ዓባይ የኢትዮጵያ መታወቂያ ከሆኑ በርካታ ሐብቶች መካከል አንዱ ቢሆንም ባለፉ ዘመናት ለኢትየጵያውያን ያበረከተው ጥቅም እንደ ግዝፈቱና ታላቅነቱ አልነበረም::
ለዚህ ግብሩ ደግሞ “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” የሚለው የሀገሬው አባባል ምስክር ነው:: ዓባይ ከመነሻው ሰከላ ጀምሮ ለም አፈርን፣ በውድ ከውጭ ተገዝቶ ለሰብል ማፋፊያ አፈር ጋር የተቀላቀለን ማዳበሪያ እና ሌሎችንም ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገትን ዕውን ሊያደርጉ የሚችሉ ግብዓቶችን ሁሉ ጠራርጎ ለሱዳን፣ ግብጽ እና ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ሲያድል ለመኖሩም ማረጋገጫ ነው::
ኢትዮጵያን እንዲያለማ በነገሥታቱ ተጀምሮ የነበረውን ውጥን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ዓባይን ለኤሌክትሪክ ኅይል የመገደብ የመሠረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ በቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንሥትር መለስ ዜናዊ በይፋ ተቀመጠ:: 80 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃን ይዞ ከሀገር ውጭ ሱዳንን እና ግብጽን ሲያለማ ለኖረው ዓባይ ወንዝ የግድብ ግንባታ ዕውን መሆን ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ ምሁር፣ ከአርሶ አደር እስከ ወታደር… ሁሉም በቻለው ለማበርከት ቃል ገባ፤ በቦንድ ግዥ፣ በልገሳ እና በሌሎች የክፍያ አማራጮች አጋርነቱን በተግባር አረጋገጠ::
ተስፋን በጽናት
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው እና ጡረተኛው አቶ ፋንታ መስተሳህል መፍለቂያውን ሳይጠቅም ግብጽ እና ሱዳንን ለዘመናት ሲያለማ ማየታቸው እጅጉን ሲያስቆጫቸው የቆየ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል:: እነዚህ ሀገራት ደግሞ ከኢትዮጵያ መልማት በተቃራኒ የቆሙ ናቸው::
በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ሊገነባ መሆኑን በ2003 ዓ.ም ሲሰሙ የዓመታት ቁጭታቸው ማክሰሚያ እንደሚሆን ተማመኑ:: ከቁጭትም ባለፈ ግድቡ በኤሌክትሪክ የኀይል ምንጭነት እንደሚያገለግል በወቅቱ መስማታቸው የኀይል እጥረቱን እና መቆራረጡን ለመፍታት ሚናው ከፍተኛ እንደሚሆን አመኑ::
ግድቡ ሊያሳካው የሚችለውን ዓላማ ከዳር ለማድረስም መንግሥት ከሚያወጣው ወጪ በተጨማሪ ግድቡ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ አቅማቸው በፈቀደ መጠን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ወሰኑ:: ግድቡ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ሲነገር በወቅቱ በየዓመቱ ሳያቋርጡ ድጋፍ ለማድረግ ለራሳቸው ቃል ገቡ:: አቶ ፋንታ ቃላቸውን አክብረው ድጋፋቸውን ጀመሩ::
አቶ ፋንታ ግድቡ ተጨማሪ ዘጠኝ ዓመታት ቢጠይቅም ድጋፋቸውን ከመቀጠል ወደ ኋላ አላሉም፤ ተስፋቸው አልመከነም:: በ14 ዓመታት የግንባታ ጊዜ ውስጥም የ168 ሺህ ብር ቦንድ እንደገዙ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል::
“የእኛ በጨለማ መኖር የሚያበቃው፣ በልቶ ለማደር ስጋት የማይሆነው ዓባይ ሲገደብ ነው” የሚለው የአቶ ፋንታ ቁጭት በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ፍጻሜውን አግኝቶ ይመረቃል:: ግድቡ አሁን ካለበት የፍጻሜ ደረጃ ላይ የደረሰው በውጭ ኀይሎች የተሰነዘረውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና በጽናት በማክሸፍ እና በሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ እንደሆነ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል::
ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ተመላክቷል:: ይህ ሐብት የተሰበሰበው በቦንድ ሽያጭ እና ስጦታ፣ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልዕክት እና ከውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን /ከዳያስፖራዎች/ ነው::
አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩም ሕዳሴን በደለል ከመሞላት ለመታደግ ባከናወነው የተፋሰስ ሥራ ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ የጉልበት አስተዋጽኦ ማድረጉን የግብርና ሚኒሥቴር መረጃ ያሳያል::
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ የሕዝብ ተሳትፎ እና የጠንካራ ዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁር እና የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ባተኮረ የፓርላማ የዜጎች ፎረም ላይ አስታውቀዋል::
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ግዙፍነት ማሳያዎች
ዓለም ካላት ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኅይል ማመንጫ ግድቦች መካከል አንዱ የሆነው የኢትጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ 145 ሜትር ከፍታ እና አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው:: ከማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመዉ የዋናው ግድብ ውፍረት ግርጌው ላይ 130 ሜትር፣ የግድቡ ጫፍ ወይም የላይኛው ክፍል 11 ሜትር፣ የሚሸፍነው ቦታ አንድ ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው:: የግድቡ ውኃ የመያዝ አቅምም 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው:: ይህም በሀገሪቱ ግዙፉ የሰው ሠራሽ ኃይቅ ያደርገዋል:: በዚህም የተነሳ በሐይቁ ላይ 78 ደሴቶች ይፈጠራሉ::
የኢትዮጵያዉያን የአንድነት እና የይቻላል መንፈስ ማሳያ የሆነው ግድቡ አሁን ላይ ኀይል በማመንጨት እና የአሣ ምርት መገኛ በመሆን እያሳየ ይገኛል:: ግድቡ በዓመት ከ10 እስከ 15 ሺህ ቶን አሣ ማምረት ያስችላል ተብሎ ይታመናል:: በ2017 በጀት ዓመት ብቻ አምስት ሺህ 895 ቶን የዓሣ ምርት ተገኝቷል:: በስምንት ወራት ውስጥም የተገኘው ገቢ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያረጋግጣል::
ግድቡ በአሁኑ ወቅት በስድስት ዩኒቶች ኀይል እያመነጨ እንደሚገኝም መረጃው ያክላል:: ሁለቱ እያንዳንዳቸው በሙሉ አቅማቸው 375 ሜጋ ዋት ኀይል፤ ቀሪዎቹ አራቱ ዩኒቶች ደግሞ 400 ሜጋ ዋት ኀይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸው አስታውቀዋል::
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኀይልን በማመንጨት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል:: የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ሽፋንን 75 በመቶ ያሳድጋል:: የሕዳሴ ግድቡ አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኀይል ያመነጫል ተብሎም ይጠበቃል::
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኅይል በ2016 ዓ.ም እንዳስታወቀው ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ከምታመነጨው ኀይል እስከ 13 በመቶ የሚሆነውን ወደ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ በሽያጭ በማቅረብ በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል:: ወደ ፊትም ዓመታዊ የኅይል ሽያጭ ገቢው አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተገልጿል::
ሕዳሴ በመጭው መስከረም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት፣ 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የሕዳሴን ግድብን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል:: የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ በመጭው መስከረም በድምቀት ለማስመረቅ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል:: የህዳሴ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ልማት መሸጋገሩም የተፋሰሱን ሀገራት ተጎጂ የሚያደርግ ሳይሆን ለቀጣናዊ የጋራ ልማት በረከት እንደሚሆን አረጋግጠዋል::
ጠቅላይ ሚኒሥትሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሱዳን እና ግብጽን ጨምሮ በሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት እንደማያመጣባቸው በጊቤ ሦስት የኀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ላይ ተነስቶ የነበረውን ውዝግብ በማሳያነት አንስተዋል:: በወቅቱ ኢትዮጵያ የምታከናውነው የኅይል ማመንጫ ግድብ የኬንያውን ቱርካና ሀይቅ ሊያደርቀው ይችላል የሚል ስጋት ተነስቶ እንደነበር አስታውሰዋል:: ጊቤ ሦስት ተጠናቆም ግን የቱርካና ሀይቅ ሞልቶ ፈተና መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚንሥትሩ፤ ሕዳሴም ለግብጽም ሆነ ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት በረከት እንጂ ስጋትን ይዞባቸው እንደማይመጣ አስታውቀዋል::
“የግብጹ አስዋን ግድብ ሕዳሴ በመገደቡ ብቻ አንድ ሊትር ውኃ አልቀነሰም፤ ወደ ፊትም ኢትዮጵያ እስከበለጸገች እና እስካለች ድረስ የግብጽ ወገኖቻችንን ጉዳት እኛ አናይም:: ፍላጎታችን ተባብሮ በጋራ ማደግ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ልማት ልማታችሁ ነው፤ የሚመነጨውም ኀይል ሁሉንም ጎረቤት ሀገራት የሚያዳርስ ነው” ሲሉ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ልማትን መርህ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል::
“እኛ እያልን ያለነው በራሳችን ምድር እና ሀብት እየተሠራ ያለውን ልማት ‘አትሥሩ‘ አትበሉን ነው እንጂ ከግብጽ ጋር አሁንም ለመነጋገር እና ለመደራደር ዝግጁ ነን” ሲሉ ኢትዮጵያ የያዘችውን ”በጋራ እንጠቀም” አቋም ዛሬም አረጋግጠዋል::
”ግብጽ በተደጋጋሚ የምታነሳው ‘ድርቅ ሲያጋጥም እጎዳለሁ‘ ለሚለው ስጋት ግብጽ በድርቅ የምትጎዳው ድርቁ ኢትዮጵያን ካጠቃት ነው” ሲሉ መከራከሪያቸውን ውድቅ አድርገዋል:: ድርቅ የኢትዮጵያ ስጋት ሆኖ ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ተጎጂ እንዳያደርግ አረንጓዴ ልማት ላይ በስፋት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል:: በመሆኑም የተፋሰሱ ሀገራት ቅንነትን መሠረት ያደረገ የጋራ ልማትን መርህ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል::
”የጋራ ሀብታችን የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ የምናስመርቅ በመሆኑ ሀገራቱ በዚህ ታላቅ ዝግጅት ላይ እንዲገኙ ግብዣ አቅርበዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም