የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልሉ ሕዝብ ራሱን ከኤም ፖክስ በሽታ ሊጠብቅ እንደሚገባ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ከሰሞኑ የኤምፖክስ በሽታን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በሽታው አማራ ክልል ተከስቷል፡፡ በክልሉ እስካሁን በበሽታው ተጠርጥረው ናሙና የተሠራላቸው ሁለት ሰዎችም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች በምዕራብ ጎንደር መተማ እና በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ናቸው፡፡
ግለሰቦቹ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ከበሽታው መዳናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከነሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎችም በተደረገላቸው ምርመራ ኤምፖክስ እንደሌለባቸው መረጋገጡን ነው ያስታወቁት፡፡
አቶ በላይ እንደገለጹት ኤምፖክስ በቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፍ ገዳይ በሽታ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የዓለም የጤና ድርጅት 2016 ዓ.ም መገባደጃ ላይ ትኩረት የሚሹ የሕብረተሰብ ጤና ሥጋት አደጋዎች ሲል ኤም ፖክስን ፈርጇል፡፡ የኤም ፖክስ በሽታ ዋነኛ የመተላለፊያ መንገዶች በበሽታው ከታመመ ሰው ጋር በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ንክኪ ሲኖር ነው፡፡
በቀጥታ ንክኪ በማድረግ ማለት የኤም ፖክስ ካለበት ሰው ጋር በመሳሳም፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ የእጅ ንክኪ እና ጡት ማጥባትን ያካተተ ነው። ቀጥታ ባልሆነ ንክኪ ደግሞ ኤምፖክስ የተያዘ ሰው የሚጠቀምባቸውን ቁሳቁሶች በጋራ መጠቀም በሽታው እንዲተላለፍ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም በኤም ፖክስ የተያዘ ሰው ሲያስነጥስ ቫይረሱ በአየር አማካኝነት ይተላለፋል ነው ያሉት። በቂ መረጃ ባይኖርም ከእንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፍ እንደሚችልም ነው የጠቆሙት፡፡
አንድ ሰው ቫይረሱ ወደ ሰውነቱ ከገባ ከአምስት እስከ 21 ቀን ድረስ ምልክቶቹን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ዋና ዋና ምልክቶቹም የመጀመሪያው ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የጀርባ እና የጡንቻ ሕመም፣ የሰውነት ዕጢዎች እብጠት፣ ጎላ ጎላ ያሉ ሽፍታዎች በሰውነት ቆዳ ላይ መውጣት፣ እንዲሁም ጠንከር እያለ ሲሄድ ለመተንፈስ መቸገር እና የድካም ስሜት ሲሆኑ እነዚህ ምልክቶች ትኩሳቱ ከጀመረበት ከአንድ አስከ ሦስት ባሉት ቀናት ውስጥ ይታያሉ፡፡ ሽፍታው እግር ላይ ሊታይ እንደሚችልም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
እንደ አቶ በዛብህ ገለጻ ኤምፖክስን ለመከላከል ዋናው ነገር ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ንኪኪዎችን ማስወገድ ነው፡፡ ንክኪ ከተፈጠረ ደግሞ እጅን በአግባቡ በሳሙና እና በውኃ መታጠብ ያስፈልጋል፡፡ የመገልገያ ዕቃዎችንም በጋራ አለመጠቀም፣ የእንስሳት ተዋጾዎችንም በደንብ አብስሎ መመገብ ይገባል፡፡ ምልክቶችን ያሳየ ሰው በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ መታከም ይኖርበታል፡፡ አሁን ላይ ምርመራው በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በብሔራዊ ላቦራቶሪ (ቤተ ሙከራ) እየተከናዎነ ይገኛል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በሽታውን በተመለከተ በፌዴራል እና በክልል ደረጃ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ለጤና ባለሙያዎች ስለበሽታው አጠቃላይ ሁኔታ ሥልጠና ተሰጥቷል፤ ከዞን እስከ ቀበሌ በተዋረድ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ አስፈላጊው ሥራ እየተሠራ በመሆኑ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ አይወጣም ነው ያሉት፡፡
ሕብረተሰቡ ከተሳሳተ መረጃ ራሱን እንዲጠብቅ እና ማንኛውም ግለሰብ ስለ ኤም ፖክስ በሽታ ለማወቅ ከፈለገ መረጃዎችን ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጰያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባወጣው መግለጫ ደግሞ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ (ሰኔ 06ቀን 2017 ዓ.ም) ድረስ በኤምፖክስ ከተገኘባቸው 18 ሰዎች መካከል አምስቱ ሲያገግሙ የአንድ ሰው ሕይዎት አልፏል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም