ሕክምና ፈላጊዉ አፈር

0
200

የሰብል ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል የአፈር አሲዳማነት አንዱ ነው። በኢትዮጵያ የአፈር አሲዳማነት የሚያጠቃቸው ከፍተኛ አምራች በሆኑ አካባቢዎች መሆኑ ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል።

የአፈር አሲዳማነት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ  በመምጣቱ አፋጣኝ መፍትሄ እና ትኩረት ካልተሰጠው በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል የዘርፉ ምሁራን  ሐሳባቸውን በተለያዩ ጊዚያት አጋርተዋል።

የአፈር አሲዳማነት በተለያዩ የሀገራችን ክፍል የአፈርን ለምነት እየጎዳው ይገኛል። መሬቱንም ከምርት ውጪ እያደረገው ነው። ለግብርና ሥራ ትልቅ ግብዓት በሆነው አፈር ላይ የሚያጋጥመው የአፈር አሲዳማነት እና ጨዋማነት በምርታማነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታዲያ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግሥት ለችግሩ መፍትሄ የሚሆኑ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ሆኖም ካለው የችግሩ ስፋት እና አሳሳቢነት አኳያ ፈጣን እርምጃ እና የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል።

በአማራ ክልል በዘር ከተሸፈነው አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 601 ሺህ ሄክታር መሬት በከፍተኛ እና አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር በመካከለኛ አሲዳማነት የተጠቃ  ነው፡፡ በአጠቃላይ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአሲዳማነት እንደተጠቃ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በግብርናው ዘርፍ በትርፍ አምራችነቱ የሚታወቀው አማራ ክልል በምርታማነቱ እንዳይቀጥል ከገጠሙት እንቅፋቶች መካከል የአፈር አሲዳማነት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። ይሁን እንጂ ችግሩን ለመከላከል አጥጋቢ ሥራ እንዳልተሠራ መረጃዎች ያመለክታሉ። የአፈር አሲዳማነት ከተስፋፋባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል ሰሜን፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ፣ ማዕከላዊ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች እንዲሁም የምሥራቅ አማራ ዞኖች በከፊል ለአፈር አሲዳማነት የተጋለጡ እንደሆኑ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

የአፈር አሲዳማነት በስፋት ከተስፋፋባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ ሳንኪት ልደታ ቀበሌ ነዋሪው  ቄስ ዜናው ወርቁ የግብርና ሥራቸውን በተመለከተ ለበኩር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል፤ በመሬታቸው የአፈር አሲዳማነት በመከሰቱ ከምርት ውጪ አድርጓቸው እንደነበር አስታውሰዋል። በባለሙያ ከመሬታቸው የአፈር ናሙና ተወስዶ ካስመረመሩ በኋላ የአፈር አሲዳማነት በመገኘቱ በኖራ ማከም እንደጀመሩ ነግረውናል። ኖራን ከ2011 ዓ.ም ጀምረው መጠቀማቸውን አስረድተዋል።

የአፈር አሲዳማነት ችግሩ አሳሳቢ እንደነበር የተናገሩት ቄስ ዜናው በኖራ ከታከመ በኋላ ግን ምርታማነቱ እንደተሻሻለ ገልፀዋል። በኖራ የታከመው መሬት ለሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ ምርት እንደሚሰጥ አመላክተዋል። በኖራ በማከም እያመረቱ እንደሚገኙ በማንሳት   ለዚህ ዓመትም አምስት ኩንታል ኖራ ለመግዛት ተዘጋጅተዋል። አሲዳማውን አፈር በኖራ ለማከም ደግሞ የባለ ሙያ ምክረ ሀሳብ በመቀበል በአግባቡ እና በጥንቃቄ እንደሚቀላቅሉ አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ እንደነገሩን በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት ምርት ካለመስጠትም ባሻገር ለከብት ግጦሽ የሚሆን ሳር እንኳን አያበቅልም። በመሆኑም አርሶ አደሮች በአሲዳማነት የሚጠረጠር መሬታቸውን የአፈር ናሙና በማስወሰድ የአፈሩ ጤንነት እንዲታይ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የሚመለከተው አካል ደግሞ በቂ ኖራ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ይገባዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩ የአሲዳማ አፈርን ሊከላከሉ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን (ኮምፖስት ማዘጋጀት፣ አፈራርቆ መዝራት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ) ማከናወን እንዳለበት መክረዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንዳስታወቁት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከጃዊ ወረዳ በስተቀር በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች መጠኑ ቢለያይም የአፈር አሲዳማነት ችግር ተከስቷል። ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱንም አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅትም የአፈር ናሙና እየተወሰደ የመለየት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ምክትል ኃላፊው እንዳሉት ከ7 ሺህ 620 ሄክታር መሬት ላይ የአፈር ናሙና ተወስዶ ወደ አፈር ላብራቶሪ ተልኳል። በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከሚታረሰው 347 ሺህ 766 ሄክታር መሬት ውስጥ 159 ሺህ 620 ሄክታሩ በአሲዳማ የተጠቃ መሆኑ ተረጋግጧል። በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል እና ጉዳቱን ለመቀነስ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ አመላክተዋል። በበጀት ዓመቱ አንድ ሺህ 524 ሄክታር መሬት በኖራ ለማከም በዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የኖራ እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አዲሱ በዚህ ዓመት በወቅቱ እና  በታሰበው ልክ እንዲቀርብ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። ኖራን በእርሻ ወቅት የዝናብ እና የእርጥበት መጠኑ ሳይበዛ በተገቢው መንገድ መጥኖ መጨመር እንደሚገባ መክረዋል። በዘር ወቅትም የባለሙያ ምክረ ሀሳብ በመቀበል ኖራን ከአፈር ማቀላቀል ይጠበቅበታል።

ምክትል ኃላፊው እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል እና ምርታማነትን ለማሳደግ 45 ሺህ 720 ኩንታል ኖራ ለመጠቀም ታቅዷል። ከዚህ በተጨማሪም የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በመጠቀም የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል እየሠራ ነው።

የአፈር አሲዳማነት እንዲከሰት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት በዋናነት ከፍተኛ የሆነ የዝናብ ሥርጭት መኖሩ ነው ፤ ይህ ሲሆን ደግሞ በአፈር ውስጥ የሚገኙ እንደ ማግኒዚየም፣ ካልሺየም፣ ሶዲየም እና ፖታሺየም የመሳሰሉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች በጎርፍ ስለሚታጠቡ ችግሩ ይፈጠራል፤ ከዚህ በተጨማሪም በተደጋጋሚ ወይም ለረዥም ዓመታት መሬቱ መታረሱ፣ በተደጋጋሚ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የባለ ሙያ ምክረ ሀሳብ ሳይቀበሉ ከመጠን በላይ መጠቀም፣ የአፈር እና የውኃ ጥበቃ ሥራ በተገቢው አለመሠራቱ፣ መሬትን በአግባቡ አለመጠበቅ፣ የተፈጥሮ  ማዳበሪያን በትኩረት አለመጠቀም፣ አርሶ አደሩ የሰብል ተረፈ ምርትን ከማሳው ሙሉ በሙሉ ማንሳት እና የመሬት ጥበቃ ሥራ አለመሠራት አፈር በአሲድ እንዲጠቃ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

ችግሩን ለመከላከል ታዲያ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም፣ በኖራ ማከም፣ የአፈር አሲዳማነትን ሊቋቋሙ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን መጠቀም እና ሌሎች የአፈሩን ጤንነት ሊመልሱ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን ይገባል ብለዋል።

በተመሳሳይ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተመላክቷል። የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንዳብራሩት ከሚታረሰው 612 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 150 ሺህ ሄክታሩ በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ ነው።

እንደ አቶ አበበ ማብራሪያ በ129 ቀበሌዎች ናሙና ተወስዶ የአፈር አሲዳማነትን የመለየት ተግባር ተከናውኗል። 61 ሺህ 440 ኩንታል ኖራ ለማቅረብም ታቅዷል። የተገዛውን ኖራ ለማጓጓዝ ደግሞ የጨረታ ሥራ ተሠርቷል።

የአፈር አሲዳማን በኖራ ከማከም ባሻገር የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም፣ ሰብልን በፈረቃ መዝራት (በተለይ የጥራጥሬ ሰብሎችን)፣ አሲዳማ አፈርን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎችን መጠቀም፣ በመሬቱ ላይ የሰብል ገለባን በሙሉ አለማንሳት፣ አርሶ አደሩ የመሬቱን ጤናማነት የግብርና ባለሙያን በማማከር ማስመርመር እና የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ማከናወን ይገባል። አሲዳማ አፈርን በኖራ ከማከም ጎን ለጎን  የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም ይገባል።

በሌላ በኩል አርሶ አደሩ አሲዳማ አፈርን ሳያክም የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የሚጠቀም ከሆነ የአሲዳማነት መጠኑን ይጨምራል ወይም ያባብሰዋል። በመሆኑም እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ማግኘት የሚገባንን ምርት እንዳናጣ እንዲሁም በአሲዳማ አፈር ምክንያት የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ ማኅበረሰቡ የአፈር እንክብካቤ እና ጥበቃ ሥራ ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

የአፈር አሲዳማነት ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቶ በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አቶ አጠቃ አይቸው ተናግረዋል። ለአፈር አሲዳማነት መከሰት ዋናው ምክንያትም ለመሬት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን አንዱ ነው። የአፈር አሲዳማነት ጠቃሚ የሆኑ በአፈር ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ሲታጡ የሚፈጠር ችግር እንደሆነም አመላክተዋል።

ችግሩን ለመከላከል ታዲያ አርሶ አደሩን በማሳተፍ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል። በ2017/2018 የምርት ዘመን በትኩረት ለመሥራት መታቀዱንም ባለሙያው አስረድተዋል። ለግብርና ሥራ ዋናው ግብዓት በሆነው አፈር ላይ ልክ እንደ ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ትኩረት እንደሚሰጠው ሁሉ ለአፈር አሲዳማነትም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል። የኖራ ማምረቻ ፋብሪካዎችን በማስፋፋት እና የተጀመሩ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም ሥራ እንዲጀምሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። ለዚህም ከፍተኛ ርብርብን ይጠይቃል ነው ያሉት።

በተያዘው በጀት ዓመት በአማራ ክልል ከ12 ሺህ እስከ 18 ሺህ ሄክታር መሬት በኖራ ማከም የሚያስችል 370 ሺህ 800 ኩንታል ኖራ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ለበኩር ጋዜጣ ገልፀዋል። ይህን ዕቅድ ለማሳካትም 500 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ጨረታ ወጥቶ የኖራ ግዥ እየተፈፀመ ነው።

አቶ አጠቃ አክለውም በአሲዳማነት የተጠቃን አፈር የተለያዩ  ዘዴዎችን በመተግበር ለምነቱን መመለስ ካልተቻለ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል።

በመሆኑም የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል በኖራ ማከም፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ማዘጋጀት፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ጨምሮ ሌሎች ዘዴዎችን መተግበር እንደሚገባም አሳስበዋል። የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት እና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በመሥራት የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ እና አሲዳማነትን ለመከላከል እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የታኅሳስ 21  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here