ጀምስ ክሌር የልማድን ጉልበት በሚያትትበት መጽሐፉ 40 በመቶው የሰው ልጅ የቀን ከቀን ውሎ በልምድ የሚደረግ ነው ይላል። ልማድንም ሲተረጉመው በዕለት ውሏችን የምንከውናቸው ውሳኔዎች ድምር ውጤት ነው ይላል። ልማድ ለውጤትም ለጉድለትም የሚጠቀስ የሰው ልጆች አኗኗር ነው። እውቁ አሳቢ አርስቶትል እንዲያውም “እኛ የሰው ልጆች በተደጋጋሚ የምናደርገውን ነን” በማለት ልማዳችን ማንነታችንን ይተረጉመዋል ብሏል። በህይወታቸው ስኬታማ ሰዎች ልማዳቸው ወደ እድገት የሚመራ እንደነበር፤ በአንጻሩ ደግሞ ያልተሳካላቸው ሰዎችም እንዲሁ የተለየ ልማድ አላቸው። አትሌቶች ባላቸው ክህሎት ብቻ አይደለም የሚሳካላቸው። ይልቅስ ለሰዓታት በሚያደርጉት የመስክ ልምምድ ወቅት ነው ለአሸናፊነት የሚበቁት።
ይህ ልምምዳቸው ነው በውድድር ሜዳ ላይ በሽርፍራፊ ሰከንድ አሸንፈው እንዲደሰቱ የሚያደርጋቸው። ስኬታማዎቹ ሰዎች የሚነግሩን ሊያሳኩት ከሚፈልጉት ግብ በላይ ጠንካራ ልማድ መገንባታቸውን ነው።
ልማድ ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነገር ነው። ጉዳዩ የተገነባው ልማድ ህይወትን የሚለውጥ ወይስ ወደ ድህነት አዘቅት የሚወረውር ነው የሚለው ነው። የሰው ልጅ አዕምሮ ልማዶችን በመገንባት ነው ለየ ዕለት ተግባራት መከወኛ የሚሆን አቅም የሚያገኘው። ለምሳሌ ትናንት ምሳ እንዴት እንደበላን፣ እጃችንን እንዴት እንደታጠብን፣ ወደ ስራ ቦታችን እንዴት እንደተጓዝን፣ ከማን ጋር እንደተገናኘን፣ ስልካችንን እንዴት እንደተጠቀምን…ወ.ዘ. ተርፈ አዕምሯችን በልማድነት ባይመዘግባቸው ምን ይፈጠር እንደነበር እናስበው እስኪ? ከቀናት በኋላ የሄዳችሁበት የወላጆቻችሁ ቤት ዛሬ ስትሄዱ ቢጠፋባችሁ፤ የራሳችሁም ቤት ጠዋት ወጥታችሁ ስትመለሱ ቢጠፋችሁ አስቡት። ጥሩው ነገር አዕምሮ ነገሮችን ለመከወን ፋታ እና ጊዜ ስለሚቸገር ያየነው፣ ያደረግነው፣ የሰማነውን ወደ ልማድ እና ትውስታ ማህደር ወስዶ ያስቀምጠዋል። በተደጋጋሚ ባደረግን መጠን በነገሮች የበለጠ ልህቀት እናሳያለን።
ብስክሌት የሚነዳን ሰው ተመልከቱት። መጀመሪያ እየወደቀ፣ እየተንጋደደ፣ እየተነሳ… ሰው ገጭቶ፣ከተሽከርካሪ ጋር ተላትሞ ነው የሚለምደው።
ከቀናት በኋላ አዕምሮው ብስክሌት መንዳትን በልምድነት ይመዘግብለታል።ውሎ ሲያድር ብስክሌቱ ላይ እንዴት እንደወጣ፣ፔዳሉን እንዴት እንዳሽከረከረው፣ፍሬኑን እንዴት እንደያዘው ሳያስታውስ መድረስ የፈለገበት ቦታ ከች ይላል። የመተንፈስ ያህል ቀላል ይሆንለታል፤ሥራ መሆኑ ይቀራል።
ቻርለስ ዲግ የልማድ ኃይል በሚል ርዕስ ባሰናዳው መጽሐፍ ከዓመታት በፊት የተከሰተን ሁነት ያነሳል። ነገሩ እንዲህ ነው። በ1990ዎቹ ኢዩጂን ፓውሊ የተባለ ሽማግሌ ሰው በትኩሳት ህመም ተጠቅቶ በመጨረሻም ኢንሱፓሌቲስ በተሰኘ በሽታ መካከለኛው የአዕምሮው ክፍል ጉዳት ይደርስበታል። በዚህም ህመም ሳቢያ የማስታወስ አቅሙን ያጣል። ኢዩጂን ቀደም ብሎ ሰላምታ የሠጠው ሰው ተመልሶ ሲመጣ እንደገና በአዲስ ካልተዋወቀው በስተቀር አያስታውስም።ከፊቱ ዘወር ሲል ይረሳዋል።
ቻርለስ ዲግ ይህ ሰው ሰዎችን ባያስታውስም እንኳን የተወሰኑ ተግባራትን መከወኑን በማንሳት ተገርሞ ይቀጥላል። ታማሚው ቢርበው ማዕድ ቤት ገብቶ አቅርቦ ይበላል፤ ከቤት ወጣ ብሎ በእግሩ ተንቀሳቅሶ ወደ ቤቱ ይመለሳል።
ማስታወስ እንኳን ባይችል በልምድ ወደ ማዕድ ቤት ገብቶ ምግብ አቅርቦ መብላት ችሏል። በጭንቅላት ውስጥ ልማድን በመፍጠር የሚያገለግለው የአዕምሮ ክፍል ባዛል ጋንጋሊያ አለመጐዳቱ ነበር ለዚያ ሰው የሚጠቅመው። በዚህም ይህ ሰው ልማዶችን መፍጠር እና ማደራጀትን በተነጠቀ ትውስታ ውስጥ ሆኖ ችሏል።
ጀምስ ክሌር ልማዶች አሉታዊ ከሆኑ በሁለት ወገን የተሳሉ ሰልፎች ሆነው ህይወታችንን ያውኩታል በማለት ያብራራል። “አንድ ልማድ አንድ ጊዜ ከገባ ለእሱ ያለህ ታማኝነት የመለወጥ አቅምህን አንዲሸረሽረው ያደርጋል” ይልና “ብዙ ሰዎች በህይወት የሚጓዙት በአዕምሯዊ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው ከማንነታቸው ጋር የተያያዙ ልማዶችን በመከተል ነው” ሲል ያክላል።
በምሳሌነትም አቅጣጫ መጠቆም አይሳካልኝም ፣ የማለዳ ሰው አይደለሁም፣ የሰዎችን ስሞች ማስታወስ አይሆንልኝም ፣ ሁልጊዜ አረፍዳለሁ፣ ከቴክኖሎጂ ጋር ብዙ አይደለሁም፣ ሒሳብ ትምህርት አይገባኝም እና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን ተከትለን ፣አምነን እንኖራለን ብሏል።
አንድን ታሪክ ለዓመታት እየደጋገምክ ለራስህ ስትነግረው ወደ አዕምሮ ይገባና እንደ እውነት ሆኖ ይቀመጣል። በዚህም ሒደት አንዳንድ ነገሮችን “እኔነቴ ጋር አይጣጣምም” በማለት እምቢ ማለት ትጀምራለህ ሲል ጀምስ ጽፏል። የሰው ልጆች የሚያድጉት ከልማዶች ጋር ነው፤ አድጎ የሚይዛቸውን እምነቶች ይዞ የተወለደ ማንም ሰው የለም። ጀምስ ይህንን ሐሳብ “ልማዶችህ ማንነትህን የምትይዝባቸው መንገዶችን የሚፈጥርባቸው ነገሮች ናቸው፤ በየቀኑ ስትጽፍ የፈጣሪነትን ስሜት ትይዛለህ፤ በየቀኑ የስፖርት ልምምድ ስትሠራ ደግሞ የአትሌት ማንነትን እየተላበስህ ትሄዳለህ” በማለት ይገልጸዋል። ትናንት ሲያንቧች የነበረን ህጻን ዛሬ ሲሮጥ መመልከት እንዴት በዚህ ፍጥነት መጓዝ ቻለ ያስብለን ይሆናል። ቀጥ ብሎ መጓዝ በጥቃቅን ልምምድ ውስጥ ዕይታ አልባ ሆኖ የሚያድግ ዝግመታዊ ተግባር ነው።የተዘራን የበቆሎ ፍሬ ቁመት ሲጨምር የሚያየው የለም፤በቀናት ልዩነት ውስጥ ግን ማደጉን እናያለን።
ልማድን አንድ ጊዜ ድንገት ልንቀይረው የምንችለው አይደለም የሚለው ጀምስ “የምንቀይረው በጥቂቱ፤በጥቂቱ ልማድ በልማድ ነው” ይላል። ስለሆነም “ሁልጊዜ በጥቃቅን ለውጦች ውስጥ እናልፋለን” ይላል። በዝግታ ተጓዝ እንጂ ወደ ኋላ እንዳትመለስ የሚለው ጀምስ “አንድ ልማድ ማዳበር ከፈለግህ ቁልፉ መደጋገም እንጂ ፍጹምነት አይደለም” ብሏል። ልማድን መደጋገም በአዕምሯችን ውስጥ ግልጽ አካላዊ ለውጥ እንዲፈጠር ያደርጋል።ልምምዳችን በሒደት አድጎ ወደ አውቶማቲክ ( ነገሮችን ሳይጨነቅና ሳያስብ) ወደ መከወን ያድጋል። ድብቁ የአዕምሮ ክፍል ነገሮችን ለመመዝገብ፣ለመልመድ ጊዜን ይፈልጋል ።ለረጂም ዓመት የያዘውን ደግሞ ቶሎ አይለቅም። ለዚህ ነው ቂም እና ጥላቻ ውስጣችን ገብቶ ቶሎ ማይወጣው። ይቅር ብንልም ቶሎ አይለቀንም።ለረጂም ጊዜያት እያብሰለሰልን አሳድገነዋልና። አጎቴ ለረጂም ዓመታት ሲገለገልባት የነበረችን ነጭ በቅሎ ሌላ ቀበሌ ይሸጣታል።በቅሎዋ አዲስ የተረከባት ጌታዋን ትታ አጎቴ ጋ መመላለስ አልተው አለች። ይወስዳታል ሮጣ ወደ ቀድሞው ቤት ከች። በቅሎዋ አዲሱ ቤት መልመድ አልቻለችም። በመጨረሻም አጎቴ ብሩን መልሶ በቅሎዋን ተረከበ።
ጠብታ ውኃ አለት ትሰብራለች እንደሚባለው ትንንሽ ልማዶችን መገንባት ለዘላቂ እና ትልቅ ልማድ ግንባታ ያበቃል። ልማዶች የምንፈልጋቸውን ነገሮች ስናደርግ የምናልፍባቸው መሰናክሎች ናቸው። የተስተካከለ ሰውነት እንዲኖረው የሚፈልግ ሰው እንቅስቃሴ በመሥራት የሚመጣን ድካም ማሸነፍ ግዴታው ነው በጀምስ ክሌር ሐተታ።
ወደ ቻርለስ ዲግ ሐሳቦች ዳግም ስንመጣ ልማዶቻችን በህይወታችን ላይ ያሉትን አዎንታዊ እና አሉታዊ ሚናዎች እናገኛለን። የምንበላው ምግብ ፣ ለልጆቻችን የምንናገረው፣ የገንዘብ አያያዛችን (ቁጠባ እና ወጪ) ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴያችን፣ ሐሳቦቻችን እና ንግግሮቻችን በጤናችን ፣በምርታማነታችን፣በገንዘብ ደህነታችን፣ ደስተኝነታችን ላይ የራሳቸውን ተፅእኖ ያሳድራሉ። ልማዶች ከሰው ልጆች ፈቃድ ውጭ የሚፈጠሩ ናቸው የሚለው ቻርለስ በአንዳንድ ቤተሰቦች የሚሆነውን ነገር እና የልማድ አወቃቀር ያነሳል። “በቤተሰብ ውስጥ የሚጠበሱ እና የታሸጉ ምግቦችን በተከታታይነት መብላት የሚፈልግ አይደለም። ከወር አንድ ጊዜ የሚደረገው ልምምድ በሒደት በሳምንት አንድ ጊዜ ወደ መሆን ይሻገራል” በማለት በመጽሐፉ አስፍሯል።
ጀምስ ክሌር “ጥሩ የገንዘብ ነክ ልማዶች ከሌሉህ ሕይወት ሁልጊዜ ትግል ትሆንብሃለች፤ ጥሩ የጤና ልማዶች ከሌሉህ ነጻ ሆነህ መኖር አትችልም። ያለ ጥሩ ትምህርት ነክ ልማዶች ሁልጊዜም ወደኋላ ትሆናለህ። ሁልጊዜም ጥቃቅን ነገሮች ላይ የምትወስን ከሆነ ለነጻነት የሚኖርህ ጊዜ ጥቂት ይሆናል። “ለማሰብ እና ለፈጠራ የሚሆን የአዕምሮ ስፍራ መፍጠር የምንችለው አንዳንድ የሕይወት መሠረታዊ ነገሮችን ቀላል በማድረግ ነው” ሲል ያብራራል። በተቃራኒው ጥሩ ልማዶችን ማዳበር አለመቻል አዕምሮ በህይወት ጉዞ የሚያጋጥሙ አዳዲስ ችግሮችን ለመጋፈጥ ነጻነት እንዲያገኝ ያደርገዋል። ዛሬ የሚገነቡ መልካም ልማዶች ወደ ፊት ማድረግ ምታስበውን በስፋት እንድትከውን ያግዙሃል በማለት ይመክራል።
ጀምስ ክሌር ልማዶች በአራት ደረጃዎች አልፈው እንደሚገነቡ ያትታል። ፍንጭ(ምልክት) ፣ ጉጉት(ፍላጎት)፣ ተግባር (ምላሽ ) እንዲሁም ውጤት ወይም (ሽልማት) በማለት ይዘረዝራቸዋል። በምልክት ፣ ፍላጎት ፣ ተግባር እና ውጤት ደረጃዎች አልፈው ልማዶች ይገነባሉ። ጄምስ በውሏችን ከሚያጋጥሙን ነገሮች አንዱን በምሳሌነት አንስቶ አራቱን ደረጃዎች የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ይሞክራል። ኪስህ ውስጥ ያለው ስልክ የጽሑፍ መልእክት ድምጽ አሰማ እንበል። ይህ ለነገሩ ምልክት ነው። ምን ይሆን የገባልኝ መልእክት ብለህ ትጓጓለህ። ይህ ሁለተኛው ደረጃ ጉጉት ይባላል። ቀጥሎ ስልክህን ከፍተህ የተላከልህን ለማየት ትሞክራለህ። ይህ ሦስተኛ የልማድ ግንባታ ደረጃ ተግባር ነው። መልእክቱን አነበብኸው። ጉጉትህን ታረካዋለህ። ከዚያም በኋላ ስልክህን መክፈት ከመልእክት መቀበያው ድምጽ ጋር ይያያዛል።በወጣትነት ዘመናችን ላይ ስንሆን ሕይወታችንን እየመሩ ያሉትን ልማዶች ብዙም አናያቸውም የሚለው ጀምስ ሁልጊዜም ጠዋት ጠዋት፣ ጠዋት በመጀመሪያ የምናስረው ከተመሳሳይ የአንደኛውን እግራችንን ጫማ መሆኑን ዞር ብለን አናይም በማለት ይቀጥላል። (እኔ የግራ ጫማየን አስቀድማለሁ)።
ሁልጊዜም ከስራ ስንመጣ የሚመቸንን ልብስ መቀየራችንንም ልብ አንልም። ከብዙ አስርት ዓመታት ቀረጻ በኋላ እነዚህን የአስተሳሰብ እና የአተገባበር ሒደቶች ስንከተል እንገኛለን ይላል።
ልማዶች ረቂቅ ናቸው። ባለቤቱ ሳያውቃቸው በድብቁ የአዕምሮ ክፍል ውስጥ ያድጋሉ። ምናልባት ለውጡን አይቶ ሰው ካልነገረን በስተቀር ለራሳችን በብዙ አይታዩም።ለምሳሌ በዙሪያችን አንዳንድ የሚያስቁን ልማዶች አሉ። አባቴ አፍንጫውን የሚናፈጥ መስሎ የሚያወጣው የፉጨት መሳይ ድምጽ አለው። አጎቴ ደግሞ ቁጭ ብሎ ሰው ጋር እያወራ ትከሻውን ይሰብቃል፣ መሬቱን በእግሩ ጠበቅ ያደርጋል። ጀምስ በመጽሐፉ ያሰፈራት የመዋለ ሕጻናት አስተማሪዋ ሴት ስራ ከቀየረች ረጅም ዓመታት በኋላ፤ አለቃዋ ሽንት ቤት ደርሰው ሲመለሱ “እጃችሁን ታጠባችሁ?” ስትል ትጠይቃለች። በተመሳሳይ የዋና ቦታ አደጋ ነፍስ አድን ሠራተኛ ሆኖ ይሠራ የነበረ አንድ ሰው ስራውን ቀይሮ ሌላ ድርጅት ውስጥ ይቀጠራል። ከዓመታት በኋላ ልጆች ሲሮጡ ካዬ “ቀስ እያላችሁ” ማለቱን አልተወም።
አዳዲስ እና ጥሩ ልማዶችን ከመገንባታችን በፊት አሁን ያሉብንን ልማዶች መለወጥ ግዴታ ነው። ይህ የለውጥ ጉዞ ግን ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ልማድ በድብቁ የአዕምሮ ክፍል ውስጥ የሚቀመጥ በመሆኑ። ታዋቂው የስነልቦና ባለሙያ ካርል ጀንግ “ያለ ንቃት በድብቁ የአዕምሮ ክፍል ውስጥ የሚደረጉ ነገሮችን ወደ ንቁው ክፍል ካልቀየርክ በስተቀር ህይወትህን በቀደመው መንገድ መምራት ይቀጥላሉ።ያንን አንተ እጣ ፋንታ እያልክ ትጠራዋለህ” ይላል።
ልማዶቻችን በአካባቢያችን ካሉ ነገሮች ጋር ከሚኖረን መስተጋብር ጋር አብረው ያድጋሉ። እንስሳት ባሉበት ቤት ውስጥ ያደገ ሕጻን እናቱን እያየ ጥጃውን ወይም ላሚቱን ስታባርር እሱም እንዲያው ያድጋል። ከፍ ሲል እጁን ሰው ላይ ያነሳል።
ብዙዎቻችን በአንድ በሁለት ቢራዎች መጠጣት የምንመለስ ልንሆን እንችላለን ነገር ግን በህብረት ስሆን ብዙ የመጠጣት ልማድ አለን። ሁኔታው እና አካባቢው የበለጠ እንድንጠጣ ያስገድደናል።
ጀምስ በሚጠቅሰው አንድ ጥናት ውስጥ ሳይንቲስቶች የእንቅልፍ ችግር ያለባቸውን ሰዎች የድካም ስሜት ሲሰማቸው ብቻ ወደ መኝታ ክፍላቸው እንዲሄዱ አዘዟቸው። እስካልደከማቸው ድረስ ወደ መኝታ ክፍል እንዳይገቡ አስጠነቀቋቸው። በጊዜ ሂደት እነዚህ በሽተኞች የአልጋቸውን አውድ ከመተኛት ጋር ማያያዝ ጀመሩ።ወደ አልጋቸው እንደወጡ መተኛት ቀላል እየሆነላቸው መጣ።
አዕምሯቸው አልጋ ላይ ተጋድሞ ስልክ መነካካት ፣ ቴሌቪዥን ማየት ወይም መጨነቅ ሳይሆን አልጋ ላይ የሚደረግ ነገር መተኛት ብቻ እንደሆነ አወቀ። በአዲስ አካባቢ ውስጥ ልማዶችን መቀየር ቀላል እንደሆነ ታሪኩ ያስገነዝባል። ጀምስ መጥፎ ልማዶችን ራሳቸውን በራሳቸው የሚያነቃቁ ናቸው ይላቸዋል። “በመጀመሪያ ሊያደነዝዙት የሚፈልጉትን ስሜት ያዳብሩታል። መጥፎ ስሜት ይሰማሃል። ከዚያ ታጨሳለህ፤ ስታጨስ የበለጠ የሚያስጨስ ደስ የማይል ስሜት ይሰማዋል” በማለት ሒደቱ ራሱን እንደሚደግም ይናገራል። የመጥፎ ልማድ መፈጠር ፍንጩን መዝጋት መፍትሔ ነው የሚለው ጀምስ “ብዙ ቪዲዮ ጌሞችን የምትጫዎት ከሆነ መጫዎቻውን ነቅለህ ራቅ ያለ ቦታ አስቀምጥ፤ መስራት ያሉብህን ስራዎች እንዳልሠራህ ከተሰማህ ለጥቂት ሰዓታት ስልክህን ሌላ ክፍል አስቀምጠው” እያለ ይመከራል።
ጀምስ ክሌር በቀን በአንድ በመቶ እድገት ጥቃቅን ለውጦች ትልቅ ውጤት ማምጣትን መልመድ አለብን ይላል። የሰጠውን ምሳሌ እነሆ። “ቤትህ ውስጥ ጠረጴዛ ላይ አንድ የበረዶ ቁራጭ አስቀምጠሃል እንበል። ክፍሉ በጣም ቀዝቃዛ ነው። የሙቀት መጠኑ 25 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው። በመቀጠልም ክፍልህ በሒደት እየሞቀ መጣ። 25 ዲግሪ፣ 26…31 እስካሁን ምንም አልተፈጠረም። ከ32 ዲግሪ በኋላ በረዶው መቅለጥ ይጀምራል ከቀደመው ሙቀት የተጨመረው ከ31_ወደ 32 ነው የአንድ ቁጥር መጨመር ለውጥ አመጣች።
ብዙውን ጊዜ ሁኔታ ቀያሪ ቅጽበቶች ቀደም ብለው የተሠሩ የብዙ ተግባራት ድምር ውጤቶች ናቸው። እነዚህ ተደራራቢ ለውጦች ዋናውን ለውጥ ለማምጣት የሚያስፈልገውን አቅም ይገነባሉ። ጀምስ እንደሚለው ካንሰር የሕይወት ዘመኑን 80 በመቶ የሚያሳልፈው የማይታይ ሆኖ ነው። የሰውነት ክፍልን የሚቆጣጠረው ግን በወራት ውስጥ ነው።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም