ሕዝቡ ግድቡን እንዴት ገለጸው?

0
67

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ14 ዓመታት የግንባታ ጊዜያት በኋላ ተጠናቆ ጳጉሜ 04 ቀን 2017 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ ይህን በማስመልከትም በመላ ሀገሪቱ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡ በአማራ ክልል መስከረም 06 ቀን 2018 ዓ.ም የድጋፍ ሰልፉ ተካሂዷል፡፡

ሮዛ ጌታቸው በሰልፉ ላይ የተገኘችው ግድቡ በርካታ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎችን አልፎ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታዋን ለመግለጽ መሆኑን ተናግራለች፡፡ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ የምትለው ሮዛ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የክፍል ተማሪዎችን በማስተባበር አሻራዋን እንዳሳረፈች ተናግራለች፡፡ በአጠቃላይ ግድቡ የሁሉም አሻራ ውጤት ነው ብላለች፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊነትን ያቀነቀንንበት፣ ከፍታችንን ያረጋገጥንበት፣ የኢትዮጵያን መልማት የማይፈልጉ ሀገራትን በአንድነት ያሸነፍንበት ነው ስትል ተናግራለች፡፡

ግድቡ ዳግማዊ ዓድዋ መባሉ ተገቢ ነው ያለችው ሮዛ ለዚህም በዓድዋ ከፍ ያለው ታላቅነታችን ዛሬም ልማቱን ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ ግድብ በመገንባቱ ነው ስትልም በምክንያትነት አንስታለች፡፡ “አይችሉምን ችለን አሳይተናል፣ የዓደዋውን አንድነታችን ዛሬም ሕያው ሆኖ እንዳለ በሕዳሴው ግድብ ለዓለም አረጋግጠናል” ነው ያለችው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ብቻውን ልዩ ትርጉም እንዳለው ሮዛ ታምናለች፡፡ አንድ ከሆንን የማንሻገረው ችግር፣ የማናሳካው ዓላማ እንደሌለ ያሳየ ነውም ብላለች፡፡

ውጫዊ ጫናው ይበልጥ ጠንካራ እንድንሆን አድርጎናል ያለችው ሮዛ ሁሉም ያለውን ዕውቀት፣ ጉልበት እና ገንዘብ ለሕዳሴው አበርክቷል፡፡ ይህም ሌሎች ሀገራት የከለከሉትን ብድር ተረት ያደረገ የዘመኑ ትውልድ መገለጫ ነው ብላለች፡፡

ሕዳሴ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል የገጠሩ ማኅበረሰብ ከእንጨት ጭስ እንዲላቀቅ፣ ኢንዱስትሪዎች በኃይል እጥረት እንዳይፈተኑ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር እምነቷን ነግራናለች፡፡ የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግር የሚፈታ እንደሚሆንም በማን ግድቡ የፈጠረውን ሃይቅ ተከትሎ በዓሳ ሐብት እና በቱሪዝም ዘርፍ የሚፈጠረው ጸጋን ለማሳያነት አንስታለች፡፡

ኢብራሂም ሞሀመድ የተባሉ ሌላው የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ በበኩላቸው ለ14 ዓመታት የተደረገው ድጋፍ ለግድቡ መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ እንደ ግለሰብ በአክሲዮን እና በግል ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

“ለዓመታት በብዙ ነገር ስደግፈው የኖርኩት ግድብ ተጠናቆ አንድ ቀን በአደባባይ ወጥቼ ሐሳቤን እንደምገልጽ እርግጠኛ ነበርኩ፤ ግድቡ ዘር፣ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ የቆዳ ቀለም ሳይለይ ሁሉንም በእኩል የሚያገለግል ኢትዮጵያዊ ግድብ ነው” ብለዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ በአሁኑ ትውልድ የተመዘገበ የኢትዮጵያ ብልጽግና ማረጋገጫ መሆኑን አንስተዋል፡፡ “የዓድዋን ድል አንድ ሆነን እንዳሳካነው ሁሉ ታላቁ ግድብም ለምረቃ የበቃው በኢትዮጵያውያን ሀገር ወዳድነት እና አንድነት ስሜት ነው”ም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ዛሬ በዓባይ ወንዝ ላይ ያሳኩት የኃይል ማመንጫ ግድብ የኢትዮጵያ እናቶችን የአኗኗር ዘይቤ በእጅጉ የሚያሻሽል እንደሆነ የገለጹልን ደግሞ ወይዘሮ ዘሪቱ አለባቸው ተሳታፊ ናቸው፡፡ ተስፋቸው እውን ይሆን ዘንድ አቅማቸው በፈቀደው ልክ ድጋፍ ሲደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ግድቡ ኢትዮጵያውያን አንድ አይነት እሳቤ ይዘው የማያሸንፉት እና የማያሳኩት መሰናክል እንደማይኖር በተግባር ያረጋገጠ፣ የእኛነታችን መገለጫ ሲሉ ነው ሐሳባቸውን የሠጡት፡፡ ይህንን አንድነታችንንም በቀጣይ አጠናክሮ በማስቀጠል ኢትዮጵያን በልማት እና በሌሎችም ዘርፎች ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚገባ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here