ልጅ ኢያሱ

0
250

ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

 አሥራ ዘጠን ዜሮ ዜሮ ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት መለወጫ ብቻ ሳይሆን የአዲስ ክፍለ ዘመን መሸጋገሪያ ወቅትም ነበር። ይህ ዓመት ሳያልቅ ግን ለኢትዮጵያውያን ብስራት ሳይሆን መርዶ ተሰማ። “እምዬ” ብሎ የሚጠራቸው እጅግ የሚወዳቸውን ታላቅ መሪውን ሕመም አልጋ ላይ ስለጣላቸው የሕዝቡ ተስፋ የጨለመበት እና ድንጋጤ ውስጥ የገባበት አሳዛኝ ወቅት ነበር። ሁሉም በየእምነቱ የመሪው ጤና እንዲመለስ ከፈጣሪው ምሕረት እየለመነ ከዛሬ ነገ ይሻላቸው ይሆናል በሚል ተስፋ ቢጠባበቅም እየባሰባቸው ሄደ። በዚህ መካከል ነበር ንጉሡን የሚተካው ቀጣይ ንጉሥ ማንነት እና የኢትዮጵያ መፃኤ እድል ሁሉንም ማስጨነቅ የጀመረው።

አርቆ አሳቢው ዐፄ ምኒልክ በሕመማቸው ውስጥ ሆነው የሀገራቸው መፃኤ እድል ያሳስባቸው ነበርና አልጋ ወራሻቸውን ይፋ አድርገው ሕዝቡን ከጭንቀት እና ከትርምስ ገላገሉት። ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ.ም. አቡኑ ባሉበት እና መኳንንቱ በተገኙበት የልጅ ልጃቸው ልጅ ኢያሱ የዙፋናቸው ወራሽ ወይም ቀጣዩ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እንደሚሆን አስታወቁ።

ልጅ ኢያሱ የሴት ልጃቸው ሸዋረጋ እና የወሎው ባላባት የራስ ሚካኤል ልጅ ሲሆን በወቅቱ የ13 ዓመት ታዳጊ ነበር። ምንም እንኳን ዕድሜው ለንግሥና የሚያበቃው ባይሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዐፄ ምኒልክን ከልቡ ይወድ ስለነበር ለልጅ ኢያሱ እንገዛለን በማለት የልጅ ኢያሱን አልጋ ወራሽነት በደስታ እንደተቀበለ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ ፅፈዋል።

በዐፄ ምኒሊክ አዋጅ ውስጥ እንደተመለከተው በመካከላቸው ምቀኝነትን፤ መጋጨትን አስቀርተው ርስ በርስ ተስማምተው በፍቅር እንዲኖሩ ለምነዋል፡፡ “አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት ርስ በርስ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ሀገራችሁን ኢትዮጵያን ለሌላ ለባእድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር ሀገራችንን አያገኛትም ብለው ነበር፡፡

“እንግዲህ እኔ እንደተመኘሁት እግዚአብሔር ተጨመረበት እና ፈቃዱ ሆኖ ልጄን ኢያሱን ቢያቆምላችሁ ከልጄ ጋር ሆናችሁ ሀገራችሁን ጠብቁ አደራ ብያችኋለሁ“ በማለት አዋጁን ማሳረጋቸውን መርስኔ ኃዘን 20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ጽፈዋል፡፡

አልጋ ወራሹ ልጅ ኢያሱ በወቅቱ ገና የ13 ዓመት ታዳጊ ስለነበር ራስ ተሰማ ሞግዚት ሆነው እስከዚያው እንዲያግዙት ራስ ቢትወደድ አድርገው ሾሟቸው፡፡ በሞግዚትነት የተሾሙት ራስ ተሰማ ግን በ1903 ዓ.ም በመሞታቸው የሞግዚትነት ቦታውን የሚፈልጉ እና ልጅ ልዑል የሚጋፉ ልክ እንደ ራስ አባተ እና ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ አይነት ተቀናቃኞች ብቅ ያሉበት ሁኔታ ነበር፡፡ ኢያሱ ግን ሞግዚት እንደ ማያስፈልገው በመንገር አሳርፏቸዋል፤ እነርሱም ከአንገት በላይ ተቀብለው ውስጥ ውስጡን ግን ውድቀቱን ይመኙለት እንደነበር መርስኔ ኃዘን ይገልጻሉ፡፡

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪከ ከ1847 እስከ 1983 በሚለው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት ልጅ ኢያሱ ከጅምሩ ብዙ ተቀናቃኞች ተነስተውበት ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን ንጉሡ ስላልሞቱ ሙሉ ንጉሥነት ባያገኝም በሞግዚቱ በኩል ስልጣኑን መተግበር ጀምሯል፡፡ በጣይቱ እና በሸዋ መሳፍንት መካከል የተነሳው የፖለቲካ እሳት በታሪክ ውስጥ አስከፊ ሊሆን ወደ ሚችል ደም መፋሰስ ሊያመራ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡

ይሁን እንጅ የሸዋ መሳፍንት ጣይቱ ላይ የመቱት አድማ እቴጌይቱን  ከቤተ መንግሥት አስወጥቶ እንጦጦ በግዞት እንዲያሳልፉ በማድረግ ከስልጣን ገለል አድርጓቸዋል፡፡ የእቴጌይቱ ገለል መደረግ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ውጥረቱን ማብረድ የቻለ እና በተለይ ለልጅ ኢያሱ አመች ሁኔታን የፈጠረ ነበር፡፡

 

በሚያዝያ ወር 1903 ዓ.ም ላይ ሞግዚቱ ራስ ቢትወደድ ተሰማ ሞቱ። በዚህ ጊዜ ሌላ ሞግዚት ይተካልህ ቢባል ኢያሱ “እኔ ራሴ ብቁ ነኝ” በማለት በራሱ መንቀሳቀስ ጀመረ ይላሉ፤ መርስኔ ኀዘን፡፡

ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እንደፃፉት አልጋ ወራሹ ልጅ ኢያሱ ገና ከጅምሩ ካልተጠበቀ አቅጣጫ የሥልጣን ተቀናቃኝ መጣበት። ከጣይቱ ውድቀት በኋላ በድል አድራጊነት ስሜት ወደ አዲስ አበባ ጦራቸውን እየመሩ የገቡት ራስ አባተ ዙፋን ለመጨበጥ ሀሳብ እንደነበራቸው ተደርጎ በቤተመንግሥቱ  ውስጥ ወሬው ተሰራጨ። በዚህ ጊዜ የልጃቸውን ሥልጣን ተቀናቃኝ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ሰራዊት አዝምተው ራስ አባተን መቅደላ ላይ አስረዋቸው ነበር።

በእንቆቅልሽ የተሞላው የኢያሱ ዘመነ መንግሥት  አዝማሚያ የሸዋን መኳንንት የሚያስከፋ እና ብዙ ተቀናቃኞችን ያስነሳበት ነበር። በተለያዩ መፃሕፍት ተደጋግሞ ስለ እርሱ የሚወሳው የኢያሱ ቧልት እና ጨዋታ መውደድ  ነበር። በአንፃሩ ግን በዘመኑ ያከናወናቸው በጎ ተግባራት መጠቀሳቸው ቀርቶ መታወቃቸውም ያጠራጥራል። ከመፃሕፍቱ ይልቅ ፊደልን ያልቆጠረው ሕዝብ ለልጅ ኢያሱ አወንታዊ አመለካከት እንዳለው ፕሮፌሰር ባሕሩ ያስረዳሉ። መልከ ቀናነቱ፣ የንግግር ችሎታው፣ ስፖርተኛነቱ የሕዝብን ህሊና የሚማርክ ነበር። በመንግሥት ስራ ላይ ዋል ፈሰስ የሚል አዝማሚያ የታየበት ቢመስልም ከእድሜው ለጋነት የመጣ ነው ብሎ ሕዝቡ ሊፈርድለት ዝግጁ እንደነበር የሚገልፁት ፕሮፌሰሩ የልጅ ኢያሱን ዘመን የለውጥ ስራዎች ይዘረዝራሉ።

አጭር የስልጣን ዘመን የቆየው ልጅ ኢያሱ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለኝታን በማጠናከራቸው ተራማጅ ሊባሉ የሚችሉ አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል። የግል ንብረትን የማስከበር እና አስራትን በወቅቱ የመሰብሰብ ደንብ ስራ ላይ አውሎ ነበር። ከሳሽ እና ተከሳሽ አብረው እንዲማቅቁ ያደርግ የነበረውን የቁራኛ ስርአት ለመሻር እርምጃ ወስዷል። እንዲሁም ከፍትሕ ይልቅ ለቂም መወጣጫ እና ደካማ ለማጥቂያነት የሚያገለግለውን የሌባ ሻይ ስርአት መልክ ለማስያዝ ሞክሯል። የመንግሥት ሒሳብ ኦዲት በማስደረግ አላግባብ ገንዘብ ባባከኑ ላይ እርምጃ መውሰዱ ኢያሱን ምናልባትም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ ሳያስብለው አይቀርም።

መርስኔ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በተሰኘው መፅሀፋቸው እንዳሰፈሩት የልጅ ኢያሱ ትልቁ ጥፋት የምኒልክን መኳንንት በከበሬታ አለመያዙ እና ለሕግ ተገዥ አለመሆኑ ነው። ባሕሩ ዘውዴ በበኩላቸው እንደገለጹት የልጅ ኢያሱን ውድቀት ያፋጠነበት እና ብዙ ተቀናቃኝ ያስነሳበት ትልቁ ክፍተቱ ፖሊሲዎቹን ግልፅ አለማድረጉ ነበር።

በሀይማኖት ፖሊሲው ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች እኩል የሀገር ፍቅር እንዲኖራቸው ብሔራዊ ስሜታቸውን እያነሳሳ ሀያል የሀገር መሪ ለመሆን ጥረት አድርጓል። ለሙስሊሞች መስጅዶችን እንዲገነቡ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግ ነበር። በተመሳሳይም ለክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን ያሰራ ነበር። ባሕሩ ዘውዴ እንደፃፉት የኢያሱን የሀይማኖት ፖሊሲ ዘመናዊነት የሚወዳደር ፖሊሲ የነደፈ አንድም የኢትዮጵያ መሪ የለም።

የልጅ ኢያሱ እና የሸዋ መኳንንት የፖለቲካ ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው እርሱ ንጉሥ ሳይሆን ግንቦት ወር 1906 ዓ.ም ላይ አባቱን ራስ ሚካኤልን የወሎ እና የትግሬ ንጉሥ አድርጎ መሾሙ እንደነበር አፈንዲ ሙተቂ፣ ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ድሬ ዳዋ በተሰኘ መፅሐፉ አስፍሮታል። በመሆኑም የሸዋ መኳንንት “ይህ ወጣት ከቤተ መንግሥት ጠራርጎ ሳያስወጣን እንቅደመው” በማለት መሯሯጥ ጀመሩ። የዚህ አድማ ዋነኛ መሪ እና አቀናባሪ የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ስለመሆናቸው ብዙ ምሁራን እንደሚስማሙበትም አፈንዲ ሙተቂ ፅፏል።

መርስኔ ሀዘን እንደፃፉትም የልጅ ኢያሱ ተግባራት የሸዋ መኳንንትን ባለማስደሰታቸው እርሱን ከስልጣን ለመጣል መዶለት ጀመሩ። የወጣቱን ስም የሚያጠፉ ወሬዎችን ያናፍሱበት ገቡ። በመጨረሻም መስከረም 10 ቀን 1910 ዓ.ም ላይ ኢያሱን በበርካታ ወንጀሎች በመክሰስ ስልጣኑ በይፋ እንዲሻር አደረጉ። ኢያሱ በጅጅጋ እያለ ነበር ይህ  መፈንቅለ መንግሥት የተደረገበት።

በዚህ ሴራ ምዕራባውያን ተሳትፈው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። የኢያሱ አካሄድ ያላማራቸው በተለይ ሶማሌላንድ ከእንግሊዝ ነፃ ለመውጣት ለምታደርገው ትግል የጦር መሳሪያ በገፍ መርዳቱን እና በአንደኛው ጦርነት ወቅት ጀርመንን እና ቱርክን ደግፎ አቋም መያዙ ያሰጋቸው እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን ኢያሱን ከስልጣን በማስወገድ አድማው ውስጥ ተሳትፈዋል። አፈንዲ ሙተቂ እንደገለፀው ምዕራባውያን በኢያሱ ላይ በተቀናቃኞቹ የሚወራውን ወሬ የሚደግፉ ኢያሱ በፊት ከሐረር እና ከአፋር ሙስሊሞች ጋር የተነሳችውን ፎቶዎች በማራባት በየከተሞቹ ለሕዝብ እንዲደርስ በመበተን እሳት ላይ ቤንዚን  የመጨመር ተሳትፎ አድርገዋል።

ኢያሱ ከአዲስ አበባ ርቆ ስለነበር ሥልጣኑን ማዳን አልቻለም። የቻለውን ያህል ተዋግቶ ሥልጣኑን ለማስመለስ ቢሞክርም ረፍዷል። ሲዶልቱበት የከራረሙት ጠላቶቹ ከውጭ  ጠላቶቹ ጋር ሆነው ከዙፋኑ አውርደውታል። ያለው አማራጭ እጅ ላለመስጠት ወደ አፋር ሸሽቶ ለተወሰኑ ዓመታት መቆየት ነበር። በኋላም አሳዳጆቹ በአፋር እንዳለ ሊይዙት መሆኑን ሲሰማ ወደ ትግራይ ሄደ። በዚያ ብዙም ሳይቆይ ተያዘ እና ለእስር ተዳረገ። በእስር እንዳለም  ሁለተኛውን የጣሊያን ወረራ ተከትሎ የማይጨው ጦርነት ከመጀመሩ ሦስት ቀናት በፊት እንደሞተ ተሰማ። የወጣቱ ልዑል አሟሟት እንቆቅልሽ እንደሆነ አሁን ድረስ ዘልቋል።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here