ልጆችዬ ሰላም ናችሁ? ትምህርትስ እንዴት ነው? እንዴትስ ይዟችኋል? የአንደኛው ወሰነ ትምህርት ፈተና ጀምሯል፤ የፈተና ዝግጅትስ እንዴት ነበር? ጥሩ ነው አይደል? መልካም ልጆች! ከፈተና በኋላ ልጆች የአንድ ሳምንት የረፍት ጊዜ ይኖራችኋል፤ ያንን ጊዜ እንዴት እንደምትጠቀሙ መረጃ እንስጣችሁ፡፡
ልጆች በቤታቸው እና ከቤታቸው ሳይርቁ የረፍት ጊዜያቸውን ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡ በዚህም ጊዜ ልጆች እንደየአቅማቸው ወላጆቻቸውን በማገዝ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር በመጫወት፣ አስተማሪ እንዲሁም አዝናኝ ፊልሞችን በማየት (በወላጅ ምርጫ) እና ወደ መዝናኛ ስፍራዎች በመሄድ ማሳለፍ ይችላሉ።
በተጨማሪም ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበትን ማለትም የሙዚቃ መሳሪያ፣ ስዕል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች፣ ውዝዋዜና ስፖርታዊ ክንውኖችን እንዲሁም ሌሎች ስልጠናዎችን በመውሰድ ያሳልፋሉ።
ልጆች የእረፍት ጊዜያቸውን ከቤታቸው ራቅ ብለው ወደሚገኙ ዘመዶች ጋር ለጥየቃ በመሄድ ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡
የሚሄዱበት አካባቢ ከሚኖሩበት አካባቢ ራቅ ያለ ከሆነ ደግሞ ከዘመዶቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማጠንከሩና ጥሩ ትዝታ ከመፍጠሩ ባለፈ የዚያን አካባቢ ባህል፣ ወግ እና እሴት የማየት የመማርና የማወቅ አጋጣሚውን ይፈጥርላቸዋል፡፡
እንዲሁም ለሚቀጥለው ወሰነ ትምህርት የሚያግዛቸውን ማጠናከሪያ ትምህርት በመማር፣ መጽሐፎችን በማንበብ፣ በአካባቢያቸው የሚገኙ ስፍራዎችን እና ቴአትሮችን በማየት፣ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ማሳለፍ ሌላው የረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ሊሆን ይችላል፡፡
በአንፃሩ ግን ያለ ወላጅ ፈቃድ እና እውቅና ከቤት ርቆ ሄዶ መጫወት፣ የመኪና መንገድ ላይ መጫወት፣ ከአቅማቸው በላይ እና ያልተፈቀደላቸውን ተግባራት ማከናወን፣ ረጅም ጊዜ የስልክ እና የቴሌቪዢን ስክሪን ላይ ማሳለፍ ተገቢ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ወላጆችም ልጆቻቸው የእረፍት ጊዜያቸውን በፕሮግራም በአግባቡ እንዲጠቀሙና የረፍት ጊዜያቸው አይረሴ እንዲሆን የማድረግ እና የማገዝ ኃላፊነት አለባቸው ሲል ሬዚንግ ችልድረን ኔትዎርክ መረጃውን አጋርቷል፡፡
ተረት
ሁለቱ ጦጣዎች
ከብዙ ዓመታት በፊት ሁለት ጦጣዎች አብረው ይኖሩ ነበር:: ታዲያ አንድ ቀን ምግብ ፍለጋ ወጥተው የሚበሉት ነገር አገኙ:: ሆኖም በምግቡ ላይ መጣላት ጀመሩ:: ስለዚህ “ወደ አቶ ቀበሮ ዘንድ ሄደን እርሱ ይገላግለን” ብለው ወደ ቀበሮው ሄዱ:: ቀበሮውም ጉዳዩን በጥሞና ካዳመጠ በኋላ “ምግቡን ሁለት እኩል ቦታ ማካፈል ስላለብኝ ሚዛን መጠቀም አለብኝ:: ነገር ግን አሁን ሚዛን በእጄ የለም:: ዛሬ ጠዋት ሚዛኑን ለአቶ አንበሳ ስላዋስኩት ወደ አንበሳው ሄደን ምግቡን እንክፈለው” አለ::
እንደደረሱም ቀበሮው አንበሳውን ተጣርቶ ጉዳዩን ነገረው:: እንዲህም አለው “አንበሳ ሆይ! እነዚህን ጦጣዎች አስታርቃቸው”፤ ይህንንም ብሎ ቀበሮው ወደ አንበሳው ዋሻ ሳይገባ ተመልሶ ሄደ:: ጦጣዎቹም የተውትን ምግብ ቀበሮው አንስቶ ራሱ በላው::
ይህ በእንዲህ እንዳለም ሁለቱ ጦጣዎች ችግራቸውን ለአንበሳው መንገር ጀመሩ:: ነገር ግን አንበሳው እነርሱን መብላት አንጂ መዳኘት አልፈለገም ነበርና በላቸው::
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች
ሞክሩ
. ሁልጊዜ የሚመጣ ግን የማይደርስ?
- የሚፈርስ ግን የማይጠገን ምንድን ነው?
- በቁርስ ሰዓት በጭራሽ የማይበሉ ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው?
መልስ
- ነገ
- ቃል ኪዳን
3.ምሳ እና ራት
ነገር በምሳሌ
ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ
መልካም ነገር ማሰብ ጥሩ ነገር ያመጣል፡፡
ሐሰት ስለበዛ እውነት ሆነ ዋዛ
ሐሰተኛ በበዛበት እውነት እንደቀላል ተቆጥሮ ሐሰት ይሆናል::
-ማምሻም ዕድሜ ነው
ባለችው ጊዜ መጠቀም መልካም ነው::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


