መልካም አስተዳደር እያንዳንዱ የፖለቲካ አመራር እንዲሁም የሕዝብ አገልጋይ የህብረተሰቡን ጥቅም በማስቀደም በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን፤ መዋዕለ ነዋይ እንዲሁም ድርጅት በኃላፊነት እና በተጠያቂነት መምራትን ማለት ነው:: አሳታፊ፣ ግልጽ እንዲሁም ተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ የአሠራር ሂደት መከተልንም ያመለክታል::
ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በህብረተሰቡ ፍላጎት እና መግባባት ላይ መመስረታቸውን የሚያረጋግጥ የደሀ እና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጽ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ እንዲደመጥ የሚያደርግ ቁልፍ መሣሪያ እንደሆነም በ2016 እ.አ.አ የወጣው ስክሪኘድ ዶት ኮም (scribd.com) ዘገባ አመላክቷል::
መረጃው መልካም አስተዳደር (Good Governance) ማለት የመሰልጠን እና ያለመሰልጠን ወይም የደም፣ የዘር እና የቀለም ጉዳይ ሳይሆን የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የአስተሳሰብ እና የአመለካክት ውጤት ነው ማለት እንደሚቻል ጠቁሟል:: በአጠቃላይ መልካም አስተዳደር የኅሊና ስምምነት፣ አሳታፊነት፣ የሕግ የበላይነትን መከተል፣ መፍትሔ ያለው እና ውጤታማነት ፣ ተጠያቂነት ፣ግልጽነት፣ ለሕዝብ ምላሽ ለመስጠት የሚደረግ ዝግጁነት /ተቆርቋሪነት/፣ እኩልነት እና ሁሉን አቃፊነት እንደሆነ መረጃው ጠቁሟል::
ሔላሪ ክሊንተን እ. አ. አ. በ2009 ስለ ናይጄሪያ ሲናገሩ “መልካም አስተዳደር ለአንዲት ሀገር ወሳኝ ሚና ይኖረዋል:: ለኢትዮጵያም እንዲሁ ነው:: መንገድ ቢሠራ ፣ ሕንፃ ቢገነባ፣ አያሌ የሕዝብ ጥሪት ቢፈስም መልካም አስተዳደር ካልገነባን፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ካላዳበርን ብል እንደሚበላው ሳይታለም የተፈታ እውነታ ነው” ሲሉ ተደምጠው ነበር::
ቢሮክራሲ እና ዕድገት (Bureaucracy and Developmen) በሚል በ2021 እ.አ.አ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ደግሞ አስተዳደር ማለት ሁሉንም የማስተዳደር ሂደቶች፣ ተቋማት እና የጋራ ጉዳዮች የሚወሰኑበት እና የሚመሩበት የአሠራር ሂደት እንደሆነ ጠቁሟል። መረጃው መልካም አስተዳደር ለሚለው ደግሞ ከሰብዓዊ መብት አንፃር በዋናነት የመንግሥት ተቋማት የሕዝብ ጉዳዮችን በአግባቡ የሚያከናወኑበትን ፣ የሕዝብ ሀብትን የሚያስተዳድርበት እና የሰብዓዊ መብቶች መከበር ዋስትና የሚያገኙበትን ሂደት ያካትታል።
መልካም አስተዳደር የሚለው ጽንሰ ሀሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምምነት የተደረሰበት ትርጉም ባይኖርም የሰብዓዊ መብት መከበር ፣ የሕግ የበላይነት፣ የዜጎች ውጤታማ ተሳትፎ፣ የባለብዙ ተዋናዮች (የሕዝብ እና መንግሥት) አጋርነት፣ የፖለቲካ ብዝኃነት፣ ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንደሆነ ያሳያል። መረጃው አክሎም መልካም አስተዳደር ተቋማት ቀልጣፋ እና ውጤታማ የመንግሥት አሠራርን፣ ሕጋዊነትን፣ የዕውቀት ተደራሽነትን፣ መረጃ እና ትምህርትን፣ የሰዎች የፖለቲካ ሥልጣን ፍትሃዊነትን፣ ዘላቂነት እና ኃላፊነትን፣ አብሮነትን እና መቻቻልን የሚያጎለብቱ አመለካከቶች እና እሴቶች በሙሉ መገለጫዎቹ እንደሆኑ አስፍሯል::
ጥናቱ መልካም አስተዳደር ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ሂደቶችን እና የልማት ግቦችን ለማሳካት አስፈላጊ ከሆኑ ውጤቶች ጋር የተያያዘ ነው። ትክክለኛው የመልካም አስተዳደር ፈተና የሰብዓዊ /የሲቪል ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ/ መብቶችን ለማስከበር የተሄደበት ደረጃ እንደሆነም ጠቁሟል።
መልካም አስተዳደር የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት ለዜጎች የጤና፣ በቂ የመኖሪያ ቤት፣ በቂ ምግብ፣ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ፍትሃዊ ፍትሕ እና የግል ደህንነት መብትን በብቃት እያረጋገጡ ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ደግሞ ዋናው ዓላማ እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል::
ተመራማሪ እዮብ አሰለፈች ባልቻ መጋቢት 9/2007 ዓ.ም መልካም አስተዳደርን በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት ደግሞ “እ.አ.አ በ1989 ዓ.ም የዓለም ባንክ ‘የአፍሪካ ችግር የአስተዳደር ቀውስ ነው’ ሲል አወጀ ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መልካም አስተዳደር የሚለው ጉዳይ በአስተሳሰብ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው ጉዳይ መሆን ጀመረ። የዓለም ዓቀፍ ገንዘብ አበዳሪ ተቋማት በኢኮኖሚ ደከም ባሉት ላይ ጫና በሚያሳድሩበት ወቅት መተማመን ፣ ግልጽነት፣ የሕግ የበላይነት እና ሌሎች መርሃ ግብሮች እስካሁን ድረስ መልካም አስተዳደር ለሚባለው አዲስ መለያ መገለጫቸው ሆነው ዘለቁ” ይላሉ።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ብዙ ሀገራት ለዜጎቻቸው እንደ ጤና አጠባበቅ ፣ ትምህርት እና የመሳሰሉ ሰፊ የሕዝብ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ያላቸው ምኞት ከፍ ያለ እንደሆነ ደግሞ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲው ጥናት ያመላክታል።
ተመራማሪው እዮብ ግን ለአፍሪካ መልካም አስተዳደር ምርጥ የተባለ ከሌላ ቦታና ሁኔታ የተቀዳ ተሞክሮ በነባራዊው አውድ እና ዕውነታ ጋር የመጣጣም ዕድሉ ከፍተኛ ክፍተት ሲፈጥር ይታያል ይላሉ። ወጥ ያልሆነ ሕግና ስርዓት እንዲሁም የአፈጻጸም ሂደቶች አሉ ፤ በሀገራችን የመንግሥት እና የሕዝብ ተቋማት ጥናቶችን በውል ሳይገነዘቡ በዘመቻ መልክ ሲተገብሩ እንደነበር አስታውሷል::
አለማዳላት፣ የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነት እና መሰል መርሆዎች በሁሉም ቦታዎች መስፈን የመልካም አስተዳደር መገለጫዎች ናቸው:: ይህንን ካደረጉ መሪዎች ተጠያቂ አይሆኑም፤ ለሀገር እድገትም ፋይዳው ከፍ ያለ ነው::
የመልካም አስተዳደር ዲስኩር መሠረታዊ ውስንነት የሚመነጨው በኅብረተሰብ ውስጥ ላሉ ኢመደበኛ (መደበኛ ላልሆኑ) ግንኙነቶች ዕውቅና አለመስጠቱ ነው። በመልካም አስተዳደር ዲስኩር እና ተግባራት ውስጥ በትውውቅ፣ በትብብር እና በመግባባት የሚከወኑ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሒደቶች ቦታ የላቸውም። በእውነታው ዓለም ግን ይህን መሰል መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶች የግልም ሆነ የመንግሥት ሥራን ለማከናወን፣ ከዚያም ባለፈ የፖሊሲ አፈጻጸሞች ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው።
ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ቢያንስ መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶችን ችላ ማለቱ የመልካም አስተዳደርን ዲስኩር ገና ከመነሻው የጨነገፈ ያደርገዋል። የኢመደበኛ ግንኙነቶችን መሠረታዊ ሚና በተገቢው መልኩ መረዳት እና ማጤን አሉታዊ ተፅዕኗቸውን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር፣ አዎንታዊ ጎናቸውን ደግሞ ለማበረታታት እና ለማጠንከር ይረዳል። ምክንያቱም ኢመደበኛ ግንኙነቶች በቀበሌ ወይም በወረዳ ደረጃ ያለን ጉዳይ ከማስፈጸም ዘልቆ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመሰሉ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ውስጥ ያሉ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳረፊያ መንገዶች ናቸውና።
ሕግን የተከተሉ የአሠራር ሂደቶችን መከተል ለዜጎች አስፈላጊውን አገልግሎት መስጠት ላይ ማተኮር ነው:: ይህንን በማያደርጉ ግን የሚወሰድ ርምጃ ከሌለ ለሀገራት የተበላሸ አሠራር መሥፈን የሚኖረው ተፅዕኖ የጎላ እንደሚሆን ነው መረጃዎች የጠቆሙት::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም