ሕጉ ምን ይላል?

0
43

ኢንቨስትመንት  /መዋዕለ ንዋይ/ ማለት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 1180/2012 አንቀጽ (2) ንኡስ አንቀጽ (1)  ላይ እንደሰፈረው አዲስ ድርጅት ለማቋቋም ወይም ነባር ድርጅት ሙሉ በመሉ ወይም በከፊል ለመግዛት፣ ለማስፋፋት ወይም ለማሸሻል ባለሀብቶች በገንዘብ ወይም በአይነት ወይም በሁለቱም መንገድ የሚውል የካፒታል መዋጮ ነው::

የአሚኮ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ አቶ ደመቀ ይብሬ እንዳሉት ባለሀብት ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ካፒታሉን ሥራ ላይ ያዋለ የሀገር ውስጥ ወይም የውጭ ዜጋ ማለት ነው:: የሀገር ውስጥ ባለሀብት ሲባል ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜግነት  ያለው ሆኖ ካፒታሉን ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ያዋለ ወይም ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን የተቋቋሙ ማለት ነው:: ለአብነት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ህብረት ሥራ ማህበራት…ተጠቃሽ ናቸው:: አዋጁ የውጭ ባለሀብት የሚላቸው ካፒታላቸውን ከውጭ  ወደ ሀገር  ውስጥ በማስገባት በሥራ ላይ ያዋሉ የውጭ ሀገር ዜጐችን እና  የውጭ ሀገር ዜግነት  ያላቸው ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑም ባለሙያው አብራርተዋል::

ባለሙያው አዋጁን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት ኢንቨስትመንት በሀገሪቱ ቀልጣፋ፣ ፈጣን፣ አካታች እና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ  እና ማህበራዊ ልማት እንዲመጣ በማድረግ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽል የሥራ ዘርፍ ነው:: ብሔራዊ የኢኮኖሚ ተወዳደሪነትን ማጠናከርም ሌላው ዓላማው ነው:: በተለይም በልዩ የልማት /አስቻይ/  ዘርፎች ላይ ኢንቨስትመንትን የማስደግ ሚናው ከፍተኛ ነው::

ኢንቨስትመንት ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ ዘርፉን ተከትሎ የሚመጣውን የቴክኖሎጅ፣ የዕውቀት እና የክህሎት ሽግግር ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል:: በተለይ የውጭ ባለሀብቶች በሚሳተፉባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች የእውቀት እና የክህሎት ሽግግር ይጠበቃል:: ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንዲሁም በኢኮኖሚው ውስጥ የግል ዘርፉን ሚና ማሳደግ የኢንቨስትመንት ሌላው ጠቀሜታ መሆኑን ባለሙያው አብራርተዋል::

በኢንቨስትመንት መስኮች  የሚሰማሩ ባለሀብቶች መነሻ ካፒታላቸውን በተመለከተም አቶ ደመቀ ሲናገሩ፤ በመርህ ደረጃ ማንኛውም ባለሀብት በፈለገው የኢንቨስትመንት ዘርፍ የመሰማራት   መብት አለው:: ነገር ግን ባለሀብቱ የሚሰማራበት የኢንቨስትመንት መስክ ከሕግ እና ከህብረተሰቡ ጤንነት ወይም ደህንነት የሚቃረን ከሆነ አይፈቀድም:: ዘርፉ ለሀገር ውስጥ ዜጐች ብቻ የተፈቀዱ እና ለውጭ ዜጐች የተከለከሉ መስኮችም  አሉት፤ ይህም የተደረገው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለማበረታታት ታስቦ እንደሆነ ባለሙያው አብራርተዋል::

እንደ አቶ ደመቀ ገለጻ የኢንቨስትመንት ክንውን መስኮች ከመንግሥት ጋር በቅንጀት የሚከናወኑ፣  ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ የተከለሉ እንዲሁም  ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በቅንጅት የሚሠሩ አሉ:: አዋጅ  ቁጥር    1180/2012 ለማስፈጸም በወጣ ደንብ ቁጥር 474/2012 ላይ በዝርዝር ተቀምጠዋል:: ለምሳሌ የጦር መሣሪያ፣ ጥይት፣ ለጦር መሣሪያነት የሚውሉ ወይም ደግሞ የጦር መሣሪያ ለመሥራት የሚያገለግሉ ፈንጅዎችን ማምረት፣ የኤሌክትሪክ ኀይል ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትና መላክ፣ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ፈጣን የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት … ከመንግሥት ጋር በቅንጅት የሚሠሩ የኢንቨስትመንት መስኮች ናቸው::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንቨስትመን ክንውን መስኮች ተብለው የተፈቀዱት ደግሞ የመጀመሪያ እና የመካከለኛ ደረጃ የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ነዳጅ እና የነዳጅ ምርቶችን ማቅረብ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረተን ምርት በጅምላ መሸጥ እና የኤሌክትሮኒክስን ንግድ ሳይጨምር ጅምላ ንግድ ፣ ቡታጋዝን እና ቢትመንን  ሳይጨምር ጥሬ ቡና፣ የቅባት እህል፣ ጥራጥሬ ማእድናት፣ ቆዳና ሌጦ፣ ከደረጃ አንድ በታች የሆነ የኮንስትራክሽን እና የቁፋሮ አገልግሎት፣ በኮከብ ደረጃ  ያለውን ሳይጨምር ሆቴሎች፣ ሎጅዎች እና ሪዞርቶች ወዘተ ደግሞ  ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተፈቀዱ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ናቸው::

በሀገር ውስጥ እና በውጭ ባለሀብቶች  በቅንጅት እንዲሠሩ የተፈቀዱ የኢንቨስትመንት ዘርፎች  ለምሳሌ እቃ የማስተላለፍ እና የመረከብ ውክልና አገልግሎት፣ የሀገር ውሰጥ የአየር ትራንስፖርት፣  ከ45 በላይ መቀመጫ ባለቸው አውቶቡሶች የሚሰጥ የሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት… ናቸው::

በውጭ ሀገር  የሚኖር ባለሀብት ሀገር ውስጥ ካለ ባለሀብት ጋር በቅንጅት  ለሚያከናውነው ኢንቨስትመንት የውጭ ባለሀብቱ የሚኖረው የካፒታል ድርሻ ከ49 በመቶ መብለጥ እንደማይችልም ባለሙያው ጠቁመዋል::  ለዚህም የውጭ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ሲሰማሩ የሚጠየቁት ዝቅተኛ የካፒታል መጠን አለ:: ማንኛውም የውጭ ባለሀብት በአዋጁ በተፈቀደለት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ለአንድ ኘሮጀክት ከ200 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር መመደብ አለበት::

ከሀገር ውስጥ ባለሀብት ጋር በቅንጅት ሚሠራ ከሆነ  ግን 150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ይጠይቃል:: ነገር ግን በኢንጅነሪነግ፣ በአርክቴክቸር እና ከኮንስትራክሽን ጋር ተዛማጅ በሆኑ ሥራዎች፣ በቴክኒክ ምርመራ፣ በአሳታሚነት  በውጭ ባለሀብት   በተናጠል የሚከናወን ከሆነ 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፤ ከሀገር ውስጥ ባለሀብት ጋር በቅንጅት የሚሠራ ከሆነ  ደግሞ 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መነሻ ሆኖ ተደንግጓል:: በልዩ ሁኔታ መነሻ ካፒታል አስፈላጊ ሳይሆን የውጭ ባለሀብቶች የሚሳተፉባቸው መንገዶችም በአዋጅ መኖራቸውን ባለሙያው ለአሚኮ ገልፀዋል::

መስፈርቶችን ላሟሉ ባለሀብቶች ፈቃድ ለመስጠት የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች በአዋጁ በአንቀጽ (10) ላይ መስፈራቸውን አቶ ደመቀ ጠቁመዋል::  የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ፣ ሁለቱ በቅንጅት እንዲሁም እንደ ሀገር ውስጥ ባለሀብት የተቆጠሩ እና የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ተሰጥቷቸው በዘርፉ የሚሰማሩ ሁሉ የግድ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማውጣት እንዳለባቸው ተለይተዋል::

ፈቃዱን ለማግኘትም በደንቡ ላይ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሀብቶች ተብለው መስፈርቶች ተለይተው ሰፍረዋል:: ለምሳሌ የሀገር ውስጥ ባለሀብት የፈቃድ ጥያቄ ለማቅረብ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀው ቅጽ  በጽሑፍ በኤሌክትሮኒክ ብቻ መሙላት፣ ባለሀብት የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚያቀርበው በውክልና ከሆነ የውክልና ማስረጃ፣ የመታወቂያ ቅጅ/ኮፒ/ እንዲሁም  የቅርብ ጊዜ ሁለት ፓስፖርት መጠን ያለው ጉርድ ፎቶ ማቅረብ የግድ ነው:: ፈቃድ ጠያቂው የንግድ ማህበር ከሆነ ደግሞ የማህበሩን መመስረቻ ጽሑፍ፣ ደንቡን እና የንግድ ምዝገባ የምስክር ወረቀቱን እንዲሁም የእያንዳንዱን አባል መታወቂያ ለተቋሙ መቅረብ አለበት:: የኢንቨስትመንት ፈቃድ ጠያቂው የውጭ ባለሀብት ከሆነም የሚጠየቀው ከሀገር ውስጥ ባለሀብት ጋር ተመሳሳይ ነው:: በዚህ መንገድ ተቋሙ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ጥያቄውን ይመረምራል፤ መረጃው ተቀባይነት ካገኘ ወዲያውኑ ፈቃዱን ይሰጣል:: የባለሀብቱ ጥያቄ ውድቅ ከሆነ ደግሞ   ምክንያቶችን ጠቅሶ  በሦስት የሥራ ቀናት ምላሽ መስጠት አለበት::

የኢንቨስትመንት እድሳትን በተመለከተም አዋጁ ላይ የተቀመጠው ባለሀብቱ ፈቃድ ካወጣ በኋላ ምርቱን ለገበያ ማዋል ወይም አገልግሎቱን እስኪጀምር ድረስ በየዓመቱ ፈቀዱ መታደስ አለበት:: የንግድ ፈቃድ ከወጣ በኋላ ግን የንግድ ሥራ ፈቃድ ማሳደሱ  አስፈላጊ አይደለም:: የእድሳት ጥያቄው የሚቀርበው  የፈቃድ ጊዜው ካበቃ በአንድ ወር ውስጥ እንደሆነ ባለሙያው አስገንዝበዋል:: ባለሀብቱ ፈቃድ ወስዶ ኘሮጀክቱን ሳይጀምር ሁለት ዓመት ካለፈው ደግሞ  ፈቃዱ እንዲሰረዝ ይደረጋል፤ በቂ ምክንያት ካለው ግን ፈቃዱን ማሳደስ ይችላል::

ፈቃድ የሚታገድበት ሁኔታ በአዋጅ አንቀጽ (13) ላይ ተመልክቷል:: ይህም የሚጠየቀውን መረጃ ወይም የአፈጻጸመ ሪፖርቱን  በሦስት ወራት በትክክል ካላቀረበ፣ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት የተሳሳተ ሪፖርት ካቀረበ፣ ፈቃዱ ወይም እድስቱን በማታለል ወይም ሀሰተኛ ማስረጃ ካቀረበ መረጃው እንደተገኘ/እንደተደረሰበት/ ይነጠቃል:: ፈቃዱን ከተሰጠው ዓላማ ውጭ ከተጠቀመ፣ ያለበቂ ምክንያት ፈቃዱን ካላሳደሰ፣ በአዋጅ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ኘሮጀክቱን ካላጠናቀቀ ወይም  እንደማያጠናቅቅ ከታመነበት እና ሌሎች የኢንቨስትመንት ሕጐችን ከተላለፈ ፈቃዱ ይታገዳል::

እገዳው ተግባራዊ ሚደረገው ለእገድ ምክንያት የሆኑትን ከ60 የሥራ ቀናት ባልበለጠ እንዲያስተካክል ወይም በቂ ምላሽ እንዲያቀርብ የጽሐፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል:: በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የዕገዳውን ምክንያት ካላስተካከለ ወይም በቂ ምላሽ ካልሰጠ ፈቃዱ ይታገዳል፡፡ ፈቃዱ በዚህ ሁኔታ የታገደበት ባለሀብት ለዕገዳው ምክንያት የሆነውን እንዲያስተካክል የአንድ ዓመት ጊዜ ይሰጠዋል፡፡

ፈቃድ ተሰረዘ የሚባለው ደግሞ ለምሳሌ በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለፈቃዱ ዕገዳ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ካላስተካከለ፣ መሬት ወስደው ሁለት ዓመት ሙሉ አጥረው ወደ ትግበራ ያልገቡ ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው ከመታገድ አልፎ ይሰረዛል:: የኢንቨስትመንት ሥራቸውን በፈቃዳቸው ከተው የተሰጣቸውን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለሌላ ዓለማ ካዋሉ ወይም ከሕግ ውጭ ለሌላ ሰው ካስተላለፉም ፈቃዳቸው ይሰረዛል:: በሂደቱ ላይ ግን የሰረዛ ርምጃው የሚወስድበት ምክንያት ለባለሀብቱ በጽሑፍ መገለጥ አለበት::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ባለሀብቱም በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተያየት  በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ማሳወቅ አለት:: ነገር ግን ባለሀብቱ በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ምላሽ ካልሰጠ ወይም ምላሹ በመ/ቤቱ በኩል ተቀባይነት ከሌለው ወደ ሥረዛ ይኬዳል:: በዚህ መንገድ ፈቃዱ የተሰረዘበት የውጭ ባለሀብት ከሆነ እስከ አንድ ዓመት ድርስ አዲስ ፈቃድ ማውጣት አይችልም:: በባለሀብቶች እና በኢንቨስትመንት ተቋሙ በኩል ቅሬታ ሲፈጠር ደግሞ አግባብ ላለው የኢንቨስትመንት ተቋም ማቅረቡ ይቻላል:: መሥሪያ ቤቱም የቀረበለትን አቤቱታ ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ መፍታት ይኖርበታል:: ባለሀብቱ መ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ካልረካ ደግሞ ቅሬታውን በፌዴራል ደረጃ ከሆነ በጠቅላይ ሚኒሥትሩ እና በአማራ ክልል ደግሞ በርእስ መስተዳድሩ ለሚመራው የኢንቨስትመንት ቦርድ ማቅረብ ይቻላል::

በፌዴራል ደረጃ ባለሀብቱ ጥያቄውን ለቦርዱ ማቅረብ ያለበት የኢንቨስትመንት መ/ቤቱ ምላሹን ባሳወቀው በ30 የሥራ ቀናት እንዲሁም በአማራ ክልል ደግሞ በ20 የሥራ ቀናት እንደሆነ ባለሙያው አሳውቀዋል:: የኢንቨስትመንት ተቋሙም ውሳኔ በሰጠ በሰባት የሥራ ቀናት  ውስጥ ትክክለኛው የውሳኔ ግልባጭ ለባለሀብቱ መስጠት አለበት::

ቦርዱ በበኩሉ አቤቱታ በቀረበለት በ90 ቀናት  እንዲሁም የክልሉ ቦርድ ደግሞ በ30 የሥራ ቀናት ተገቢ ያለውን ውሳኔ መስጠት  አለበት:: በመጨረሻም ቦርዱ ውሳኔ በሰጠ  በሰባት የሥራ ቀናት ውሳኔውን ለባለሀብቱ የማሳወቅ ግዳታ እንዳለበት ባለሙያው አስገንዝበዋል::

 

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የህዳር  8  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here