እንደ መንደርደሪያ
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በክልሉ ውስጥ ያጋጠመው በትጥቅ የታገዘ ግጭት እና በሌሎች ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት የወደመውን ሐብት እና ንብረት መልሶ በመገንባት የአማራ ክልልን ቀድሞ ወደ ነበረበት ገጽታው ለመመለስ ከ102 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የክልሉ መንግሥት በወርሀ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም አስታውቋል፡፡ ይህ የተባለው የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች፣ አምባሳደሮች እና አጋር አካላት ጋር በአዲስ አበባ በነበረው ምክክር ነው፡፡
በእርግጥ ይህ የገንዘብ መጠን በጦርነት እና በግጭት የታጣውን የሰው ሕይወት እና የደረሰውን የአካል ጉዳት አያጠቃልልም፡፡ በጤና ተቋማት ላይ በደረሰ ጉዳት እና የመንገድ መዘጋቱን ተከትሎ የሕክምና ግብዓትን በወቅቱ ማድረስ ባለመቻሉ ምክንያት በሰዎች ላይ የደረሰው አካላዊ እና የሥነ ልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ወላዶች በጤና ተቋማት በሚደረግላቸው የሕክምና ክትትል በሰለጠኑ ባለሙያዎች መገላገል ሲኖርባቸው በሰላም እጦቱ ምክንያት በቤታቸው እንዲገላገሉ ተገደዋል፡፡
ግጭቱን እንደ ምቹ መደላድል ቆጥረው የተሻለ አቅም ያላቸውን ሰዎች በማደን እና የሚወዷቸውን የቤተሰብ አባላት በማገት ‘ካለኝ ወደነበረኝ’ እንዲሸጋገሩ ያደረጉት የሐብት መጠን ቢደመር ቁጥሩ አስደንጋጭ ሊሆን ይችላል፡፡ የቤተሰብ አባል ለሥራ እና ለተለያየ ምክንያት ወጣ ብለው እስከሚመለሱ የሚፈጠረው አዕምሯዊ መረበሽ፣ ደኅንነትን ለማረጋገጥ በየደቂቃው ለስልክ የሚወጣውን ገንዘብ… ማን ይገምተዋል፡፡
የአንድ ሰው የዕውቀት ደረጃ ዓመታዊ ልኬታ ተሠርቶለት ወደ ሀብት ቢቀየር በሁለት ዓመት ውስጥ ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው የከረሙት ከስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የሚልቁ ተማሪዎች ምን ያህል ይሆናል? ይህም ግጭቱ የፈጠረው ትልቁ ተጽእኖ ነው፡፡ በግብርና እና በሌሎች የልማት ሥራዎቻችን ላይ የደረሰው ጉዳትም ከላይ ባየነው ልክ ካሰብነው ጦርነት ገንዘብ ሊመልሰው የማይችልን ጉዳት ጥሎ ያልፋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በርስ በርስ ጦርነት በዓለም የመጀመሪያዎቹ አለመሆናችን በጦርነት አዙሪት ውስጥ ዓመታትን ከተሻገሩ እና ጦርነት ዜጎቻቸው በየሀገሩ እንዲበተኑ ከሆነባቸው ሀገራት ትምህርት ወስደን በፍጥነት ወደ ሰላም እንድንመለስ ሊያግዘን ይችላል፡፡ ሶሪያውያን ቀድመው የጦርነትን አስከፊነት ሳያውቁ ‘በለው በለው’ ማለታቸው ሀገሪቱ ከአሥር ዓመታት በላይ ባላባር ቀውስ ውስጥ እንድትጓዝ ሆናለች፡፡ እንደ አይ ኤስ ላሉ ዓለም አቀፍ ሽብርተኞች መነኸሪያ ሆናለች፡፡
ትናንት ሞልቶላቸው በተድላ ይኖሩ የነበሩ ዜጎቻቸው የነበራቸውን ሀብት እና ንብረት አጥተው ዛሬ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እና በውጭው ሀገራት ተበትነዋል፤ አንዳንዶች የልጆቻቸውን መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት ሲሳናቸው በየከተማው ለልመና እጃቸውን ዘርግተዋል፡፡ በፍጥነት ጦርነቱን ከማስቆም ይልቅ ጎራን ለይተው ለጦርነት በመሰለፍ ሶሪያን ለከፋ ጉዳት እንደዳረጋት አነሳን እንጂ እንደ አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት ደግሞ የእርስ በርስ ጦርነት በዜጎቻቸው እና በልማቶቻቸው ላይ ሊያደርሰው የሚችለውን ጉዳት ቀድመው በመረዳታቸው ከውድቀት ድነዋል፡፡
እኛም የጦርነትን አስከፊነት ቀድመን በመረዳት ከወዲሁ ለጦርነቱ መቆም አበክረን መሥራት ይገባናል፡፡ ለዚህም ይመስላል የአማራ ክልል ሕዝብ ሁለት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የቆየው ጦርነት ለሌላ ሦስተኛ ዓመት እንዳይሻገር ዐደባባይ ወጥቶ “ጦርነት ይብቃ! ሰላም ይስፈን!“ በማለት እየጠየቀ ነው፡፡
የሕዝቡ ፍላጎት
የኢትዮጵያ ትንሳኤስ መቼ ይሆናል? ለትንሳኤዋስ የሚቆመው ማነው? የሚሉት ጥያቄዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ በ2013 ዓ.ም ያጋጠመው የሰሜኑ ጦርነት ለከፍተኛ ጉዳት የዳረገው የአማራ ክልል ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ ውስጥ በተፈጠረ በትጥቅ በታገዘ ግጭት ውስጥ ይገኛል፡፡ ሕዝቡን ለዘርፈ ብዙ ሁለንተናዊ ኪሳራ እየዳረገ የሚገኘው ግጭቱ ወደ ሦስተኛ ዓመት እንዳይሻገር ከወዲሁ ለሰላም መስፈን መሥራት እንደሚገባ የዐደባባይ ላይ ሕዝባዊ ሰልፍ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
ጦርነት የሰለቻቸው፣ ልጆቻቸው ከትምህርት ውጪ ሆነው የከረሙባቸው ወላጆች፣ በስጋት ነጻነታቸውን አጥተው ለወራትም ቢሆን ተራርቀው የሚኖሩ ቤተሰቦች፣ ልማት የናፈቃቸው፣ በነጻነት ወጥቶ መግባት ያሳሰባቸው… ወገኖች “ክልሉ ወደ ቀደመ አስተማማኝ ሰላሙ ይመለስ! ዳግም ግጭት የሚቋቋም ሥነ ልቦና የለንም!“ በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
የሰላም እጦቱ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዳይገቡ ከፍተኛ ፈተና መፍጠሩን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው መቶ አለቃ ደጋረገ ፈንቴ ይናገራሉ፡፡ ተማሪዎች በነጻነት ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ የሆነውም በጸጥታ ችግሩ ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ የሰላም እጦቱ ሕገ ወጥ ንግድ እንዲበረታታ በር በመክፈት ዜጎች በኑሮ ውድነት እንዲማረሩም አድርጓል፡፡
የትኛውንም ያህል ጊዜ ውጊያ ቢደረግ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝብን ከጎዳ በኋላ መቋጫው ድርድር፣ ውይይት እና ንግግር እንደሆነም አቶ ደጋረገ ያምናሉ፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ወገኖች ሕዝብን ላልተገባ ጉዳት እየዳረገ ያለው ግጭት እልባት እንዲያገኝ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በተለይ ታጣቂ ኀይሎች መንግሥት በተደጋጋሚ እያስተላለፈ ላለው የሰላም ጥሪ ቢያንስ አንድ እርምጃ ተጉዘው ‘እንታገልልሀለን’ ለሚሉት ሕዝብ በተግባር መቆማቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
ወይዘሮ መዓዛ ፍቅሩ በበኩላቸው የተፈጠረው ግጭት ወንድም ከወንድሙ ጋር እንዲጠፋፋ ከማድረግ በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ እንዳላመጣ ታዝበዋል፡፡ ልጆች ከትምህርት ውጪ እንዲሆኑ ያደረገው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም በተደጋጋሚ የሚደረገውን የሰላም ጥሪ በአዎንታ መመልከት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡ ነዋሪውም በየአካባቢው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ወጣቶች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ከማድረግ ጀምሮ የተመለሱትም ስለ ሰላም አስፈላጊነት ምስክርነት እንዲሰጡ በማድረግ ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ ምክረ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
አቶ ደስታው ያረጋል ሌላው ሰላም እንዲሰፍን ዐደባባይ ወጥተው ከጠየቁ የከተማው ነዋሪዎች መካከል ናቸው፡፡ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ግጭት በክልሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ እንዲያጋጥም ያደረገበትን አግባብ ማንም ሊረዳው የሚችለው ክስተት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ባሕር ዳርን ጨምሮ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በብዙ አካባቢዎች እንዲፋዘዝ ማድረጉን መታዘቡን ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን በስጋት አንስተዋል፡፡ ማንኛውም ወጣት ግጭቱ መሬት ላይ ያደረሰውን ነባራዊ እውነታ በአንክሮ ተመልክቶ ለግጭቱ ማብቃት እና ለዘላቂ ሰላም ጅማሮ የበኩሉን አሻራ እንዲያሳርፍ ጠይቀዋል፡፡
በአጠቃላይ በደብረ ማርቆስ፣ በጎንደር፣ በባሕርዳር፣ በደሴ እና በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች በተደረገው ሕዝባዊ ሰልፍ ሕዝቡ ሁለት ዓመት የዘለቀው የሰላም እጦት ውድመት እንጂ ጥቅም እንዳላስገኘ በመግለጽ ድርጊቱን አውግዟል፡፡ “ብዙ ወገኖቻችንን አጥተናል፤ ሀዘን በየቤቱ ሰፍቷል፤ ክልሉ ምሁሩ እየሞተበት እና ተተኪም እያጣ ነው፤ ሰው ሞቶ ካለቀ መሪው እና ተመሪው ማነው?” ሲሉ የሰላም ተማጻኞች ጠይቀዋል፡፡
“ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ! የተከፈቱት አይዘጉብን! አስተማሪዎችን አይግደሉብን! ልጆቻችን ያለ ስጋት ይማሩ!” በማለት ያለፉት ሁለት ዓመታት ምን ያህል ፈታኝ ጊዜያት እንደነበሩ ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡
“እኛ የናፈቀን ልማት ነው!? ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር እንደፈለግን ገዝተን ማምረት እንፈልጋለን!? በተለይ ይህ ወቅት የቀጣይ ዓመት የልማት ሥራዎች የሚከናወኑበት በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከሥጋት ነጻ የሆነ አካባቢን እንዲፈጠርልን እንፈልጋለን!?” በማለትም ሕዝቡ ጠይቋል፡፡
በሰላም መደፍረስ ስጋት የተሰደዱ ወገኖች እንዲመለሱ የክልሉን ሰላም መሆን መናፈቃቸውንም ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡ “ልጆቻችን ያለ ስጋት ወጥተው የሚገቡበት፣ ተምረው የሚመለሱበት፣ እኛም በነጻነት ተንቀሳቅሰን ሠርተን የምንመለስበትን ቀን ጓጉተን እንድንጠብቅ ሆነናል” ሲሉ አሳሳቢነቱን ተናግረዋል፡፡
ጦርነት ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ ለቁሳዊ ውድመት፣ ለማኅበራዊ መስተጋብር መቋረጥ፣ በሕዝብ መካከል መተማመን እንዳይኖር ከማድረግ ባለፈ ለውጥ እንዳላመጣ ባለፉ የጦርነት ታሪኮች ማየታቸውን የሰላም ፈላጊ ወገኖች ድምጽ አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ለአማራ ሕዝብ እንታገላለን ብለው ጫካ የገቡ ወገኖች የሕዝብን ስቃይ፣ መከራ እና ተማጽኖ ተረድተው በሰላማዊ የትግል አማራጭ ለሕዝብ ትግል መረጋገጥ እንዲመለሱ ተጠይቋል፡፡
መንግሥትም ችግሩን በዘላቂነት ለመቋጨት ያስችለኛል ያለውን ሁሉ አማራጭ በቁርጠኝነት በመተግበር ለሕዝብ በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉጉት እንዲሠራ ተጠይቋል፡፡ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በድርድር ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ሕዝብን ተጠቃሚ፣ ክልሉን ብሎም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግር በመሆኑ ሁለቱም ወገኖች ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ ሰላም ፈላጊ ወገኖች በአደባባይ አረጋግጠዋል፡፡
የመንግሥት ምላሽ እና ቀጣይ የቤት ሥራዉ
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሐኑ የፌዴራል እና የክልል የጸጥታ ኅይላት ከዞኑ ሕዝብ እና አመራር ጋር በመቀናጀት በሠሩት ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ የዞኑ ሰላም ወደ ተሻለ ሰላም እና መረጋጋት መመለሱን ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ ክልሉ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ተወዳዳሪ እንዳይሆን ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ “ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወገኖቻችሁን እና ቤተሰቦቻችሁን መክራችሁ እና አሳምናችሁ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንድትመልሱ” ሲሉ ለሰላም መስፈን አጋር ነን ብለው ለወጡ ዜጎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው መንግሥት አሁንም ለሰላም በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ወደ አትራፊው ሰላም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ባሕር ዳር ከተማ ሰላሟን አስጠብቃ የልማት ሥራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና ነጋዴው ማኅበረሰብ እየተገኘ ያለውን ሰላም ለማጽናት እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዲያስፓራዎችም ባሉበት ሆነው ስለ ሀገራቸው ሰላም እና ልማት እንዲሰብኩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ሕዝባዊ ሰልፉ የሕዝቡ ሰላም ፈላጊነት፣ ልማት ወዳድነት፣ ግጭት እና ጦርነት ጠልነት በተግባር የታየበት እንደነበር የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ በዐደባባይ ወጥቶ ግጭት ፈጣሪዎችን እና አሉታዊ አስተሳሰቦችን በአንድነት ቆሞ ያወገዘው ብለዋል፡፡
በሰልፉ የክልሉ ሕዝብ ለግጭት ያለውን የመረረ ጥላቻ፤ ለሰላም እና ለልማት ደግሞ ያለውን ጠንካራ አቋም አንስቷል ብለዋል፡፡ ሕዝባዊ ሰልፉ ለሕግ የበላይነት መቆምን ያሳየ፤ አፍራሽ አካሄድን በመጸየፍ ለሀገራዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት መጽናት ያለውን ጽኑ ፍላጎት እና ቁርጠኛ ትግልም ያመላከተ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
መልማት፣ ማደግ፣ መለወጥ፣ መበልጸግ እና ከዓለም ጋር በዕውቀት መወዳደር የክልሉ ሕዝብ ዋነኛ ፍላጎት መሆኑ በተግባር ታይቷል ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም የተረጋጋ ክልል ለመምራት፤ የሕዝቡን መብት፣ ፍላጎት፣ ጥቅም እና ደኅንነትም ለማስከበር ያለመታከት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡
የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በበኩላቸው ሕዝቡ የቀደመ ባህል እና እሴቱን የሚያዋርዱ፣ ጥቅም እና መብቶቹን የሚሸረሽሩ እኩይ ተግባራትን ሲያወግዝ፣ ሕግ እና ሥርዓት እንዲከበርለት ደግሞ በአጽንኦት መጠየቁን ተናግረዋል፡፡ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ያለውን ጽኑ አቋማም በተግባር ማንጸባረቁን ገልጸዋል፡፡
የሕዝባችን መብትና ጥቅም በዘላቂነት የሚረጋገጠው በግጭትና ብጥብጥ ሳይሆን ሰላማዊ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ግጭት ድህነትን እንጂ ወረትን ለዛሬውም ሆነ ለነገው ትውልድ በፍፁም አያወርስም። ለየትኛውም ወገም አይጠቅምም። መንግሥትም ሁሉም ችግሮች በሰለጠነ መንገድ እልባት እንዲያገኙ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል። ዓላማችን የሕዝባችን መብትና ጥቅም ተረጋግጦ ማየት ነው። ወደፊትም ለሰላም ቅድሚያ እንሰጣለን፤ ልማታችን ላይም ትኩረት አድርገን እንሠራለን!” በማልት ከሕዝብ እና ከመንግሥት ምን እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም