ሕልሙን የኖረው የፈጠራ ሰው

0
20

መምህር አሥራት ታደሰ ይባላሉ። በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ (ምሕንድስና) እና ‘ቴክኒካል ድሮዊንግ’ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቅ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ በሚገኘው የአምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መመህር ናቸው። 11 ዓመታትን በማስተማር አሳልፈዋል። እያስተማሩም ይገኛል።

ትምህርትን በተግባር አስደግፎ መስጠት መገለጫቸው እንደሆነ በቅርብ የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ፤ ይህም ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት አቀባበል እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ እርሳቸውንም ወደ ፈጠራ ሥራ አስገብቷቸዋል።

መምህር አሥራት የልጅነት ራዕይ ወይም ፍላጎት አንድ ሰው መድረስ ለሚፈልግበት የሕይወት ግብ መሠረት ነው ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ራሳቸውን አብነት አድርገዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን ሠርተዋልና ነው። በፈጠራ ሥራቸውም በተለያዩ ውድድሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

ኢንጅነር (መሐንዲስ) የመሆን ፍላጎት እንደነበራቸው የሚናገሩት መምህሩ፤ ከበርካታ የምሕንድስና ዘርፎች መካከል አውቶሞቲቭ ቀዳሚ ምርጫቸው ነበር። እስካሁን የሠሯቸው ሥራዎችም የልጅነት ህልማቸው እውን እንዲሆን በር የከፈቱ ሆነዋል።

“መምህርነት ትውልድ የመቅረጽ፣ ወደ ትክክለኛው መንገድ የማስገባት ኃላፊነት ነው“ ያሉት መምህሩ፣ እርሳቸውም ሥራ ፈጣሪ ትውልድን ለማፍራት በተግባር የታገዘ ትምህርትን ለመከተል የፈጠራ ሥራ እንደጀመሩ አስታውሰዋል።

መምህሩ እንዳሉት የሙያ ትምህርቶችን በተግባር አስደግፎ በማስተማር የትምህርቱን አይረሴነት ለማረጋገጥ እና ሥራ ፈጣሪ ትውልድን ለማበረታታት የፈጠራ ሥራዎች ትልቅ እቅም አላቸው። ምክንያቱም ተማሪዎች ከሚሰሙት ይልቅ ያዩትን ነገር በተግባር ልምምድ ታግዘው ሲማሩ ብቁ እና ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉና ነው፤ በፈጠራ ሥራቸውም የላቁ ሆነው ከራሳቸው አልፈው ዓለምን ይቀይራሉ።

በዓለም ላይ ዛሬ በቴክኖሎጂ እና በሌሎችም ዘርፎች ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ሀገራት መሠረታቸው የፈጠራ ሥራዎች ናቸው። ጥናትና ምርምሮቻቸው በመደርደሪያ (ሼልፍ) ላይ ሳይቀሩ ወደ ተግባር መለወጣቸው ደግሞ ለግብ እንዳበቃቸው ነው ቴክኖሎጂ ዶት ኦርግ ላይ ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው፤ መምህሩ ያጠናከሩልንም ይህንኑ ሐሳብ ነው።

በእኛም ሀገር ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በሚል በርካታ ጥናቶች ይሠራሉ። ተማሪዎች ለመመረቂያ የሚያቀርቧቸው የማሟያ ጽሑፎች ደግሞ ለዚህ በአብነት ይጠቀሳሉ፤ ነገር ግን ለመመረቂያ ከማሟያነት በዘለለ የማኅበረሰብ ችግርን ለመፍታት ወደ መሬት አይወርዱም።

መሰል ችግሮችን በተደጋጋሚ እንደሚታዘቡ ሐሳባቸውን ያካፈሉን መምህሩ ይህም ችግር እርሳቸውን ወደ ፈጠራ እንዲገቡ ዋናው ገፊ ምክንያት እንደሆናቸው ጠቁመዋል።

መምህር አሥራት ባለፉት የመምህርነት ዓመታት በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን አስተዋውቀዋል። እስካሁንም በክልል ደረጃ በተዘጋጀ የዕውቅና መርሀ ግብር አምስት ጊዜ  ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። በዚህም አምስት የተለያዩ ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን ነው ያስተዋወቁት። መምህሩ እስካሁን ካስተዋወቋቸው የፈጠራ ሥራዎች መካከል ከተለያዩ እፅዋት የተቀመመ ፈሳሽ ሽቶ፣ ከከብቶች ፅዳጅ እና ከሽንት ቤት የመነጨ ሚቴን ጋዝ፣ የወተት መግፊያ ወይም መናጫ ማሽን፣ ከተለያዩ እፅዋት የእስክብሪቶ ቀለም እና የፓርከር ቀለም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅትም ለራሳቸው አምስተኛ የፈጠራ ሥራ የሆነውን ሁለገብ የሽመና ክር ማቅለሚያ እና ማጠንጠኛ ማሽን አስተዋውቀዋል፡፡ “የዓለም ሳይንስ ቀን ለሰላምና ልማት” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲካሄድ በቆየው 10ኛው ሀገር አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የፈጠራ ሥራ ውድድር እና አውደ ርዕይ ላይ ተሳታፊ በመሆን ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የጨርቃ ጨርቅ /ቴክስታይል/ ዘርፉን ለማዘመን ታሳቢ ተደርጎ የተጀመረ እንደሆነም ነግረውናል፡፡ ለዚህ የፈጠራ ሥራው መነሻው ደግሞ የሀገርን ባሕል የሚያስጠብቁት የሽመና ሰሪዎች እየደረሰባቸው ያለው ዓለም አቀፍ አፍራሽ ተጽዕኖ ነው።

በዚህ ዘመን የባሕል አልባሳት ትንሳዔ የተመለሰ ይመስላል፤ በበዓላት ብቻ ሳይሆን በትልልቅ የአደባባይ ዝግጅቶች ሁሉ የሀገር ቤት የባሕል አልባሳት እየደመቁ ነው።

ልብስ ከውበት እና ከመሠረታዊ ፍላጎትነቱ ባለፈ የማንነት መገለጫም ጭምር ነው። የኢትዮጵያዊ ማንነት እና የባሕል መገለጫ የሆኑ ሀገርኛ አልባሳት አሁን ካለበት ይበልጥ እንዲሰፋ ማድረግ የሚለው ሐሳብ ደግሞ ለመምህር አሥራት የፈጠራ ሥራ ተጨማሪ መነሻ ሆኗቸዋል። ሀገራችን በጥጥ እና በሌሎች የፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎች ግብዓት ሰፊ ሀብት ቢኖራትም ዕሴት ሳትጨምር ለውጭ ገበያ ማቅረቧ እና በኋላም በእኛው ጥሬ ዕቃ የተሠሩ ምርቶችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገባቷም ሌላው እልህ የፈጠረባቸው ገፊ ምክንያት ነው።

ይህንኑ የፈጠራ ሥራቸውን በሽመና ሥራ የሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ መጀመራቸውን ያስታውሳሉ። በዚህም አሠራሩ ባለመዘመኑ ምክንያት አድካሚ፣ ለማምረት የሚወስደው ጊዜ ረዥም እና የሚያስገኘው ገቢም ዝቅተኛ መሆኑን ታዝበዋል።

በተመሳሳይ በርካቶች መማርን ተቀጥሮ ለመሥራት እንደ ብቸኛ መንገድ ሲቆጥሩት በመታዘባቸው ይህን አመለካከት ለመቀየር ወደ ፈጠራ ሥራ እንደገቡ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በተለይ በምሕንድስና ትምህርት የሚገኝ ዕውቀት በተግባር የሚገለጥ የሕይወት ዘመን ሙያ ነው፤ ይሁን እንጂ በዘርፉ የተመረቁ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ተቀጣሪነትን ብቻ ጠባቂ ናቸው፡፡ መምህር አሥራት ደግሞ ይህን የተዛባ አተያይ መቀየርን አለሙ፤ ሐሳቡም ለፈጠራ ሥራቸው ተጨማሪ አቅም ሆናቸው።

“መምህራን ዕውቀት ለጋሽ ብቻ ሳይሆኑ የዳቦ ምንጭም መሆን አለባቸው” ያሉት መምህሩ፣ መምህራን የሚያስተምሩት ተቀጥሮ መሥራትን ብቻ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪነትን ከፍ በሚያደርግ አግባብ ሊሆን እንደሚገባ መክረዋል።

የፈጠራ ሥራውን (ፕሮጀክቱን) ይዘው ከወረዳ እስከ ፌደራል በሄዱበት ወቅት የተሰጣቸው ግብረ መልስ ጅምራቸውን ከዳር ለማድረስ ጉልበት እንደሆናቸው ነው የጠቆሙት። ፕሮጀክቱን ወደ ምርት በማሸጋገር የሥራ ዕድል መፍጠር ደግሞ ግባቸው መሆኑን አክለዋል።

በየጊዜው የሚያስተዋውቃቸው የፈጠራ ሥራዎች አሁን ለደረሰበት የፈጠራ ሥራ ስኬት እንዳበቃቸው ተናግረዋል።

መምህሩ እንዳሉት የተሠራው ማሽን በፋብሪካ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ እና በአንድ ጊዜ አራት ሥራዎችን ያከናውናል፤ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ጥጥ መፍተልን ጨምሮ የመጠምጠም እና የክር ማዳወር ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ይህም በአንዴ የአራት ሰዎችን ጉልበት የሚተካ ነው፤ በአሁኑ ወቅትም በሥራ ላይ ይገኛል።

ማሽኑ በተለያዩ የኃይል ምንጮች (በፀሐይ ብርሐን (ሶላር)፣ በሰው እና በኤሌክትሪክ ኃይል) እንዲሠራ ተደርጎ መሠራቱን የፈጠራ ባለቤቱ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ማሽኖችን በማብዛት የሥራ ዕድልን  ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጓል፤ በተጨማሪም የማሽኑን ሥሪት በተሻሉ መሣሪያዎች የመተካት ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።

አብዛኛው ሰው የፈጠራ ሥራ ላይ መሠማራት ይፈልጋል፤ የፈጠራ ሥራ ግብዓት እጥረት ግን ትልቅ ፈተና መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ለሀገር ብዙ ነገር ማበርከት የሚችሉ ብዙ አቅም ያላቸው ወጣቶች እንዳት ያነሱት መምህሩ፣ በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን አስፈላጊ ግብዓቶችን ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዘመኑ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ሀገራት እሽቅድምድም የገቡበት ነው የሚሉት መምህሩ፣ ኢትዮጵያም ለዘርፉ ትኩረት ልትሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ትምህርት ቤቶች ፈጠራን እንዲያበረታቱ ማገዝ፣ የሚመለከታቸውም አካላት ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች እንዲተዋወቁ በግብዓት እና በማበረታቻ የበኩላቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል። ከዕውቅና መድረክ በኋላ የተመረጡ የፈጠራ ሥራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው የማኅበረሰብ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ መከታተል፣ መደገፍ እና ማገዝ እንደሚገባም ጠይቀዋል። የትምህርት ተቋማት ከወቅታዊ ዕውቅና ባሻገር ተጨማሪ ፈጠራዎች እንዲተዋወቁ የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩም ነው ያነሱት።

የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በአሁኑ ወቅት መንግሥት ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ የገንዘብ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ማቋቋሙን፣ በርካታ የቴክኖሎጂ መፈልፈያ ማዕከላትን ማቋቋሙን፣ የፈጠራ ባለቤቶችን ከገበያ ጋር የማስተሳሰር እና ከታክስ እና መሰል ግዴታዎች ነጻ የሚሆኑበት የእፎይታ ጊዜ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ተማሪዎችና መምህራን ምቹ ሁኔታ መኖሩን አውቀው ተሰጥኦዋቸውን እንዲያወጡ ጠይቀዋል።

በመምህራን እና በተማሪዎች የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎች ራሳቸውንም ሆነ ሀገርን ወደሚጠቅሙበት ደረጃ እንዲደርሱ ጠንክረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው በማንሳት መሥሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን መግለጻቸውን ከኢትዮጵታ ትምህርት ሚኒስቴት ማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

ግእዝ በአማርኛ

  • እነዚህ ሞክሼ ፊደላት አንዱ በአንዱ ቦታ መግባት የለበትም፤ ምክንያቱም የትርጉም ለውጥ ያመጣሉ።
    ለምሳሌ፡- ፦
    ሠረቀ-ወጣ
  • ሰረቀ-ሰረቀ
  • አመት- አገልጋይ
  • ዓመት- ዘመን
  • ሰዐለ- ስዕል ሳለ
  • መሀረ – አስተማረ
  • መሐረ – ይቅር አለ
  • ኀለየ – አመሰገነ
  • ሐለየ – አሰበ
  • ፈጸመ – ጨረሰ
  • ፈፀመ -ነጨ
  • ማኅሌት – ማመስገን
  • ማሕሌት – ማሰብ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here