ሕጻኑ “ዲጄ”

0
216

እንዴት ሰነበታችሁ ልጆች? ሳምንት ስንሰናበታችሁ በሌላ አዲስ ታሪክ እንደምናገኛችሁ ቃል ገብተን ነበር፤ እነሆ ለዚህ እትማችን ደግሞ በዓለማችን ላይ ትንሹ የሙዚቃ አጫዋች (ዲጄ) ስለሆነው ደቡብ አፍሪካዊው አርክ ጁኒየር ተሰጥኦ የምንላችሁ ይኖረናል::

ደቡብ አፍሪካዊው አርክ ጁኒየር ገና በሦስት ዓመት ዕድሜው ሙዚቃ አጫዋች (ዲጄ) መሆን የቻለ ነው::ጁኒየር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚዘጋጀው የደቡብ አፍሪካ የተሰጥኦ ውድድር  ወይም “ጎት ታለንት” ላይ ሥራውን ሲያቀርብ ዕድሜው ገና ሦስት ብቻ ነበር፤ በዚህም በትንሽ ዕድሜው በተሰጥኦ ውድድር ያሸነፈ ብቸኛው ሕጻን ሆኖ ስሙ በክብር ሰፍሯል::

የትንሹ ዲጄ ጁኒየር ተሰጥኦ መጎልበት የጀመረው በአባቱ ድጋፍ ነው:: የጁኒየር አባት የሙዚቃ አጫዋች (ዲጄ) ባለሙያ ሲሆኑ ልጃቸው ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር በመረዳት እሳቸው የሚጠቀሙባቸውን የሙዚቃ ማጫወቻዎች ልጃቸውም እንዲጠቀምባቸው ይፈቅዱለት ነበር:: የጁኒየር አባት የልጃቸውን ተሰጥኦ ለይተው ከሕጻንነቱ ጀምረው ስላገዙትም የዓለማችን ትንሹ ዲጄ የእሳቸው ልጅ እንዲሆን አስተዋጽኦዋቸው የጎላ ነው::

ጁኒየር የደቡብ አፍሪካው የተሰጥኦ ውድድር (ጎት ታለንት) ላይ ተወዳድሮ ካሸነፈ በኋላ በአሜሪካው ጎት ታለንት ላይም ችሎታውን ማሳየት ችሏል:: ጁኒየር እ.አ.አ. በ2017 በአሜሪካ እና በእንግሊዝ ጎት ታለንቶች ላይ ተወዳድሮ ለፍጻሜ በቅቷል:: በእነዚህ ውድድሮቹም በአምስት ዓመቱ ለዚህ ክብር የበቃ ትንሹ ዲጄ ተብሎ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሙን ማስፈር ችሏል::

ምንም እንኳን አሁን ላይ የዲጄ ጁኒየር ክብረ ወሰን በኤዢያዊ ሌላ ታዳጊ ቢሻሻልም፣ ጁኒየር በአፍሪካ ካሉ ሕጻናት ባለተሰጥኦዎች አንዱ ሆኖ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል::

ልጆች፣ ከዚህ ታሪክ የምንማረው ወላጆች በልጆቻቸው ልዩ ተሰጥኦ ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚችሉ ነው፤ በተጨማሪም ልጆች ከትምህርታቸው በተጨማሪ ያላቸውን ተሰጥኦ በማሳደግ ለተሻለ ክብር እንደሚበቁም ተገንዝበናል:: ሳምንት በሌላ ታሪክ እስክናገኛችሁ መልካም ሳምንት ይሁንላችሁ::

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here