ሕዳሴ “አይችሉም”ን ተረት አድርጎ ያሳየ የኢትዮጵያውያን አርማ ነው ተባለ

0
13

ጅማሮውን መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረገው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ14 ዓመታት በኋላ መጠናቀቁ ተበስሯል፡፡ ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ እንደተሸፈነ የተነገረው ግድቡ አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ መያዙን ተከትሎ የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ሃይቅም በአሣ ሐብት እና በቱሪዝም ዘርፍ ተጨማሪ ገቢን የሚያስገኝ እንደሚሆን ይታመናል፡፡

ለግድቡ ዕውን መሆን የኢትዮጵያዊያን አንድነት እና መተባበር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደነበረው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዉ አቶ አስማረ ኃይሌ ሕዳሴ ለምረቃ የበቃው በኢትዮጵኊያን ርብርብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ርብርብ አሁን የገጠመውን የሰላም እጦት ቀልብሶ ወደተሻለ ከፍታ ለመጓዝ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

50 አለቃ መንበሩ አንዷለም በበኩላቸው የግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል፡፡ ዓባይ መገደቡን የኃይል ችግራችን መፍትሄ እንዲያገኝ ከማድረጉም ባለፈ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ የምግብ ዋስትና በዘላቂነት እንዲረጋገጥ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራው አድጎ ሥራ አጥነት እንዲቀንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

የሕዳሴ መጠናቀቅ እና ወደተሟላ ልማት መሸጋገር የአሁኑ ትውልድ አደራ አስቀጣይነት ማሳያም ነውም ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ያለፉ ነገሥታት እና ኢትዮጵያዊያን በዓባይ ላይ ግድብ የመገንባት ፍላጎት ነበራቸውና፤ ይህም በመተባበር ዕውን ሆኖ አይችሉም ላሉን ችለን ያሳየንበት አሻራችን ነው ብለዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት  ጽሕፈት ቤት እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ ዲጂታል የብስራት መልዕክት እና ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክትን ይፋ ባደረጉበት ወቅት የጽሕፈት ቤቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ግድቡ የአንድነታችንና የፅናታችን ማሳያ፣ የዘመናችን ዓድዋ ነው ብለዋል። በውስጥም በውጭም ያጋጠሙ ፈተናዎችን በማለፍ የጥረታችንን ፍሬ አይተናል፤ በአብሮነት እና በኅብረት ተሰልፈን ሰላማዊ ዓድዋን በሕዳሴው ግድብ እውን አድርገናል” ብለዋል።

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here