ልጄ አልሞተም

0
62

ስሙ ግር ይላል። የጥበብ ሰው አንተ ነው የሚባለው በሚል የወል ሐሳብ  ተስማምቼ አንተ እያልሁ ልቀጥል። “አለ” የሚለው ቃል ጠብቆ ሲነበብ እውነትም ትክክለኛውን ስሙን ይናገራል። የአባቱም ስም ትንሽ ግር ይላል። “ፈለገ” የሚለው ቃል ላልቶ ይነበባል። በኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት ከተማሩት አንዱ ነው።  የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት የከፈተ፣ ያስተማረ እና የመራውን ሰው ታሪክ ዛሬ እንመለከታለን።

“አንዳንድ የኢትዮጵያ ሰዓሊዎች የሕይወት ታሪክ” የሚለው መጽሐፍ እንደ ጠቀሰው ሰዓሊ እና መምህር አለ ፈለገ ሰላም ኅሩህ ትውልዱ በሰላሌ ፍቼ ከተማ ነው። ዘመኑም 1915 ዓ.ም ነበር። የሁለት ወር ጨቅላ ሕጻን ሳለ አባቱ ፈለገ ሰላም ፈረስ ሲጋልብ ወድቆ ሞተ። በሰዓሊ አያቱ አለቃ ኅሩይ ቤት አደገ። ሕጻኑን አለን ሲመለከቱ ልጄ ፈለገ ሰላም ልጅ ተክቷልና አልሞተም ብለው “አለ” የሚል ስም አወጡለት።

የአለ ፈለገ ሰላም አያት አለቃ ኅሩይ በአጼ ምኒልክ ዘመን የአብያተ ክርስቲያናትን ስዕል በመሳል የታወቁ ነበሩ። የልጅ ልጃቸው አለ ያሳደገው ይህንን ከቤተሰብ የወረሰውን ጥበብ ነበር። አለ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ አዲስ አበባ ይኖሩ ከነበሩት አጎቱ  ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ ዘንድ ሄዶ ዘመናዊ ትምህርት  መማር ጀመረ።

የአለ ፈለገ ሰላም ቤተሰብ ሰዓሊ ነው ማለት ይቻላል። አያቱ አለቃ ኅሩይ በአጼ ምኒልክ የሚመሰገኑ ሰዓሊ ነበሩ። በዚህም የእንጦጦ ማርያምና ራጉኤል አብያተ ክርስቲያናትን  የግድግዳ ላይ ስዕሎች ሰርተዋል።

ልጃቸው ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይም መንፈሳዊ እና  ዓለማዊውን ሥዕል በመሥራት የሚታወቁ  ነበሩ። በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት  በአጼ  ኃይለ ሥላሴ ዘመን  ተቀጥረው ይሠሩ ከነበሩት ሠዓልያን አንዱ ነበሩ፡፡

አለ ፈለገ ሰላም ወደ አዲስ አበባ የተላከበት ምክንያት የቅኔ ትምህርት ይማር በሚል ቢሆንም ብዙ አልገፋበትም። በጣሊያን ሁለተኛው ወረራ ወቅት በአርበኝነት ዘምተው የነበሩት አሳዳጊው አጎቱ  እምአዕላፍ ኅሩይ ከጦርነቱ ሲመለሱ አንተ ዘመናዊ ትምህርት ነው መማር ያለብህ ብለው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስገቡት።

አንድ ቀን አጼ ኀይለ ስላሴ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን ሲጎበኙ የአለን ስዕሎች ይመለከታሉ። ይህን የሳለው ማነው ሲሉም ይጠይቃሉ። ንጉሡ ስዕሎችንም ሰዓሊውንም አደነቁ። ቤተመንግሥት ጠርተውም “በል አሁን ጥሩ ሠዓሊ ሆነህ ተገኝተሃልና ወደ ውጭ አገር ሄደህ ሥዕል ተማር” በማለት ስላዘዙ ሁኔታዎች ሁሉ በአፋጣኝ ተከናውነው አሜሪካ ቺካጎ አርት ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ትምህርቱን ተከታተለ።

ከዚያም በኋላ በፍጥነት ወደ ሀገሩ በመመለስ ከአያቱ እና አጎቱ የወረሰውን የስዕል ሙያ ከዘመናዊው ዓለም አሳሳል ጋር በማቀናጀት ማሳደግ ስለሚችልበት መንገድ ማሰብ ጀመረ። በአውሮፓ የተለያዩ የጥበብ ስራዎችን ጎብኝቷል። ያ ትምህርት እና ጉብኝት  በሀገሩ “አዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት”ን የመመስረት ሐሳብ ወለደለት።

ትምህርቱን  አጠናቅቆ እንደተመለሰም  ከንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ፊት ቀርቦ እጅ ነሳ። “በአገራችን የሥዕል ትምህርት ቤት እንዲከፈትና የኔም ተግባር በሚከፈተው የሥዕል ትምህርት ቤት ማስተማር እንዲሆን እፈልጋለሁ” ሲልድ ሐሳቡን  ለንጉሡ አቀረበ።

በወቅቱ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ተመድቦ በልጆች መማርያ መጻሕፍት ላይ ሥዕሎችን መሥራት ጀመረ።

ከዚሁ ጎን ለጎን ትምህርት ቤቱን የመክፈት ራዕዩን ለመጀመር ግን የመንግሥትን ውሳኔ አልጠበቀም፡፡ በሚኖርበት ቤት ግቢ  ውስጥ አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት ቅዳሜና እሑድ ማስተማር ጀመረ፡፡  የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የስዕል ትምህርቱን ተከታተሉ፡፡  በወቅቱ የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ሚካኤል እገዛና ድጋፍ ከክረምቱ ባለፈ በበጋውም ማስተማሩን ቀጠለበት። ካስተማራቸው ተማሪዎች ጥሩ ስራዎችን በመምረጥ መርጠው ልዕልት ተናኘ ወርቅ ኀይለ ሥላሴ  በተገኙበት አውደ ርዕይ አዘጋጁ፡፡ የተመረቀው ዐውደ ርዕይም ትምህርት ቤት የመመሥረት ራዕዩ ዕውን የሚሆንበትን አጋጣሚ ፈጥሮለታል።

ለዐውደ ርዕዩ ታዳሚዎች ባደረገው ንግግር  የብዙዎችን ቀልብ ሳበው። ለጥበብ ያለውን ተቆርቋሪነት በሚገባ አስረዳ።  በዐውደ ርዕዩ የቀረቡትን ሥዕሎችም እንዲገዙ በጠየቀው መሠረትም ብዙዎቹ ተሸጡለት፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ ስለ አለ ፈለገ ሰላም የትምህርት ቤት ምስረታ ታሪክ እንዲህ ሲል ጽፏል “በዕለቱም ግሪካዊ ከበርቴ የሰጠውን 50,000 ብር ጨምሮ 78,000 ብር ተሰበሰበ፡፡ ለጃንሆይም ያስረከቡት ‘በራሴ ጥረት ይችህን ገንዘብ አግኝቻለሁ ተማሪ ቤት ይሥሩልን’ በማለት ነበር”

“በንጉሡ  ትዕዛዝም 150,000 ብር ተጨምሮበት የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህር ቤት ተከፈተ፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ የልደት ቀን ሐምሌ 16 ቀን 1950 ዓ.ም ትምህርት ቤቱ ተመርቆ ተከፈተ። ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኀይለ ሥላሴ ያስገነዘቡት ዐቢይ ነጥብ፣ በሥነ ጥበብ ታላቅ ሞያ ያላቸው ወጣቶች ሁሉ ጥንታዊውን አሠራር ሳይለቁ ከዘመናዊው ጋር እያዋሐዱ እንዲሄዱ የሚለው ነበር።” አለፈለገ ሰላም የት/ቤቱ የመጀመሪያው ዳይሬክተር በመሆን እና በማስተማር  እስከ 1967 ዓ.ም ለ16 ዓመታት አገልግሏል።

በኢትዮጵያ የዘመናዊ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በሠዓሊ አለ ፈለገሰላም መመሥረት ለኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማበርከት ችሏል፡፡  ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ እስክንድር በጎሲያን፣ ታደሰ ግዛው እና ሌሎች የትምህርት ቤቱ ምሩቃን የሆኑ ታላላቅ ሠዓሊያን በትምህርት ቤቱ ውስጥ በማስተማር ከፍተኛ ውጤትም አስገኝቷል፡፡

የደርግ መንግሥት ሲመጣ ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም በራሱ ፍላጎት ሥራውን ለቆ ወደ ባህል ሚኒስትር በመግባት የቅርስ ጥገና ክፍል ኃላፊ በመሆን ሰርቷል። በዚህም ጊዜ  በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ ተከማችተው የነበሩትን ቅዱሳን መጻሕፍትና ሥዕላት ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲጠበቁና እንዲጠገኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

አለ ፈለገ ሰላም ምንም እንኳን ዘመናዊውን የስዕል ትምህርት አሜሪካ ሄዶ ቢማርም፤ አሳሳሉ ግን ሀገራዊ ይዘቱን የለቀቀ አልነበረም። መንፈሳዊ ስዕላትን በብዛት በመሳል ይታወቃል። ከስዕሎቹ በላይ ምናልባትም ትምህርት ቤት መመስረቱ ጎልቶ የወጣ ጉዳይ ይመስላል። ብዙዎችን ሰዓሊያንን ያፈራን ትምህርት ቤት መክፈት ስዕል ከመሳልም በላይ ሳይሆን ይቀራል?

በሰዓሊነት ሙያው ብዙ የግድግዳ ላይ ስዕሎችን ሰርቷል። በኢትዮጵያ ባሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት የሠራቸው  የሥዕል ሥራዎች በርከት ያሉ ናቸው፡፡ ከአለፈለገ ሰላም ተደናቂ ስዕሎች መካከል የጦርነት ፊት፣ አባትና ልጅ፣ አሁንም እናት አገር ወይ ሞት እና ጥቁር አባይ የሚባሉ ይገኙባቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ፣ የፀጉር አሰራር ስልትን የሚያሳይ እና ልዩ ልዩ ታሪካዊ ስፍራዎችን የሚያሳዩ ቴምብሮችን ሠርቷል፡፡

የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1947 ዓ.ም ሲሠራ ትውፊታዊና ዘመናዊ የሥነ ጥበባት ሙያዎች ባዋሐደ መልኩ የኢትዮጵያን የቅዱሳን ታሪክና ድርሳናት አጢኖ፤ በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የቅድስት ሥላሴን ሥዕልና በጉልላቱ ላይ የተሣለውን የቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ሥዕል ከሌሎች ቅዱሳን ሥዕላት ጋር  በማድረግ መሳሉ ይጠቀሳል፡፡ በአዳማ የቅድስት ማርያምን፣ በአዲስ አበባ የጎፋ ገብርኤልን፣ እንዲሁም የቁልቢ ገብርኤልን፣ በመርካቶ የቅዱስ ሚካኤል ካቴድራልንና በመርካቶ የቅዱስ ራጉኤልን ቤተክርስቲያንና በዋሽንግተን ዲሲ የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እንዲሁም በሌሎች የሚገኙ ቅዱሳን ሥዕላት በመሥራት አሻራውን አስቀምጧል።

 

ሥዕሎቹ የኢትዮጵያ ትውፊታዊንና ዘመናዊ የእውነታ አሣሣልን ያቀናጁ፣ ብሔራዊና ኢትዮጵያዊ ድባብን የተላበሱ፤ ስሜትንና ህሊናን የሚስቡና የተረጋጉ ሥዕላት እንደነበሩ ይነገራል፡፡  እነዚህ  ሥራዎች በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በሕንድ፣ በሶቪየት ኅብረት፣ በቼኮዝላቫኪያ፣ በግሪክና በዩጎዝላቪያ  አውደ ርዕይ ታይተዋል፡፡

ሥራዎቹ የኢትዮጵያን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ከዘመናዊ የአሳሳል ስልት ጋር ያዋሀዱ ናቸው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቤቱን በስሙ  “አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት” ብሎ ሰይሞለታል።

ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ስለ አለ ፈለገ ሰላም አሳሳል ሲናገር እንዲህ ይላል “አለ ፈለገሰላም በአሜሪካ የተማሩትን ዘመናዊ የሥዕል ዕውቀት ከኢትዮጵያ ትውፊታዊና ባህላዊ የአኗኗር ልምዳቸው ጋር አዋህደዋል። ሥራዎቻቸው በቅርጽ የእውነታ ጥበብን (ሪያሊዝም) ከከፊል ትውፊታዊ አቀራረብ ጋር ያጣመሩ ሲሆኑ፣ በይዘት ደግሞ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና የመልክአ ምድር ጉዳዮችን ይዳስሳሉ”  ብሏል።

በ 2008 ዓ.ም በ 93 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ስርዓት ቀብሩም   በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተፈጽሟል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here