“ልጄን ቢመልስልኝ…”

0
323

በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 01 አካባቢ ካለ አንድ የባሕል ሕክምና ማዕከል ዘመድ ለማሳከም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ ተገኝቻለሁ፤ በቦታው በርካታ የውስጥ ደዌ ሕክምና የሚፈልጉ ሕሙማን እየገቡ በወረፋ ካርድ ያወጣሉ:: በሀምሳዎቹ አጋማሽ የዕድሜ ክልል የሚገኙ እናት ወ/ሮ ፀሐይ መኮንን አንድ በዐሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ወንድ እና ከሱ ብዙም የማትበልጥ ሴት ልጅ ይዘው መጡ:: በአንድ አካባቢ ስለተቀመጥን ልጃቸው ወደ ውጭ በወጣ ቁጥር “እስኪ ተከተይው … ዕይው” እያሉ ሴቷን ልጃቸውን ሲያስጨንቁ፣ እርሳቸውም ይጨነቃሉ::

የመተዋወቅ ዕድሉን ካገኘን በኋላ “ልጅዎትን ምን አሞት ነው?” ስንል ጠየቅን፤ እናት ታዲያ ጭንቅ ጥብብ እያሉ “ልጄን ምን እንደነካብኝ እንጃ፤ ይኸው ትምህርት መማር የለ፣ መታዘዝ የለ፣ … ከጠዋት እስከ ማታ ውጪ  ነው ውሎው:: በፊት በፊት  የስፖርት ቁማር እያለ እዛ ወረቀት ላይ አፍጥጦ አልፎ አልፎም ቢሆን  ቤት ይውል ነበር፤ አሁን ግን ውሻው እያለ ጠዋት ይሄዳል:: ለመኝታ ነው ቤቱ የሚገባው” ሲሉ መለሱልን::

እናት እንባ እየተናነቃቸው  ሐሳባቸውን ቀጠሉ፣ “ደህናው ልጄ …ትንሹ፣ ታዛዡ ልጄ፣ ጎበዙ ልጄ፣ የት ይደርሳል! ስል ትምህርቱን አቋርጦ በየምንሜናው ሲውል በጤናውማ አይደለም ብዬ የምወስድበት ቢጨንቀኝ ሰው አማክሬ ባሕል ሕክምና አመጣሁት” ሲሉ የመጡበትን ምክንያት አጫወቱን::

አብራ የመጣችው ታላቅ እህቱም ሁኔታውን ስትገልፀው፣ “በትምህርቱ ጎበዝ፣ በደረጃ የሚወጣ፣ የ16 ዓመት ታዳጊ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ የጀመረው የቨርቹዋል (ቁማር) ለነሱም ለሱም ሳይታወቅ ዛሬ ላይ ማንንም መሥማት የማይችልበት ደረጃ አደረሰው” ብላለች፤ እናታቸውም በሱ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ እንደገባች ገልጻ “ታማሚ እንዳትሆንብን ብለን በስንት ግድ ወደ ባሕል ሕክምና ይዘነው መጣን” ነው ያለችው::

እናት ታዲያ እጃቸውን እያርገበገቡ “እንደው ሕክምናው ልጄን ቢመልስልኝ ብዬ …” እያሉ እንባቸውን እያፈሰሱ ሲያወሩ ለተመለከተ ስንት እናት በየቤቱ በቁማር ምክንያት የልጆቹ እና የወደፊት ጧሪዎቻቸው ሕልም እየመከነ መሆኑን ከበቂ በላይ ማሳያ ይሆናል::

ቢቢሲ በጥቅምት 16 ቀን 2019 እ.ኤ.አ በወቅቱ የተሠራን ጥናት ዋቢ አድርጎ ያወጣው ዘገባ እንደሚጠቁመው 55 ሺህ የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ11 እስከ 16 ዓመት የሚደርሱ የእንግሊዝ ታዳጊዎች አሳሳቢ የሚባል የቁማር ሱሰኞች ሲሆኑ የአብዛኛዎቹ ቤተሰቦች ደግሞ ስለ ልጆቻቸው ሱሰኝነት ዕውቅና የላቸውም። በ2022 እ.ኤ.አ ቢቢሲ በድጋሚ በጉዳዩ ዙሪያ በሠራው ዘገባ በእግር ኳስ አማካይነት የሚደረግ ቁማር (ቤቲንግ) ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ  ተስፋፍቷል ነው ያለው። በዚህ ቁማርም ለእግር ኳስ ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ታዳጊዎች እና ወጣቶች ዋነኛ ተሳታፊዎች ናቸው።  ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ የውርርድ ቁማር በበርካቶች ዘንድ ወደ ሱስነት እየተሸጋገረ ነው።

ጌታቸው ዓለማየሁ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ ይገኛል፤ ወጣቱ ከበኩር ጋር ባደረገው ቆይታ “በቁማሩ  ተሳታፊ ነበርኩ” ይላል፤ ቁማሩን ሲጀምርም እንደቀልድ በ20 ብር የገዛው ትኬት ካሸነፈ የአንድ መቶ ሺህ ብር አሸናፊ እንደሚሆን ሲያስቀምጥለት ብሩ አጓጉቶት መሆኑን ያስታውሳል:: ይሁን እንጂ በአሸንፋለሁ ተስፋ ሦስት ሺህ ብር መበላቱን ነግሮናል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን  ልብስ ሲታጠብ ባለቤቱ የቁማር ወረቀቱን ተመለከተችው፤ ይህም ከባድ ጭቅጭቅን አስከትሎ እስከ ሽማግሌ ቢደርስም ጆሮ ዳባ ልበስ በሚል ቁማሩን ቀጠለ:: በዚህ መሃል የኢንተርኔት መዘጋት ቁማር ቤት እንዳይሄድ አደረገው፤ ይህም ቆም ብሎ ራሱን እንዲመለከት፣ ትዳሩንም እንዲያስታውስ ዕድል ሰጠው፤ ከዚህ ጊዜ በኋላም ቁማርን እርም ብሎ እንደተወ ነግሮናል::

ሌላው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ወጣት እንደገለፀልን ደግሞ መጀመሪያ ወደ ቁማሩ ሱስ የገባው ለሥራ ወደ ባሕር ዳር ሲመደብ መሔጃ የለኝም በሚል እየሄደ በመቀመጥ ነው፤ ቀስ በቀስ በትንሽ ብር ቁማሩን መጫወት ቀጠለ:: ከዚያም ሙሉ ለሙሉ የቁማሩ ሱሰኛ ሆነ:: በዚህም ደመወዙ አልበቃ ብሎት የቤት ኪራይም መክፈል አቅቶት ከተከራየበት ቤት እንዲለቅ በመገደዱ ተጠግቶ እንዲኖር አድርጎታል::

እጁ ላይ ብር ካለ ወደ ውሻ ውድድር (ቨርቹዋል ጌም) ሄዶ እንደሚያጠፋው ይናገራል፤ ሕይወቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ዕቁብ አምስት ሺህ ብር ገብቶ እንደነበር የሚናገረው ወጣቱ በሱሱ ምክንያት የገጠመውን መጥፎ ክስተትም ያስታውሳል:: ዕቁብ እየጣለ በሁለተኛው ወር ዕቁቡን ለመስጠት እየሄደ ድንገት ጌም (ቁማር) ቤት ተመለከተ፤ ወደ ቁማር ቤቱም በመግባት ሲጫወት የዕቁቡን ብር በቁማሩ ጨረሰው:: በዚህም ምክንያት ከዕቁቡ መባረሩን፣ ሕይወቱንም አስተካክሎ ለመምራት እንደከበደው ነው ያስታወሰው:: በተለይም አንድ ቀን ትንሽ ብር ካሸነፉበት ሁሌም ይገኛል በሚል ተስፋ እንደሚሄዱበት ገልፆ ባጃጃቸውን ሁሉ አስይዘው የሚጫወቱ በርካታ ወጣቶች እንዳሉ ይናገራል::

በሌላ በኩል በ2015 ዓ.ም በዚሁ ሥራ ሰባታሚት አካባቢ ተከራይታ ሥትሠራ የነበረችው ወጣት ዝናሽ አታላይ ለሁለት በመሆን ሥራውን በሁለት ኮምፒውተር ለመጀመር በወቅቱ ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ አውጥተዋል::

ሰዎች ከእስክሪኑ ላይ ያዩትን ቁጥር ቁረጭልን በሚሉ ሰዓት ከአስር ብር ጀምሮ እየቆረጡ እንጀሚጫወቱ ትናገራለች::

በ10 ወይም በ20 ብር ጀምሮ እስከ አንድ ሺህ አምስት መቶ እና ሁለት ሺህ ብር ድረስ በአንድ ጊዜ መቁረጥ እንደሚቻል እና በአንድ ቀን 11 ሺህ ብር ድረስ ተበልቶ የሚወጣ ሰውም እንደሚኖር ገልጻለች::

ዝናሽ ከግጭቱ መጀመር በኋላ ኢንተርኔት ሲዘጋ ሥራውን እንደተወችው ነግራናለች፤ ያለ ኢንተርኔት ሥራውን መሥራት ቢቻልም እቃ ግዙ ተብለው የተላኩ ልጆች ጭምር ቁማር ሲጫወቱ ቆይተው ብራቸው ሲያልቅ ቤቴ እንዴት ልግባ እያሉ ሲያለቅሱ መመልከቷ በሥራው እንዳትቀጥል አድርጓታል::

በመኖሪያዋ ባሕር ዳር ከተማ “በየሰፈሩ በየትንሽ ርቀት ልዩነት ቢያንስ ሁለት ጌም ሃውስ (ቁማር ቤት) አለ:: መንገዶችን ተከትሎ በሁለቱም አቅጣጫ መብራት ባይኖር እንኳን በጀነሬተር ተጠቅመው የሚያጫውቱ ቤቶች መብዛት በርካታ ታዳጊዎች፣ ወጣቶች፣ ህፃናት፣ ጎልማሶች ሱሰኛ በመሆን ከባድ ማሕበራዊ ቀውስ እያስከተለ ነው” ብላለች::

ጉዳዩን በተመለከተ የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የወጣት አደረጃጀት እና ሰብዕና ልማት ድጋፍ ክትትል ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ይታየውን በኩር አነጋግራቸዋለች፤ ዳይሬክተሩ በምላሻቸው “ሐሳቡ ተነስቶ ፈቃድ የሚሠጠው አካል ፈቃድ መስጠት ማቆም አለበት ተብሎ ነበር፤ ነገር ግን አሁን ያለው የፀጥታ ችግር እና የበጀት አለመኖር ተደማምሮ የችግሩ ሥፋት ምን ያህል ነው? የሚለውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለማጥናት የተደረገውን ጥረት እንዳይሳካ አድርጎታል” ብለዋል::

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ፈቃድ የሚሰጠው አካል  ከገቢ ጋር ያያይዘዋል፤ ቢሮው ከአደንዛዥ እፅ ጋር ዜጎች ወደ ማንኛውም ሱስ እንዳይገቡ የማሳወቅ ተግባር ካልሆነ ማስቆም አይችልም:: በመሆኑም ፈቃድ የሚሰጠው አካል የቨርቹዋል ጌምን እና የቁማርን ፈቃድ መስጠት እስካላቆመ ድረስ መፍትሔ የለውም::

እያደረሰ ያለውን ችግር፣ የሚያስከትለውን የጤና እክል፣ … መገናኛ ብዙኃንም በትኩረት ሊሠሩበት እንደሚገባም ጠቁመዋል፤ “በጥናት ላይ ተመሥርቶ የሚያስከትለውን የከፋ ጉዳት ማየት እና ማሳወቅ ካልተቻለ ንግግር ብቻ ነው የሚሆነው” ብለዋል::

የባሕር ዳር ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ፍትኃነገስት በዛብህ በበኩላቸው እንደ ምክር ቤት አመራር ብዙ ልጆች ከቤት እንዲወጡ እና ሃብት፣ ንብረት እንዲባክን ያደረገ ማሕበራዊ ቀውስ  መሆኑ በግል የመነጋገሪያ ጉዳይ ቢሆንም ጉዳዩ በምክርቤት ደረጃ ቀርቦ ውይይት አልተደረገበትም ብለዋል፤ በቁማሩም ባሕር ዳር ከተማ ከፍተኛ ስጋት ያለባት ናት:: ይሁን እንጂ ከጎጂ ልማዶች በተለይ ጫት ላይ ክልከላ ለማስቀመጥ በምክር ቤት ቢቀርብም ሌላው ግን አለመቅረቡን ገልጸውልናል::

የብሔራዊ  ሎተሪ አስተዳደር  የሕዝብ ግንኙነት አቶ ቴዎድሮስ  ንዋይ   ከስፖርታዊ  ውድድር ጋር ተያይዞ በየቦታው የሚከፈቱ ውርርድ (ቤቲንግ) ቤቶች እንደ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ቁማር አይደሉም ተብሎ እንደሚገመት ገልጸው “አሁን በየቦታው  ወጣቶች እየተጫወቱ ያሉት ግን ቨርቹዋል ጌም ነው እንጂ ቤቲንግ (ቁማር) አይደለም” ብለዋል::

አቶ ቴዎድሮስ እንዳሉት የቤቲንግ ስፖርት ውርርድ ላይ ተወራራጁ ከኳሱ ውድድር ጋር ብቻ ስለሚቆይ ቁማር አይደለም:: የቨርቹዋል ጌም ግን ረጅም ሰዓት ቁጭ ብሎ ያሳልፍበታል፣ ቁማርም ነው። የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርም የሚያስተዳድርበት ሕግ የለም (አያስተዳድረውም) ነው ያሉት::

አስተዳደሩ ለቤቲንግ (ቁማር) ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ያለ አግባብ የማይሆኑ ቦታዎች ላይ እየተጫወቱ ስለነበር ይህንን ሥራ አስቁሞ ለሁለት ዓመት ያህል ፍቃድም አልተሰጠም:: ጥናት ተደርጎ፣ ተስተካክሎ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሠሩት ከአስተዳደር እና ከፈቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ   አዲስ የተሻሻለው መመሪያ 172/2014 ደንበኞች ከ21 ዓመት በላይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፣ ለፈቃድ ማውጫ የሚከፈለውን አራት መቶ ብር በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ተግባራዊ ሲሆን አምስት መቶ ሺህ ብር ሲሆን፣ በባንክ ማስያዝ የሚገባው ገንዘብ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር የነበረው ወደ ሁለት ሚሊየን ብር ከፍ ብሏል::

በሌላ በኩል ከሐይማኖት ተቋማት እና ከትምህርት ቤት አምስት መቶ ሜትር ርቀት ላይ መሆን  ይገባዋል:: ቤቲንግ የስፖርታዊ ውድድር ስለሆነ ማገድ አይቻልም፤ የቨርቹዋል ጌም ግን የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፣ ፈቃድ አይጠይቅም ሲሉ ነው ያጠቃለሉት::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here