የአማራ ክልል የምርትና ግብይት፣ የገበያ አረጋጊ፣ የሕገ ወጥ እና ፀረ – ኮንትሮባንድ ጥምር ግብረ ኃይል የወንጀል ጉዳይ ክትትል ቴክኒክ ኮሚቴ የ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል። በግምገማው ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተሠራው ሥራ ቀርቧል::
የገበያ ሥርዓቱን ከሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ነፃ ለማድረግ እና ሕጋዊ የገበያ ሥርዓትን ለማጠናከር የወንጀል ጉዳዮች ክትትል ቴክኒክ ኮሚቴ ተደራጅቶ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ፈጠራ፣ በሕገ ወጥ ተግባር በተሰማሩት ላይ ሕጋዊ የቅጣት ርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረጉ ተገልጿል። ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ መስመሩ እንዲገቡ መደረጉም ተመላክቷል።
የቴክኒክ ኮሚቴው በ2018 በጀት አንደኛ ሩብ ዓመት የተከናወኑትን ተግባራት ሪፖርት ያቀረቡት የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ አቶ ዓለምነህ ሹመቴ ናቸው፤ ጥራት የጎደለው ምርት ለገበያ የሚያቀርቡ፣ ደረጃውን ባልጠበቀ መሣሪያ የሚያመርቱ፣ ያለደረሰኝ እና በሐሰተኛ ደረሰኝ የሚሸጡ፣ ምርትን የሚደብቁ አካላትን እና ያለፈባቸውን ምርቶች ማስወገድን በተመለከተ የተሠሩ ተግባራት ተነስተዋል።
ወንጀል ሠርተው የሚጠፉ ሰዎች እና በሕገ ወጥ ንግድ የተሠማሩትን ተከታትሎ ተገቢውን ሕጋዊ የእርምት ርምጃ መውሰድ እንደሚገባ በተሳታፊዎች ተነስቷል፤ ግብረ ኃይሉ ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል፣ ተንቀሳቃሽ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ፈጣን ሕጋዊ ርምጃ ለመስጠት ተባብሮ መሥራት፣ በሕገ ወጥ ኬላዎች የሚሰበሰበው ክፍያ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ በማድረግ በሸማቹ ላይ ጫና እየፈጠረ ስለሆነ ማስተካከል እንዲሁም ሕገ ወጥ ንግድ የሚበዛባቸውን አካባቢዎችን ለይቶ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ የሚሉትም የተነሱ ተጨማሪ ሐሳቦች ናቸው።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም “የንግድ ሥርዓቱ በሕገ ወጦች ተጠልፎ ሕጋዊ ነጋዴዎች ከንግድ ሥርዓቱ እንዳይወጡ፣ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት፣ የመንግሥት ገቢ እንዳይቀንስ፣ የምርት እጥረት እንዳያጋጥም እና የተረጋጋ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር በትብብር መሥራት ያስፈልጋል” ብለዋል።
ቢሮ ኃላፊው እንዳሉት ሕጋዊ የገበያ ሥርዓትን ለማጠናከር የወንጀል ጉዳዮች ክትትል የቴክኒክ ኮሚቴ ተደራጅቶ ሥራዎችን ሲፈጽም ቆይቷል። ግንዛቤ ፈጠራ፣ በሕገ ወጦች ላይ ርምጃ መውሰድ እና ሕገ ወጥ ንብረትን መውረስ ደግሞ ከተከናወኑት መካከል ይጠቀሳሉ። ተቀናጅቶ በመሥራት የተገኙ ውጤቶችም ናቸው።
ዘርፉ ለሕገ ወጦች ያለው ተጋላጭነት ሰፊ መሆኑን ያነሱት አቶ ብርሃኑ ችግሩን በቶሎ ማስቀረት አይቻልም ባይ ናቸው። ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ደግሞ ወሳኝ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ በኮሚቴው በሩብ ዓመቱ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፈጠሩን፤ ጥፋቶች እንዳይፈጸሙ መከላከል እና ከተፈጸሙም በሕግ የማስቀጣት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል::
አቶ ሙሉጌታ እንዳሉት ለ26 ሺህ 997 ነጋዴዎች የበር ለበር ስልጠና ተሰጥቷል፤ በ150 ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ክስ ተመስርቶ በ26 መዝገቦች ላይ ፍርድ ተሰጥቷል:: 29 ሚሊዮን 96 ሺህ 163 ብር ዋጋ ያለው ንብረት (ኤግዚቢት) ለመንግሥት ገቢ ሆኗል፤ ከዋሥትና 745 ሺህ ብር እንዲሁም ከቅጣት አንድ ሚሊዮን 795 ሺህ 500 ብር ገቢ ተደርጓል::
አቶ ሙሉጌታ አክለውም “የቴክኒክ ኮሚቴው ግንዛቤ መፍጠሩ፣ ክትትል እና ቁጥጥር ያደረገበት ሂደት፣ ያደረገው ድጋፍ እና አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረጉ የሚበረታታ ነው” ብለዋል። በምሥራቅ አማራ የተሠራውን ቅንጅታዊ ተግባር ደግሞ ሕገ ወጥ ንግድን የመከላከል ውጤታማ ሥራ በማሳያነት አንስተዋል::
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተዘረጉ ኬላዎች ያልተገባ ገቢ መሰብሰብ በሚል ቅሬታ የተነሳባቸው ናቸው፤ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው 71 ኬላዎች እንዲነሱ የተላለፈውን መመሪያ ፖሊስ እንደሚያስፈጽም ነው ያመላከቱት:: ወንጀለኞች ተደራጅተው ስለሚንቀሳቀሱ ግብረ ኃይሉም ከዚያ በላይ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል::
ሕገወጥ ነጋዴዎች ሕገ ወጥነታቸውን በብሔር፣ በአካባቢ እና መሰል ሽፋንን ለመጠቀም እንደሚሞክሩ አንስተዋል:: ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ንብረታቸው እንጂ ባለቤቶቹ በአብዛኛው አይያዙም፤ በመሆኑም ችግሩን ከስሩ ለመፍታት ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደሚገባ አብራርተዋል::
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፈንታው ፈጠነ በአማራ ክልል ለዓመታት ያጋጠመው ግጭት ለሕገ ወጥ ንግድ መስፋፋት ምክንያት እንደሆነ አንስተዋል:: የቴክኒክ ኮሚቴው መጠንከር እንዳለበት በማንሳት በየቦታው ያለው ሕገ ወጥ የኬላ ቀረጥ የምርት ዝውውርን በመገደብ በሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ የዋጋ ውድነት እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል:: ኬላዎች እንዲነሱ መመሪያ መተላለፉ ይታወሳል፤ በመሆኑም የተላለፈውን መመሪያ በፍጥነት መተግበር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት::
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አያሌው አባተ (ዶ/ር) በክልሉ ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴን ማስፈን፣ የሸማቹን መብት እና ጥቅም መጠበቅ፣ ሕገ ወጥነትን መከላከል እና ሕጋዊ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የግብረ ኃይሉ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።
የሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥሩ የሸማቹን ማኅበረሰብ ችግር የሚፈታ መሆን እንዳለበትም በመግለጽ ለሕጋዊ ነጋዴው ነጻነት መስጠት እንደሚገባ አክለዋል፤ እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ ከሕግ ተጠያቂነት ሸሽቶ መነገድን ማክሰም ይገባል።
ወቅቱ ሰብል የሚሰበሰብበት ነው፤ በመሆኑም የገበያ ሰብሎች በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ እንዳይወጡ በትኩረት መሥራት ይገባል። የአሠራር መጣረስ እንዳይኖርም ተቋማት የሚሠሩባቸውን የሕግ ማዕቀፎች ለግብረ ኃይሉ እንዲያስገነዝቡ አሳስበዋል።
የቴክኒክ ኮሚቴው በጋራ አቅዶ መሥራቱ፣ እንዲሁም በየሩብ ዓመቱ አፈጻጽምን በመገምገም አጠናክሮ ወደ ተግባር መግባቱ እና የሚመለከታቸው ተቋማት የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ውጤታማ ሥራ ለመፈጸም እንዳስቻለ አንስተዋል።
የክልሉ የፀጥታ መደፍረስ ለኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ ቁጥጥር ሥራው ተግዳሮት መሆኑ፣ የክልሉ ኮሚቴ አደረጃጀት ወደ ዞን፣ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች አለመውረዱ እና ተግባራዊ አለመደረጉ እንዲሁም የትኩረት ማነስ በክፍተት የተለዩ ጉዳዮች ናቸው።
በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የሚፈጠርን የመረጃ ልውውጥ ክፍተት ለማስቀረት ዲጂታላይዝድ ማድረግ፣ ሕገ ወጥነት በሚበዛባቸዉ አካባቢዎች የመስክ እና ልምድ ልውውጦችን ማካሄድ፤ በኮንትሮባንድ እና ንግድ ማጭበርበር ዙሪያ በተናጠልም ሆነ በቅንጅት የጥናት ሥራዎችን በመሥራት ተገቢ ርምጃ መውሰድ እና ለሚመለከታቸውም አካላት ማስተላለፍ በመፍትሔነት ተጠቅሰዋል፤ በቀጣይም በትኩረት ይሠራባቸዋል ተብሏል።
::
የሕግ አንቀጽ
የኤሌክትሮኒክ ንግድ ምንነት
የኤልክትሮኒክ ግብይት ከኦንላይን ችርቻሮ እስከ ኤልክትሮኒክ አገልግሎቶች ድረስ ያለውን ሁሉ የሚያጠቃልል የግብይት ዘዴ ነው፤ በሕላዊ የነበረውን ንግድ በበይነ መረብ መንገድ በማድረጉ ምክንያት ግብይቱ እንዴት ይመራ? በግብይቱ የሚሳተፉ ሸማቾች ከመደበኛው ግብይት ሸማቾች ጋር እኩል እንዴት ጥበቃ ይደረግላቸው? በኤሌክትሮኒክ የሚነሱ ሌሎች የሕግ ጉዳዮች በምን መለኩ ምላሽ ያግኙ? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ ቁጥር 1205/2012 ዓ.ም ተደንግጎ ወጥቷል።
በኢትዮጵያ አሁን በሥራ ላይ ያለውና የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽንን የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 1205/2012 በአንቀጽ 2 (12) ላይ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ፤ ማለት ኢንተርኔትን ወይም የመረጃ መረብን በመጠቀም የሚደረግ የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ግብይት ወይም ልውውጥ ነው፤ በማለት ትርጉም ሰጥቶታል።
ምንጭ፡- ፍትሕ ሚኒስቴር
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


