ሕዳሴ ግድብ፦ የአንድነት ገመድ

0
200

የሐሳብ ጥንስሱ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ነው፤ ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግድቡ ኅይል ማመንጨት መጀመሩን ተከትሎ በተፈጠረ የማብሰሪያ መርሀ ግብር ወቅት አረጋግጠዋል:: ኢህዴግ መጋቢት 24 ቀን  2003 ዓ.ም ተግባራዊ እንቅስቃሴውን አስጀምሯል:: በ2010 ዓ.ም መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ብልጽግናም አዳዲስ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ሥራውን አስቀጠለ::

የምናስነብባችሁ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው:: ኢትዮጵያውያን ዕውቀታቸውን እና ሐብታቸውን ለነገው ትውልድ በአሻራነት ለማስቀመጥ ከዳር እስከ ዳር የተንቀሳቀሱበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው:: የግድቡ የመሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ አምስት ዓመታት የግንባታ ጊዜያት እንደሚኖረው ተገለጸ፤ የግንባታ ወጪውም 80 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተነገረ::

የሀገሬውን የኤሌክትሪክ ኀይል ፍላጎት ለማሳካት፣ በኀይል አቅርቦት የተፈተኑ ኢንዱስትሪዎችን በዘላቂነት ወደ ምርት ለማስገባት የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ግድቡን ከችግር የመውጫ መንገድ አድርገው ተነሱ:: ከተማሪ እስከ ምሁራን፣ ከአርሶ አደር እስከ ወታደር፣ ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከመንግሥት ሠራተኛ እስከ ቀን ሠራተኛ… ሁሉም የፈካ ፊቱን ለግድቡ አሳይቷል:: ሕዝቡ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ የመንገድ ርቀት ሳይገድበው ለግድቡ መጠናቀቅ ጥሬ ገንዘብ በባንክ ከማስተላለፍ ጀምሮ በኢትዮ ቴሌኮም አጭር የጽሑፍ መልዕክት እና በቦንድ ግዥ አጋርነቱን አሳይቷል::

ይሁን እንጂ ግድቡ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቅቆ ለሕዝቡ ርብርብ ምላሽ ሳይሰጥ 13 ዓመታትን ዘልቋል:: በእነዚህ ዓመታት ለግንባታው የወጣው ወጪም ከ184 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ከሕዳሴ ግድቡ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል::

ግንባታው ለምን ስምንት ተጨማሪ ዓመታትን ጠየቀ?

በግንባታ ፕሮጀክቱ የተስተዋሉ የአስተዳደር እና የብልሹ አሠራር እንከኖች ግድቡ መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ ተጨማሪ ስምንት ዓመታት የግንባታ ጊዜን እንዲጠይቅ አድርጎታል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም የህዳሴ ግድቡን ለሁለተኛ ጊዜ በጎበኙበት ወቅት በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተይዞ የነበረው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ መጓተት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ማድረጉን ተናግረዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማከልም ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁ ሀገሪቱን ለአንድ ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ኪሳራ ዳርጓታል:: የግድቡ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ሀገሪቱ በየዓመቱ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንድታገኝ ያስችላት እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል:: መዘግየቱ ግን ሀገሪቱን ለተጨማሪ ከፍተኛ ወጪ እንደዳረጋት ገልጸዋል::

ፕሮጀክቱን ከፍተኛ የሙያ ልምድ ላላቸው ተቋራጮች በመስጠት ማጠናቀቅ የመንግሥት የቅድሚያ ትኩረት ሆኖ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመት ታስቦ ሲውል አጠቃላይ የግንባታ ደረጃው ከ95 ነጥብ አምስት በመቶ በላይ መድረሱ ተገልጿል::

ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች እና የኢትዮጵያ አቋም

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ፖለቲካ ተመራማሪ እና የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓለም አቀፍ ተደራዳሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ግድቡ  ለኢትዮጵያውያን የልማት አጋዥ፣ በኤሌክትሪክ ኀይል ለሚደገፉ በርካታ ልማቶችም ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ ለበኲር በስልክ ገልጸውልናል:: የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ቁርጠኝነት በተግባር የታየበትም ነው:: ኢትዮጵያ በብሄራዊ የተፈጥሮ ሀብቷ ጎረቤቶቿን ሳትጎዳ ልማቷን የማከናወን ሉዓላዊ መብት እንዳላት ያረጋገጠ እንደሆነም ጠቅሰዋል::

ይሁን እንጂ ግብጽ ወደ ሀገሯ የሚገቡ እና ሀገሯን አቋርጠው የሚፈሱ ወንዞች ከፈቃዷ ውጭ በማንኛውም የውኃ ምንጭ መፍለቂያ ሀገራት ውሳኔ ሊገደብ እንደማይችል “እኔ ከሞትኩ…” አይነት ብሂልን ማራመዷ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን ከዳር ዳር አስቆጥቷል::

የውኃ ፖለቲካ ተመራማሪው ግብጽ በዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግድብ የኢትዮጵያን ከፍታ በእጅጉ በማሳደግ ግብጽን ተገዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑ ግድቡን ለማስተጓጎል ረጅም ርቀት እንድትጓዝ አድርጓታል ይላሉ:: የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎልም ሱዳንን ጨምሮ የውጭ ደጋፊ ኀይሏን በማስተባበር እስከ ጸጥታው ምክር ቤት ሳትታክት ተጉዛለች:: ኢትዮጵያም  በግብጽ እና ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ ወዳጆቿ የተደረገባትን ጫና እየመከተች በአሁኑ ወቅት ኀይል እስከ ማመንጨት ደርሳለች::

ከበርካታ ጥረት በኋላ በ2015 ዓ.ም የተደረሰው የሦስትዮሽ የመርህ ስምምነት ደግሞ የኢትዮጵያን ተደማጭነት ከፍ ያደረገ፣ በቀጣይ የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችንም የሚያረግብ እንደሚሆን ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) አብራርተዋል:: ኢትዮጵያ የተፋሰሱን ሀገራት በተለይ ግብጽ እና ሱዳንን በማይጎዳ መልኩ ግንባታ እያከናወነች እንደምትገኝ፣ ግድቡንም እየገነባች በደረሰችበት የግንባታ ደረጃ ልክ የውኃ ሙሌት ማከናወን እንደምትችል፣ በሀገራቱ መካከል ለሚኖር አለመግባባት ዳኝነት የሚሰጠው ሦስቱ ሀገራት በአንድ ድምጽ በሚስማሙበት አደራዳሪ ብቻ መሆኑ በሦስትዮሹ የመርህ መግለጫው ላይ መስፈሩን ጠቁመዋል:: ስምምነቱ ኢትዮጵያ ግድቡን የመገንባት አቅም  እንዳላት እና ግንባታ እንደጀመረች ዕውቅና የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር ግድቡን እየሞላች ኀይል ማመንጨት እንደምትችል ያረጋገጠ መሆኑን ምሁሩ ጠቁመዋል::

ግድቡን ለማስተጓጎል ከተደረጉ ጫናዎች በተጨማሪ በግድቡ ላይ የተስተዋሉ አስተዳደራዊ እና ብልሹ አሠራሮች ላይ የተወሰደው ሥር ነቀል ርምጃ የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ደረጃ በአማካኝ ከ95 በመቶ በላይ እንዲደርስ አድርጎታል::

ግድቡ ኅይል ከማመንጨት ባለፈ የኢትዮጵያን የወደፊት ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ጭምር የሚወስን መሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት እና ሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ተናግረዋል:: 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንደሚይዝ የተነገረለት ግድቡ በአሁኑ ወቅት 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ  ውኃ መያዙ ተነግሯል:: ዋናው ግድብ ሲጠናቀቅ ከግድቡ ኋላ የሚተኛው የውኃ መጠን 246 ኪሎ ሜትር ቦታን እንደሚሸፍንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል:: በአሁኑ ወቅት የተኛው የውኃ መጠን 160 ኪሎ ሜትር ነው::

ግድቡ ሲጠናቀቅ በ13 ተርባይኖች አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኀይል ያመነጫል::   አሁን በደረሰበት የግንባታ ደረጃ በሁለት ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት ኀይል በማመንጨት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ::

የኀይል አቅርቦቱን ምን ያህል ያሻሽለዋል?

የኢትዮጵያ አሁናዊ አጠቃላይ የኀይል አቅርቦት 5 ሺህ 250 ሜጋ ዋት ነው:: የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የኮይሻ ኀይል ማመንጫ፣ የአሰላ የነፋስ ኀይል እና አይሻ የኀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በድምሩ ሰባት ሺህ ሜጋ ዋት ኀይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖራቸው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል የተገኘው መረጃ ያሳያል:: ፕሮጀክቶቹ የሚያመነጩት ኀይል ከነባሩ ጋር ተደምሮ አሁን ያለውን የሀገሪቱን አጠቃላይ የኀይል አቅርቦት ከ12 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ያደርሰዋል::

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ በላይነህ አስማረ ለበኲር በስልክ በሰጡን መረጃ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አሁን ላይ በኢንዱስትሪዎች የሚስተዋለውን ከሚፈለገው በታች የማምረት ችግር እና በኅይል እጥረት ወደ ሥራ ላልገቡት ብስራት እንደሚሆን ገልጸዋል::  ይህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በማዳን ለተጨማሪ ኢንዱስትሪዎች በር የሚከፍት እንደሚሆን ገልጸዋል::

የኢንዱስትሪዎች የኅይል አቅርቦት ችግር ሲፈታ ሰፊ የሥራ ዕድልን ይዞ እንደሚመጣ፣ ይህም የዜጎችን ገቢ በማሳደግ የፍጆታ ምርቶች ፍላጎት በእጅጉ እንዲጨምር ያደርጋል:: ይህም አምራች ተቋማት የፍላጎት ክፍተቱን ለመሙላት በስፋት ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ያደርጋቸዋል::

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለአሚኮ እንደተናገሩት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ከምታመነጨው ኀይል እስከ 13 በመቶ የሚሆነውን ወደ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ በሽያጭ በማቅረብ በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል:: በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ሀገራት ጥያቄ እያቀረቡ ነው:: በዚህም ከታኅሳሥ 2016 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኀይል ወደ ኬንያ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል::

ታንዛኒያ እና ሌሎች አጎራባች ሀገራትን ጨምሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል:: ግድቡ በኅይል ሽያጭ ብቻ በዓመት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ተመላክቷል::

የኤሌክትሪክ ኀይል ከማመንጨት ባሻገር የመነጨውን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው::

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት አዲስ መሠረተ ልማት መዘርጋት ሳያስፈልግ በነባሮች ተጨማሪ ኀይል ተደራሽ ማድረግ ይቻላል:: አሁን ያለው ነባሩ መሠረተ ልማት እያስተላለፈ የሚገኘው ኅይል 200 ሜጋ ዋት ብቻ መሆኑን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፣ የተሟላ የማስተላለፍ አቅሙ ግን እስከ ሁለት ሺህ ሜጋ ዋት እንደሚደርስ አስታውቀዋል::

ከኅይል ምንጭነት ባሻገር

የሕዳሴ ግድቡ የኤሌክትሪክ ኅይል ማመንጨት ዋና ተግባሩ ነው። ነገር ግን ግድቡ ከኅይል ምንጭነት ባሻገር ይዞት የሚመጣው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የኢኮኖሚክስ መምህሩ አቶ በላይነህ አስማረ በመዘርዘር ያስረዳሉ:: የሕዳሴ ግድብ ከኅይል ማመንጨት ባሻገር ኢትዮጵያ ካሏት የአሳ ማምረቻ ሐይቆች በተጨማሪ ሌላ ተጨማሪ የሐብት ምንጭ እንደሚሆን ያምናሉ::

የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ በዓመት ከ10 ሺህ ቶን በላይ አሳ ማምረት እንደሚያስችል ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል:: መምህሩ እንደገለጹት ሃይቁን በትኩረት መጠቀም ከተቻለ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ያለፈ አሳን አቀነባብሮ ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል:: በመጠንም ሆነ በጥራት ተፈላጊ የሆኑ የአሳ ምርቶችን ለማግኘት ግን ለተሻሻሉ ዝርያዎች ትኩረት መስጠት ይገባል::

“ግድቡን ለማየት የማይጓጓ ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ጎብኝ የለም” ያሉት ተመራማሪው፣ በመሆኑም ግድቡን ለጎብኝዎች ምቹ በማድረግ የተለየ የኢንቨስትመንት አማራጭ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል:: ለዚህም በደሴቱ የሚፈጠሩ 78 ደሴቶች ትልቅ አቅም ይሆናሉ:: በመሆኑም ደረጃቸውን የጠበቁ መናፈሻዎችን፣ ሆቴሎችን… መገንባት የግድቡን ዙሪያ ብቻውን የገቢ ምንጭ ማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል::

ዘላቂ የአፈር ለምነትን በማረጋገጥ ምርት እና ምርታማነትን ለማስቀጠል የግድቡ ፋይዳ ከፍተኛ ሆኖ ይነሳል:: ይህም የሚሆነው ግድቡ ከኢትዮጵያ ይዞት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ለም አፈር ለማስቀረት የሚያስችል መሆኑ እንደሆነ አቶ በላይነህ አስታውቀዋል:: ገድቡ ትልልቅ የመስኖ ልማቶችን ለመፍጠር ትልቅ ዕድልን ይዞ እንደሚመጣም ታምኗል::

በአጠቃላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቱን ምጣኔ ሐብት በእጅጉ የሚያሳድግ፣ በዓለም ያላትን ተሰሚነትም ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ ቀሪ ሥራውን ለማጠናቀቅ የሚስፈልገውን 50 ቢሊዮን ብር በተለመደው ተሳትፎ ማስቀጠል እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here