላይ  በኑሮው ውድነት እና በሰላም እጦት ምክንያት መማር ተስኖት እቤቱ የዋለውን እንዲሁም የተሰደደውን ቤት ይቁጠረው። እንደ ቋያ እሳት የሚፋጀውን የኑሮ ውድነት ተቋቁሞ ጥሪቱን ሸጦ፣ ፆሙን እያደረ ያስተማረው ልጁ ዳግም በቅጥር ፍለጋ  መከራውን ያያል፤ ተምሮም  ሥራ ማግኘትም ሌላኛው ፈተና በሆነባት ኢትዮጵያ በተለይ የጀርባ አጥንት ለሌለው ሰው ችግሩ የበረታ ይሆናል ።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች በመኖራቸው   አንዱን ሲሉት  ሌላው እየተተካ አንዳንድ ችግሮች በጆሮ ዳባ ልበስ እየታለፉ ቀላል የማይባል ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ። በዚህም በሀገራችን  ኢትዮጵያ ስርአት አልበኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣት ለበርካቶች ህይወት ማለፍ፣ ለበርካቶች መፈናቅል፣ መሰደድ፣ ለመሰረተ ልማት ውድመት እና ለመሰል ችግሮች በመዳረግ ሀገሪቱን በድህነት አረንቋ ሲደፍቃት ኖሯል።

ሀገር ማለት ህዝብ ነው፤ ያለ ሀገር ህዝብ ሊኖር አይችልም፡፡ ያለ ህዝብም የምትኖር ሃገር ሀገርነቷ ቀርቶ ምድረ በዳ መሆኗ አይቀርም። የሰላም እጦት ሀገርን ይንጣል፡፡ በሂደት ሀገር  የተገነባችበትን  ግርግዳ መሰንጠቅ ይጅምራል፡፡ ከዚያም  ምርጊቱ እየረገፈ የህዝብ ትከሻን መድቃት ይጀምራል፡፡ የዛኔ በናዳው የደደረው የህዝብ ትከሻ ጎብጦ ማሽብረኩ  አይቀሬ ይሆናል። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለማለፍ በቆየው ኢትዮጵያዊ ባህል መሠረት ልንተሳሰብ፣ ልንደጋገፍ  ይገባል፡፡

(ኢዮብ ሰይፉ)

ከባሕዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ተማሪ

በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here