በቻይና ጓንግዶንግ ግዛት ዶንግጓን ከተማ ባላቸው ከእፅዋት የተቀመመ መድሃኒት መሸጫ ሱቅ የሚተዳደሩ ጥንዶች በመልካቸው መመሳሰል አልባሳት በመቀያየር በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቋቸው ማስታወቂያዎች በርካታ ተከታታይ ደንበኞችን አፍርተው የሽያጫቸው መጠን መጨመሩን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
ሊያንግ ካዩ እና ባለቤቱ ሄ ዢያንሺንግ እድሜያቸው በ20ዎች ውስጥ ነው፡፡ምንም እንኳን የጥንዶቹ መተዳደሪያ ባህላዊ የእፅዋት መድሃኒት መሸጫ ሱቅ የዓስርት ዓመታት ልምድ ከነበራቸው ቤተሰቦቻቸው የተረከቡት ቢሆንም ገቢያቸው ቀንሶ፣ ገበያቸው ተቀዛቅዞ ነበር፡፡
ጥንዶቹ የሽያጭ መጠናቸው ስለማነሱ አውጥተው አውርደው ገበያቸው እንዲያንሰራራ አንድ ስልት ዘየዱ፡፡ በተለመደው መልኩ የተፋዘዘ እና የተቀዛቀዘ ገበያቸውን እየመሩ መቀጠል እንደሌለባቸው አምነው ጥንዶች የመልካቸውን መመሳሰል መሠረት አድርገውም የተለያዩ አጫጭር የማስታወቂያ ቪዲዮዎችን በመስራት ለእይታ ለማብቃት ወሰኑ፡፡
ጥንዶቹ በሚሰሩት አጫጭር ማስታወቂያም በቻይና የቲክቶክ ስሪት በሆነው “ዶዩን” የተሰኘውን ማህበራዊ ሚዲያ መቀላቀል ቻሉ፡፡ ጥንዶቹ መልካቸው በእጅጉ በመመሳሰሉ ሚስት እና ባል ልብሶቻቸውን እየተቀያየሩ በመተወን ለእይታ ያበቁ ጀመር፡፡ በቃ “ባልና ሚስት?” ወይስ “መንትዮች?” ጥርጣሬ ውስጥ የገባውን ተመልካች ቀልብ መግዛትም ቻሉ፤ በዚህም የንግድ ስራቸው ማንሰራራት ችሏል፡፡
በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚከታተላቸው እውነቱን ለማረጋገጥ ወደ መድሃኒት ሱቃቸው መጉረፉን ተያያዘው፡፡ አጫጭር ትዕይንቶቹም እንደተወደዱላቸው ከተለጠፉት ግብረ መልስ ሊረዱ መቻላቸውን ድረ ገጾች አስነብበዋል፡፡
ባል ሚስቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሷን ልብስ ለብሶ በአጫጭር ቪዲዮዎች ላይ ማስታወቂያ እንዲሰሩ ሀሳቡን ስታቀርብለት እንደማይሆን ገምቶ ከተሰማው ስሜት በተለየ ዛሬ ላይ ውጤቱ ጥሩ ሆኖ ገበያቸው ደርቶ ሲመለከተው ባለቤቱን ማመስገኑንም ነው የድረ ገጹ ጽሁፍ በማጠቃለያነት ለንባብ ያበቃው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


