ትምህርት የለውጥ እና ራስን ለተሻለ ለውጥ ማዘጋጃ መሳሪያ ነው። የዘርፉ ምሁራን መማር ማለት የባህርይ ለውጥ ማምጣት ነው ይላሉ። ትምህርት ዓለም ለተጓዘችበት የረዥም ዓመታት ቁልፍ የለውጥ መንገድ ነው። ከምድር ባሻገር ጨረቃ ለመድረስም ያስቻለው መሣሪያ ትምህርት ነው። ለዚህም ነው “እኛ የምናደንቀው ጨረቃ ላይ የወጣውን ሳይሆን ጨረቃ ላይ እንዲወጣ ያስተማረውን ነው” የሚባለው።
ትምህርት የአዕምሮን ንቃት በማጎልበት ተመራማሪና ለለውጥ የተጋ ህብረተሰብ እንዲፈጠር በማድረግ የሀገር ግንባታ ሂደትን ያፋጥናል። በየትኛውም ሀገር የለውጥ ሐዋርያ ተደርጎ ይወሰዳል። እኛ ኢትዮጵያውያንም የዚህ ዓለም አቀፍ እሳቤ ተጋሪዎች ነን።
በሀገራችን ዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት በተቀናጀ መንገድ ከመጀመሩ በርካታ ዓመታት በፊት ይዘቱ የተለያየ ቢሆንም ተዋረዱን የጠበቀ የትምህርት ሥርዓት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ለአብነት በ15ኛው እና በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተሠሩ የትርጉም እና ወጥ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎችን ብንጠቅስ በወቅቱ የነበረውን የመጻሕፍት አንድምታ ትርጓሜ (የትምህርት ሥርዓትን) ያሳያሉ። ለዚህም በየቤተ ዕምነቱ የሚገኙ ጥንታዊ የሆኑ ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ምስክር ናቸው።
የብዙ ስኬታማ ኢትዮጵያዊያንን የሕይወት ታሪክ ስናነብ … በመጀመሪያ ፊደል ቆጠረ፣ ቀጥሎም ዳዊት ደገመ… የሚሉ የሕይወት መንገድ ማሳያዎች ደጋግመው ይስተጋባሉ። ይህም ከዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት መጀመር አስቀድሞ የነበረውን ጥንታዊ የትምህርት ሥርዓት የሚያሳይ እና ለሕይወት መንገድ መሠረት መሆኑን አመላካች ነው።
ደራሲ ጌታቸው አበበ “የኢትዮጵያ ደራሲያን እና ሥራዎቻቸው” በሚል በታተመ ክፍል አንድ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ የሚከተለውን ያትታሉ፤ “… እንደሚታወቀው የራሳቸው ፊደል አላቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ጥቂት የዓለም ሀገራት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በመሆኑም የሥነ ጽሑፍ ሊቃውንት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ፍልስፍና እና የመሳሰሉትን በራሷ ፊደል ቀርፀው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላልፉ ቆይተዋል።…” ደራሲው እንደገለጹት ዛሬም ድረስ ሳይቆራረጥ የመጣውን አዕምሯዊ፣ ሰነዳዊ እና ሰነድ አልባ ብሔራዊ ሃብት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ትምህርት ሚናው ጉልህ ነው።
የራስን ፊደል ቀርፆ ቋንቋን፣ ባሕልን፣ ታሪክንና ሌሎችን ሃገራዊ ሃብቶች ለመጪው ትውልድ ጠብቆ ለማስተላለፍ ከመማር፣ ከማወቅ እና አዕምሮን ከማንቃት የተሻለ ምርጫ አለመኖሩንም ደራሲው አጽንኦት ሰጥተውታል።
ሌላኛው ደራሲ አክሊሉ ሀብቴ (ዶ/ር) “የዘመናዊ ትምህርት መቋቋም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን” በሚል ባሳተሙት ማስታወሻ/ጆርናል/ ላይ “የመማር እና የማሰብ ችሎታ ለሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠው ጸጋ ነው። ይህ ጸጋ የሚሰጠው ደግሞ ከሰው ውጭ ሌላ ፍጥረት የለም” በማለት ያትታሉ። ደራሲው “የመማር” እና “የማሰብ ችሎታ” የሚሉትን ሁለት ሃሳቦች “መማር” የሚለውን ሃሳብ አስቀድመው በተርታ አስቀምጠዋቸዋል። ከጽሑፉ እንደምንገነዘበው መማር ለአዕምሮ ንቃት እና የማሰብ ችሎታን ለማጎልበት አይነተኛ መሣሪያ ነው። “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” የሚለው የኢትዮጵያዊያን ብሂልም መሠረቱ ይህ መሆኑን ልብ ይሏል።
እግር የትምህርት ቤትን በር ረግጦ፣ ክንድ የጓደኛን ትከሻ አቅፎ “መማር ያስከብራል ሃገርን ያኮራል!” እያሉ መዘመር የሁሉም ተማሪዎች የልጅነት ትዝታ ነው። ይህ የልጅነት ትዝታ ብቻ ሳይሆን የቀለም ጨዋነት ትውፊት አንድ አንድ እያለ የቀነሰበት የሕይወት ጉዞ ላይ ደርሳል ።
ይሁን እንጅ በአሁኑ ጊዜ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የማይተካ ወርቃማ የትምህርት ጊዜ እየባከነ ይገኛል። የባከነ የትምህርት ጊዜ ሾልኮ እንደጠፋ ዕድሜ የሚቆጠር ነው። ዶክተር፣ ፓይለት፣ መሃንዲስ… የሚሉ ብሩህ የልጅነት ህልሞች የሚሰነቁበት፣ ነገን አሻግሮ ለማየት የሚያስችል የከፍታ ቦታ ትምህርት ቤት ነው። ተደጋግሞ እንደሚባለው ዛሬ ላይ ይህን ፅሑፍ በመጻፍ፣ እናንተ አንባቢያንም ልታነቡ የቻላችሁት እግራችን ትምህርት ቤት በመርገጡ እና መምህራንም በሰጡን ተመን የለሽ የቀለም ገፀ በረከት ምክንያት መሆኑን አንዘነጋውም።
ዛሬ ላይ ሀ፣ ሁ… ብሎ ፊደል ያልቆጠረ ልጅ ለታሪኩ ብሎም ለራሱ ባዕድ ነው። ዛሬ ላይ “ኤ” አፕል፣ “ቢ ቦል” … ብሎ ያልቆጠረ ልጅ ፈጣን ስልጣኔ እና ዓለም አቀፋዊነት (ሉላዊነት – globalization) ለሚዘውሯት ዓለም የበይ ተመልካች እና ባይተዋር ያደርጋል። ትምህርት ቤት ያልዋለ ልጅስ የት ሊውል ይችላል? ምናልባት ቁማር ይለምድ ይሆናል አሊያም ስርቆት ማን ያውቃል።
በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት ክፉኛ ከጎዳቸው መካከል ትምህርት ግንባር ቀደሙ ነው፤ የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዳስታወቀው የተያዘው የትምህርት ዘመን ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ይማራሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር:: ይሁን እንጂ ወደ ትምህርት ገበታ የተመለሱት ተማሪዎች ከሦስት ሚሊዮን የተሻገረ አይደለም::
ዛሬ ላይ በድህነት ላይ ግጭት ተጨምሮበት ትምህርት ለመማር ያልቻለ ልጅ የነገ ዕጣ ፋንታው ምን ይሆን? እንደ ሀገርስ መገኛችን የት ሊሆን ይችላል? “የተማረ ይግደለኝ!” በማለት የትምህርትን አይተኬ ዋጋ የሚገነዘብ ማሕበረሰብ ልጁን ትምህርት ቤት ለመላክ መንታ ልብ ሲሆን እየተስተዋለ ነው።
ተምሮ ሥራ በማጣት ቢፈተንም “የተማረ ሰውና የታጠበ ብርጭቆ አንድ ነው!” እያለ ተስፋ ሳይቆርጥ ለሚታትር ማሕበረሰብ የዕውቀት ዋጋው ልብን ያሞቃል። ሰፋ አድርገን ካየነው፣ ህይወታቸዉ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነባቸዉ ቤተሰቦች የተገጘ ተማሪ በአንድ መማሪያ ደብተር አምስት እና ስድስት የትምህርት አይነት በብጣሽ እርሳስ እየጻፈ፣ “ሳይንስ ሳይንስ፥ መድኃኒቴ ….” ብሎ እየዘመረ ነገ መልካም ይሆናል ብሎ ለሚያስብ የአፍሪካ ቀንዲል ለምንላት ኢትዮጵያችን ልጅ አለመማር ትልቅ የመብት ጥሰት ነው።
በዚህ በድህረ ዘመናዊነት (postmodernism) የውድድር ዘመን ለልጆች ከትምህርት ቤት የበለጠ ገነት (ጀነት)፣ ከመማርና ከማወቅ የበለጠ አስተማማኝ ዋስትና የላቸውምና።
አለም ወደ አንድ መንደር እየጠበበች እና ስልጣኔዉ በአደገበት በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ጦም አዳሪ መሆናቸው ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። የአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ደረጃ በአጠያያቂ ሁኔታ ከደረጃ በታች መሆኑ ተደጋግሞ በሚጠቀስበት በዚህ ወቅት በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚደረግ ተደጋጋሚ ግጭትም ለትህርታችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆንበታል።
አብዛኛው የማሕበረሰብ ክፍል ከተማሪ ልጆቹ አፍ ቀምቶ ለትምህርት ቤት ግንባታ ገንዘቡን ይለግሳል። ይህን የተቀደሰ ተግባር የሚፈፅመው ድሎት አነሳስቶት ሳይሆን የልጆቹን የወደፊት ዕጣ ፋንታ ብሩህ ለማድረግ ነው። በትምህርት ቤቶች መፍረስ የአያሌ ትውልዶች የወደፊት ተስፋ አብሮ ይመክናል። ተምሮ መማርን መቃወም ደግሞ እኩይ ራስ ወዳድነት ይሆናል።
ማንኛውም ፖለቲካ፣ ማሕበራዊ እና ታሪካዊ እሳቤ በሰው ልጅ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎች ማዕቀፍ ሊቃኝ ይገባል። የትውልድ የወደፊት ዕጣ ፋንታ በትውልዱ ሊወሰን ይገባል። “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ!” እንዲሉ የተድበሰበሰ የቤት ሥራ ለትውልድ መስጠት ትርፉ ኪሳራ ነው። በመሆኑም የተማሪዎችን ነገ መልካም ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ታካዊ ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል::
(ደረጀ ደርበው)
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም