ልፋቱ ፍሬ እንዲያፈራ …

0
164

የህዳር  16 ቀን 2017 ዓ.ም

ወቅቱ፦

“ተጓዘ ማልዶ ጥጋጥጉን፣

አጭዶ ሊከምር አዝመራውን!” የሚለው ኢትዮጵያዊ ብሂል በተግባር የሚታይበት ነው። ምክንያቱም አርሶ አደሩ የድካሙን ፍሬ የሚጨብጥበት ጊዜ ነውና። በአሁኑ ወቅት ታዲያ ፈጣሪውን አምኖ፣ ሰማዩ የሚለግሰውን ዝናብ ጠብቆ አርሶ፣ አለስልሶ፣ ዘርቶ፣ አርሞ፣ ኮትኩቶ፣ ከወፍ እና ከተባይ ጠብቆ… ለፍሬ ያደረሰውን ሰብል እየሰበሰበ ይገኛል። ሀገር መጋቢው አርሶ አደር ታዲያ በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ተቋቁሞ የልፋቱን ውጤት በእጁ ለማስገባት ሩጫ ላይ ነው።

አርሶ አደሩ ሩጫው እንዳይስተጓጎል፣ ሰብሉ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና መሰል ችግሮች ባክኖ እንዳይቀር እየሰበሰበ ነው። ለዚህ ደግሞ በደቦ (በወንፈል) መሰብሰብ አይነተኛ ዘዴ መሆኑን በመረዳት ተግባራዊ እያደረጉ እንደሚገኙ በስልክ ሐሳብ የሰጡን አርሶ አደሮች ነግረውናል።

ምርቱን ፈጥኖ ለመሰብሰብ እና በወቅቱ ወቅቶ ወደ ጎተራ ለማስገባትም የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በጋራ (በደቦ) እና የጉልበት ሠራተኛ በመቅጠር ሰብላቸውን እየሰበሰቡ መሆናቸውን የነገሩን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አበርገሌ ወረዳ 017 ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ኃይሌ በላይ ናቸው። አርሶ አደሩ እንደነገሩን በአካባቢው ማሽላ፣ ጤፍ፣ እንቁ ዳጉሳ፣ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ ኦቾሎኒ፣ በቆሎ እና አደንጓሬ በብዛት ይመረታል። በምርት ዘመኑም የተሻለ የግብዓት አቅርቦት እንደነበር ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ተጠቅመው መዝራታቸውን የነገሩን አርሶ አደሩ የተሻለ የሰብል ቁመና መኖሩንም አክለዋል። አርሶ አደር ኃይሌ በመኸር ወቅት ማሽላ፣ እንቁ ዳጉሳ፣ ጤፍ፣ ኦቾሎኒ እና ማሾ አዝምረዋል። ማሳውን በአግባቡ ሲንከባከቡ ከርመዋል። በዚህ ወቅትም የማሽላ ሰብላቸውን እንደሰበሰቡም ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ድርቁ ጉዳት አስከትሎ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ በዚህ ዓመት የተሻለ ምርት ይገኛል የሚል ተስፋ አላቸው። ሰብላቸውንም ወበራ (ሰብልን በጋራ መሰብሰብ) በተባለ ባሕላዊ የአሰባሰብ ዘዴ ተጠቅመው እየሰበሰቡ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በቀጣይም እየደረሱ ያሉ ቀሪ ሰብሎችን በጉልበት ሠራተኛ እና በደቦ ለመሰብሰብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላው አርሶ አደር ከአሁን በፊት የጤፍ ሰብላቸውን በደቦ (በወበራ እና በወንፈል) እንደሰበሰቡ የነገሩን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ አምበላ ቀበሌ ነዋሪው የሺዋስ ሳህሉ ናቸው። ስድስት ሄክታር በሚጠጋ መሬታቸው ጤፍ፣ በቆሎ፣ ዳጉሳ፣ ገብስ እና ሽንብራ መዝራታቸውንም ነግረውናል።

አርሶ አደር የሺዋስ በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት እና አለመረጋጋት የጉልበት ሠራተኛ እጥረት ገጥሞ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ ግን አንፃራዊ ሰላም በመፈጠሩ የጉልበት ሠራተኛ አግኝተው የደረሱ ሰብላቸውን መሰብሰብ መጀመራቸውን በስልክ ነግረውናል። በቀጣይ የደረሰውን የበቆሎ ሰብላቸውን በደቦ እና በጉልበት ሠራተኛ ለመሰብሰብ ተዘጋጅተዋል። ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰው ሰብላቸው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንደሚያደርጉም ነግረውናል። በተለይ ታጭዶ ከተከመረ በኋላ እንዳይበላሽ በሸራ ወይም በኘላስቲክ እንደሚሸፍኑት ነው ያስገነዘቡት። ከዚህ በተጨማሪም ሰብል በሚከመርበት ወቅት ከመሬት ከፍ ብሎ በቂ ነፋስ እንዲያገኝ፣ እርጥበት በማያስገባ መልኩ እንደሚከምሩ አክለዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2016/2017 የምርት ዘመን 120 ሺህ 638 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 118 ሺህ 657 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ከብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ከዚህም አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ምርታማነቱን ለማሳደግ 147 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ (ዩሪያ እና ዳፕ) ጥቅም ላይ ውሏል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ወልዴ ለበኩር በስልክ እንደገለፁት በዘር ከተሸፈነው ውስጥ 85 ሺህ 325 ሄክታር የሚሆነው ሰብል ተሰብስቧል። እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በአብዛኛው የቆላማ አካባቢዎች ቀድመው የደረሱ ሰብሎች ተሰብስበዋል። ማሾ፣ ሰሊጥ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ አተር እና እንቁ ዳጉሳ ከተሰበሰቡት ሰብሎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የአካባቢው ማኅበረሰብ  ምርትን በጋራ የመሰብሰብ  ባሕሉ የተጠናከረ መሆኑን ያነሱት አቶ አዲሱ የእርጥበት ጊዜው ሳያልፍ ለበጋ መስኖ ሥራ ለመዘጋጀት እንዲረዳ አርሶ አደሩ በተደራጀ መንገድ እየሰበሰበ መሆኑን ይናገራሉ።

በቀጣይም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል ምርት እንዳይባክን አርሶ አደሮች በወቅቱ፣ በጥራት እና በፍጥነት ሰብሉን  እንዲሰበስቡ አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ላይ ናቸው። የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው ለበኩር እንደተናገሩት በ2016/2017 ዓ.ም የምርት ዘመን 347 ሺህ 766 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ተሸፍኗል። 664 ሺህ 118 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ ውሏል። 14 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎም ይጠበቃል። በቆሎ በዋናነት እየተመረተ ያለ ሰብል ሲሆን 46 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው። በብሔረሰብ አስተዳደሩ በሁሉም አካባቢዎች የሚታየው የሰብል ቁመናም የተሻለ ነው።

ከ79 ሺህ 263 ሄክታር መሬት በላይ ሰብል ተሰብስቧል ያሉት አቶ አዲሱ፣ ገብስ እና ሰሊጥ ሙሉ ለሙሉ መሰብሰቡን አስታውቀዋል። በቆሎ፣ ማሾ፣ ቦሎቄ፣ ለውዝ፣ ጤፍ፣ አኩሪ አተር፣ ባቄላ፣ አተር እና ማሽላ እየተሰበሰቡ ያሉ ሰብሎች ናቸው። ምክትል ኃላፊው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብን ተከትሎ የሚከሰተውን የሰብል ምርት ብክነት ለመቀነስ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ እንዳለበት አሳስበዋል። ሰብሉ ከተሰበሰበ በኋላ በወቅቱ  መውቃት ባይችል እንኳ እርጥበት እንዳይገባው ከፍ አድርጎ መከመር እና ፕላስቲክ (ሸራ) ማልበስም ይገባል።

በተያዘው የምርት ዘመን በአማራ ክልል የሰብል አያያዙ በጥሩ ቁመና ላይ ነው ተብሏል። ከፍተኛ የምርት አቅም ያለው ክልሉ ምርት እና ምርታማነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱም ተመላክቷል። በክልሉ እስካሁን በሰብል ከተሸፈነው መሬት ከሁለት ሚሊዮን  ሄክታር በላይ የሚሆነው ተሰብስቧል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ለአሚኮ እንደተናገሩት በክልሉ አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።

“በክልሉ ያለው የሰብል ግምገማ ያቀድነውን ዕቅድ  ማሳካት እንደምንችል የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

የድኅረ ምርት ብክነት እንዳይኖር ሜካናይዜሽንን መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፣ አርሶ አደሮች ገንዘብ ቆጥበው የሰብል መሰብሰቢያ ማሽን (ኮምባይነር) እየጠየቁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የአርሶ አደሮችን ፍላጎት ለማሟላት እየተሠራ ነው ብለዋል። አርሶ አደሮች የደረሰ ሰብላቸውን በፍጥነት እንዲሰበስቡም ጥሪ አቅርበዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here