ብሔራዊ ፓርኩ በኬኒያ በሰሜናዊ ጫፍ ከኢትየጵያ ጋር በምትዋሰንበት ማንዴራ አምባ ነው የሚገኘው፡፡ ስፋቱም 876 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡
ፓርኩ በ1989 እ.አ.አ ቀጣናውን አቆራርጦ በሚፈሰው የዳዋ ወንዝን ተንተርሶ በርካታ የዱር እንስሳት እና አዕዋፍ መገኛነቱ ታምኖበት ነው በአዋጅ ማልካማሪ ብሔራዊ ፓርክ በፓርክነት የተሰየመው፡፡
ዓየር ንብረቱ ደረቅ እና ሞቃታማ ነው፡፡ ቀጣናው በቁጥቋጦ እና ሳር የተሸፈነ ሲሆን የፓርኩን ክልል አቆራርጦ በሚያልፈው የዳዋ ወንዝ ግራ እና ቀኝም ዘንባባ እና ሳሳ ያለ ደን ለብሷል፡፡ ለፓርኩ ህልውና ዋና ዋና ከሚባሉት የዱር እንስሳቱ እና እፅዋቱ መስህቦች ሸለቆዎች፣ ኮረብታዎች፣ የዱር እንስሳት እና ወንዙ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በፓርኩ ከሚገኙ የዱር እንስሳት ቀጭኔ፣ የሜዳ ፍየል፣ ዥንጉርጉር ጅብ፣ ዓዞ ይጠቀሳሉ፡፡ ፓርኩን ዓመቱን ሙሉ መጐብኘት የሚቻል ሲሆን ለዚህ ደግሞ በቀጣናው ከፍ ያለ ዝናብ የማይጥል፣ ጥቅጥቅ ደን የሌለው መሆኑ ነው በየድረ ገፆች ለንባብ የበቃው፡፡ ዓየር በተሞላ ፊኛ ወይም “ባሉን” ቀጣናውን በመዘዋወር ያሉትን ተፈጥሮዊ ሀብቶች መቃኘት እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡
ወደ ፓርኩ ለመጓጓዝ የታካባ፣ መንደራ፣ ማልካማ እና ኤልዋክ የተሰኙ ዓየር ማረፊያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በረራቸው አብዛኞዎቹ በሣምንት ሁለት ቀናት ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ጐብኚዎች አመቺ ቀናትን መርጠው ሊጓጓዙ እንደሚችሉ ነው የተጠቆመው፡፡
ፓርኩን ለማስጐብኘት የተመረጡ ድርጅቶች እንደሚገኙ የተጠቆመ ሲሆን በተዘጋጁት ጣቢያዎች ለጐብኚዎች በየማረፊያ ክፍሎቹ የግል መታጠቢያ፣ የዓየር ማቀዝቀዣ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስሪያ፣ የንግድ ቤቶች እና የተለያዩ አገልግሎቶችንም ማግኘት ያስችላሉ፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት- ቺታ እንዲሁም ጂውልስ ሳፊሪ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም