በደቡብ ኢትዮጵያ ሲዳማ ክልል አባያ ወረዳ ይገኛል፤ ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ:: ብሔራዊ ፓርኩ ከሀዋሳ 68 ከአዲስ አበባ ደግሞ 343 ኪሎ ሜትር ይርቃል።
በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚካተተው ፓርኩ በ2000 ዓ.ም ሲከለል 500 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል:: በመልካምድራዊ አቀማመጡ ኮረብታማ፣ የሳር ሜዳ፣ ረግረጋማ፣ ገደላማ፣ ሐይቅ፣ የወንዝ ዳርቻ፣ ደንና ሸለቆዎችን ያካተተ ነው::
የፓርኩ ክልል ዝቅተኛው ሻላ ኦዳ ከመሬት ወለል አንድ ሺህ 178 ሜትር ከፍታ፣ ከፍተኛው የጉዳኖ ኮረብታ አንድ ሺህ 650 ሜትር ተለክቷል::
በፓርኩ 198 የእጽዋት ዝርያዎች ተመዝግበዋል::
የፓርኩ ክልል በረሀማ እና ወይና ደጋ የዓየር ንብረት አለው፤ አማካይ የሙቀት መጠኑ 16 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ተለክቷል:: ሁለት የዝናብ ወቅቶች አሉት። ወራቶቹም የመጀመሪያው ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዚያ ወር መጨረሻ፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሀምሌ እስከ ጥቅምት ናቸው።
ዓመታዊ የዝናብ መጠኑ ዝቅተኛው 374 ፤ ከፍተኛ 1 ሺህ 194 ሚሊ ሜትር ሲሆን ከ2004 እስከ 2017 እ.አ.አ አማካይ የዝናብ መጠን 846 ሚሊ ሜትር ተለክቷል::
በፓርኩ ውስጥ ለሚገኝ ብዝሃ ህይወት የአባያ ኃይቅ እና የብላቴ ወንዝ ዋነኛ መሠረት ናቸው:: በፓርኩ ክልል በ28 መካከለኛ እና ትልልቅ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ውስጥ የሚካተቱ በቁጥር 2 ሺህ 573 እንደተጠለሉ ተለይቷል:: ከተጠቀሱት 28 ዝርያዎች የአፍሪካ የዱር ውሻ፣ ነብር እና ጉማሬ ሊጠፉ ከተቃረቡት ውስጥ እንደሚካተቱ በድረ ገጹ ተመላክቷል::
በፓርኩ ክልል ተበራክተው ወይም በቁጥር ላቅ ብለው ከሚገኙ የዱር አንስሳት ዝንጀሮ እና የሜዳ ፍየል በቅደም ተከተል ተጠቅሰዋል::
በመረጃ ምንጭነት ሪሰርች ጌት እና ቪዚት ሲዳማ ድረገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም