የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልሉ ሕዝብ ከዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ራሱን እንዲጠበቅ የሚያስችለውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) የተያዙ ሁለት ሰዎች መገኘታቸውን ተክትሎ የፌደራል ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሽታው ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ይፋ አድርገዋል፡፡
የተለመዱ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምልክቶች ውኃ የቋጠሩ ሽፍታዎች በብዛት በእጅ መዳፍ እና በውስጥ እግር ላይ ይወጣሉ፡፡
በመቀጠልም በመላው የሰውነት ክፍል መታየት ይጀምራሉ፡፡ በሽታው ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ሕመም፣ የንፍፊት (ሊምፍ ኖዶች) እብጠት እና የአቅም መቀነስ ምልክቶችን ያሳያል ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በዋናነት ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ የቅርብ ግንኙነት ሲኖር ነው፡፡ በንክኪ፣ በግብረ ስጋ ግንኙነት፣ በመሳሳም እና በትንፋሽ ይተላለፋል፡፡ በእርግዝና ወይም በወሊድ ጊዜም ቫይረሱ ወደ ሕፃኑ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ በእርግዝና ወቅት የጽንስ መቋረጥ እና አዲስ በተወለደ ሕጻንም አደገኛ እና ሞትን ሊያስከትል እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡ በእናትየውም ላይ ውስብስብ ችግሮች ሊፈጥር እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡
የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ማሕበረሰቡ የበሽታው ምልክቶች ሲታዩበት አቅራቢያው በሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ መታየት እንደሚኖርበት ነው ያሳሰበው፡፡ ሕብረተሰቡ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ላይ የነበረው ጥንቃቄ እንዳይለየው ነው የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ያስታወቁት፡፡
የጤናው መዋቅርም የዝንጀሮ ፈንጠጣ ምልክቶች የታየበት ሰው ወደ ጤና ተቋማቸው ለሕክምና ከመጣ ለሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ሪፖርት እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
እ.አ.አ. በ2022 እና በ2023 ዓለም አቀፍ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ የተከሰተ ሲሆን ዛሬም ስጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ቫይረሱ በስፋት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሰራጭቶ እንደሚገኝ ነው የዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቀው፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በበሽታው ከተያዙ እንስሳት ወደ ሰው በንክሻ፣ በመቧጨር፣ እንስሳትን በማጥመድ፣ የሞቱ እንስሳት ቆዳን በመጠቀም፣ የሞቱ የእንስሳት አስከሬን በመንካት ወይም እንስሳትን አድኖ በመመገብ ምክንያቶች ሊተላለፍ ይችላል።
በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ብዙዎች ሙሉ በሙሉ ይድናሉ፤ ነገር ግን አንዳንዶቹ በሽታው በጣም እንደሚጠናባቸው ነው የዓለም ጤና ድርጅት ላይ ያገኘነው መረጃ የሚያትተው፡፡ እ.አ.አ ከጥር 2022 እስከ ነሐሴ 2024 መካከል ከ120 በላይ ሀገራት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ እንደተከሰተባቸው ሪፖርት አድርገዋል። ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችም በቤተ ሙከራ በሽታው እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከተረጋገጡት መካከልም ከ220 በላይ የሚሆኑት ሞተዋል።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም