ሕዳሴ ግድብ የይቻላል ወኔን ያጎናጸፈ ነው  –  የግድቡ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት   

0
77

ኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድቧን ከመመረቅ የሚያስቀራት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም በመንግሥት፣ በመላው ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ርብርብ የተገነባ ነው።

ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ስለ ሕዳሴው ግድብ የሚነገረውን አፍራሽ መልዕክት የሚመክት እውነታን መናገር እንደሚገባ አመላክቷል።

 

መንግሥት እና ሕዝቡ በይቻላል መንፈስ በድል እያከናወነው ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የጽሕፈት  ቤቱ  ምክትል  ዋና  ሥራ         አስፈፃሚ ፍቅርተ  ታምር  በመግለጫቸው  ያብራሩት፡፡

በግድቡ  ሥራ ኢትዮጵያዊያን ደማቸውን ያፈሰሱበት እና ላባቸውን ጠብ ያደረጉበት ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል።

 

ላለፉት 14 ዓመታት ለግድቡ ግንባታ ምንም ዓይነት ገንዘብ ከውጭ ብድር እና ዕርዳታ እንዳልተደረገ ለሕዝቡ ሲገለፅ መቆየቱንም አስታውሰዋል። በኢትዮጵያዊያን ብርቱ ርብርብ የተገነባውን ግድባችንን ከመመረቅ የሚያስቀረን አንዳችም ምክንያት የለም ሲሉም ተደምጠዋል።

 

ኢትዮጵያውያን በሐሳብ፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት እና በሞራል በመረባረብ የተመዘገበው ስኬት በትውልድ የሚዘከር ህያው ድል ነው ብለዋል፡፡

ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ሪቫኑ እስከሚቆረጥበት ዕለት ድረስ ይቀጥላል ያሉት ወይዘሮ ፍቅርተ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ብዙ ቦንድ እየተሸጠ ስለመሆኑም ገልጸዋል። አሁንም ኅብረተሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

 

ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ አሸናፊነት እና የይቻላል ወኔን ያጎናጸፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያውያን አንድነት የተባበረ ክንድ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በመጪው መስከረም ወር 2018 ዓ.ም ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሐምሌ 21  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here