ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ሠርቶ ከፍታዋን ለማረጋገጥ የነበራት የሐሳብ ጥንስስ ተስፋን የዘራው በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይነገራል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነበሩ የተለያዩ መንግሥታት ቅብብሎሽ ግድብ የመገንባት ሐሳቡ ቢቀጥልም የተጀመረው ግን መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነው። የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒሥትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያውያን ከተረጂነት ለመውጣት ሕዳሴን በራሳቸው አቅም እንዲሠሩት የጀመሩት ግድብ በአቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ ቀጥሎ ከ14 ዓመታት የግንባታ ጊዜ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተጠናቋል። ይፋዊ ምረቃውም ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሂዷል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ላይ የታሰረው ቀዳሚ ዓላማው የኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጨት ነው። በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባም አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኅይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል። ባለፈው ዓመት ከተገኘው ኀይል 33 በመቶ የሚሆነው ከሕዳሴ ግድብ የተገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል መግለጫ ያሳያል። የኀይል ማመንጫ ግድቡ በሙሉ አቅም ኀይል ማመንጨት ሲጀምር የሀገሪቱን የኀይል ተደራሽነት አሁን ካለበት 54 በመቶ ከማሳደግም ባሻገር በአሳ ሐብት፣ በቱሪዝም፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎችም ዘርፍ የሀገሪቱን ከፍታ እንደሚያሳድግ እምነት ተጥሎበታል።
ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን አሳልፎ ላለመስጠት በተደረገው ጦርነት በዓድዋ የተገለጠው ኢትዮጵያዊው አይበገሬነት እና አንድነት ዛሬም ሕያው መሆኑ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደግሟል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ከዓድዋ ድል ጋር የሚያመሳስለው ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ጸሐፊ እና የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪ ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) ለድርጅቱ በላኩት ጽሑፍመረጃ አሳውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያለማንም ረዳት፣ አጋዥ፣ ለጋሽ፣ አበዳሪ እና አይዞሽ ባይነት ብቻዋን የተወጣችው እና የተጐናፀፈችው ድል መሆኑን ቀዳሚው ማሳያ አድርገውታል፡፡
የዓድዋ ጦርነት እና የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያዊያን አመላቸውን በጉያቸው፣ ልዩነታቸውን በጓዳቸው ትተው ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ላባቸውን፣ ደማቸውን አዋጥተው እና አስተባብረው ያከናዎኑት ዘመን ተሻጋሪ ድል መሆኑነም ዶ/ር ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡
ጸሐፊ እና ተመራማሪው የዓድዋ ድል እና የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ሌላኛው ምስጢር ነው ያሉትንም ያስረዳሉ፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ በሀገራቸው እና በሉዓላዊ ግዛታቸው በነጻነት የመወሰን፣ ሦስተኛ ወገን ያወጣውን ሕግ መሰል ቀንበር፣ ውል መሳይ እግረ ሙቅ ያለመቀበል ጀግንነትን ያስተዋወቀ፣ በጥቅሉ የኮሎኒያሊስቶችን ቀንበር የሠበረ፤ ፍትሕን በራስ አቅም ያስከበረ ለመላው ታዳጊ ሀገር ሕዝቦች ትምህርት የሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ድሎች መሆናቸው ማረጋገጫ አድርገዋል፡፡
ሕዳሴ የዳግም ዓድዋ ተምሳሌት መሆኑን የተለያዩ የአፍሪካ እና የሌሎች አህጉራት መሪዎችም አረጋግጠዋል፡፡ የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንድትሠራ ማንም ፍላጎት አልነበረውም፤ ይህም ግድቡ ለምረቃ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዲያልፍ እንዳደረገው ገልጸዋል። ግድቡ ለምረቃ የበቃው ኢትዮጵያውያን ቀድሞውኑ በሚታወቁበት የቁጭት ስሜት ግለት እንደሆነ አንስተዋል።
“ኢትዮጵያውያን አይበገሬዎች ናቸው፡፡ ጠላት ሲገጥማቸው ጥረታቸውን በእጥፍ ይጨምራሉ፡፡ ማግኘት ያለባቸውን ሳያገኙ ወደ ኋላ አይሉም” በማለት በኢትዮጵያውያን አንድነት የተጠናቀቀ ግድብ መሆኑን ጠቁመዋል። ግድቡ የሚያመነጨው ኅይል የሀገሪቱን የኅይል ሽፋን ከማሻሻል በተጨማሪ ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ ትብብሯን ለማጠናከር እንደሚያግዛትም ተናግረዋል።
በምረቃው ወቅት የተገኙ የአፍሪካ እና የሌሎች ሀገራት መሪዎችም ሕዳሴ የጽናት ተምሳሌት፣ የአሸናፊነት አርማ፣ የመተባበር ውጤት መሆኑን ተናግረዋል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ሕዳሴን የገለጹት የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክት እና ለቀጣናው ሀገራት የመገናኛ መንገድ በማለት ነው፡፡ ለግድቡ ዕውን መሆን ኢትዮጵያውያን የከፈሉት ዋጋ ለልማት የማይበገሩ መሆኑ የታየበት እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ግድቡ ኀይል በማመንጨት በዘርፉ ለሚስተዋለው ችግር መፍትሄ ከመሆኑም በላይ ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሕዳሴ በረከት ለደቡብ ሱዳናውያን የገጠር ሰፈሮች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች የሚተርፍ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሀገራቸውም ከግድቡ ኀይል ለመግዛት የሚያስችል ስምምነት እንደምትፈራረም አስታውቀዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐመድ አሊ የሱፍ የሕዳሴው ግድብ የሕልም፣ የጠንካራ ሥራ ባህል እና ብልሃት የተሞላበት አመራር ውጤት ነው ብለዋል፡፡ ሕዳሴ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ፣ ጉልበት፣ ደም እና ላብ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ 2063 አጀንዳ ዜጎችን በተለያየ የመሠረተ ልማት አውታሮች እና በኀይል አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡ ሕዳሴ ደግሞ ግቡን ለማሳካት ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል አንደኛው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ኅይል ማመንጫ ግድቡ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ ለኤሌክትሪክ ኀይል እና ለሌሎችም የልማት ዘርፎች ትልቅ አቅም እንደሚሆን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
የባርባዶስ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒሥትር ሚያ አሞር ሞትሊ ሕዳሴ አፍሪካውያን እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጠ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ከማንም ምንም ሳይጠብቁ የሠሩት፣ የኢትዮጵያም መቻል ማሳያ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ የካሪቢያን እና የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ ከገለጠችው የይቻላል መንፈስ ትምህርት እንዲወስዱም ጠቁመዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትናንት ቁጭት ማሰሪያ፣ የመጪው ንጋት ማብሰሪያ ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፈጠረው የንጋት ሃይቅ 74 ትሪሊዮን ሊትር ውኃ መያዙን ተናግረዋል፡፡ ይህም በጥቁር ሕዝብ ታሪክ የመጀመሪያው ታላቅ ሥራ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ሕዳሴ ጥቁሮች ጀምረው መጨረስ እንደሚችሉ ያረጋገጠ አሻራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 15 ቢሊዮን ብር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሥትሩ፣ ንጋት ከኢትዮጵያ ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት የላቀ ሀብት መያዙን የግዙፍነቱ ማሳያ አድርገው አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከጥልቅ ጨለማ ያወጣ እና ከእንቅልፍ ያነቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕዳሴ የአሁኑ ትውልድ ታሪክ ከመሥማት ወደ መሥራት ያሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ትውልድ ጀምሮ ያጠናቀቀው የሕዳሴ ግድብ የዳግም ዓድዋ ተምሳሌት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሥትሩ፤ ይህም የኢትዮጵያ የልመና፣ የስንፍና እና የእንጉርጎሮ ዘመን እንዲባቃ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ለኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ሕዳሴ የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ልክ አይቀሬ መሆኑን ዳግም ያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግባቸው የልማት ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩ አረጋግጠዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ችግር ይዞ እንደማይመጣ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሕዳሴን የሠራችው ለመበልጸግ፣ አካባቢውን በብርሐን ለመሙላት እና የጥቁር ሕዝብ ታሪክን ለመቀየር እንጂ በፍጹም ወንድሞቿን ለመጉዳት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡ “ኢትዮጵያ ሀቃችሁን አታስቀረም” በማለት ግድቡ ለተፋሰሱ ሀገራት ስጋት እንደማይሆን አረጋግጠዋል፡፡ “የግብጽ ረሃብ፣ የሱዳን ረሃብ እና የሌሎች ወንድሞቻችን ረሃብ እና ችግር የኛም ረሃብ ስለሆነ አብረን ከመብላት እና ከመካፈል ውጭ እኛ ተጠቅመን ማንንም የመጉዳት ፍላጎት የለንም። ለወደፊት በምንሠራቸው ታላቅ ሥራዎች በትብብር እና በጋራ እንድንቆም ከወዲሁ በአደራ ጭምር ላሳስባቸው እወዳለሁ” በማለት ኢትዮጵያ ዛሬም በጋራ መልማት መርኋ ሆኖ መቀጠሉን አረጋግጠዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም