“መምህር አለመሆኔ ይቆጨኛል”

0
203

የተወለደው በ1964 ዓ.ም በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር መተከል አውራጃ ማንዱራ ወረዳ ገነተ ማርያም ከተማ ነው:: “ለእናቴ አራተኛ ልጅ ነኝ፤ ለአባቴ ግን ስንተኛ ልጅ እንደሆንኩ አላውቅም” ሲል ይቀልዳል:: ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል በማንዱራ ከተማ ነው የተማረው፤ ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ከፍል በቻግኒ ከተማ ተምሯል::
የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለ የደረጃ ተማሪ ነበር፤ በኋላ ወላጆቹ ከሚኖሩበት ማንዱራ ለቆ ወደ ቻግኒ ሲሄድ በቤተሰቦቹ ናፍቆት እና በነበረው ከፍተኛ ፉክክር ወደ መካከለኛ ደረጃ ተማሪነት ዝቅ ማለቱን ይናገራል:: በ1981 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ወስዶ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አመጣ:: በሚቀጥለው ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ የቲያትሪካል አርት ትምህርት ክፍልን ተቀላቀለ:: ትምህርት ክፍሉን የተቀላቀለው በፍላጎቱ እንደሆነ ይናገራል::
ሁለተኛ ዓመት ሲደርስ የወያኔ ሰራዊት ወደ መሃል ሀገር እየተመመ የነበረበት ወቅት ስለሆነ ለምኒችል እና ሌሎች ተማሪዎች አስቸጋሪ ጊዜ ነበር:: ትምህርቱን አቋርጦ ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ገባ:: ለሁለት ወራት ወታደራዊ ስልጠና ሲወስድ ቆይቶ ከጓዶቹ ጋር ወደ ግዳጅ ሊሰማራ ሲዘጋጁ መንገድ ይቆረጣል:: አዲስ አበባም በወያኔ ሰራዊት ልትያዝ አንድ ቀን ነበር የቀራት:: ገሚሱ ወደ ኬንያ ኮበለለ:: ምኒችል ግን ሀገሩን ለቆ ለመውጣት አልፈለገም:: 90 ኪሎ ሜትሮችን በእግር ለሁለት ቀናት በመጓዝ ሀዋሳ ከተማ ገባ:: በመንገድ ላይ ብዙ ፈተናዎችንም አስተናግዷል::
በሀዋሳ ከተማ ሕዝቡ ያሳያቸውን ፍቅር ግን አይረሳውም:: ለሰባት ቀናት ያክል ምግብ እያመጣ፣ ውኃ እያጠጣ ተንከባክቦ አቆይቷቸዋል:: በወቅቱ የያዘውን የሲቪል ልብስ በአራት ብር በመሸጥ ያንን ክፉ ጊዜ ለማለፍም ሞክሯል:: ምኒችል ግንቦት 20 1983 ዓ.ም ሀዋሳ ከተማ እንደነበር እና ኢህአዴግ ኢትዮጵያን መቆጣጠሩን በሬዲዮ እንደሰማ ይተርካል::
የደርግ መንግሥት “ተነሳ ተራመድ”፣ “ዝመት” የመሳሰሉ ዘፈኖችን ይለቅ ስለነበር፤ ወያኔ ሲገባ የድሮ ሙዚቃዎች መለቀቅ ጀምረው ነበር፤ የፍቅር ሙዚቃዎች መለቀቃቸው እንግዳ ነበር:: ምኒችል ይናገራል “አንድ ሙስሊም ጓደኛየ ‘ወላሂ እዚህ ሀገር ሰላም ሊሆን ነው፣ የድሮ ሙዚቃ መለቀቅ ጀመረ’ በማለት ተስፋዉን ገለጸ ይለናል፤ ይህ ተስፋ እውን ተሳክቶ ይሆን?
ግንቦት 27 ቀን ቀይ መስቀል ከነበሩበት ከተማ ይዟቸው ወጣ እና አዲስ አበባ ገቡ፤ አዲስ አበባ በዚያ ቀን የበቅሎ ቤት ፍንዳታ የሚባለው ተከስቶ ከፍተኛ ቃጠሎ ነበር:: ከዚያም ወደ ቤተሰብ ተመለሰ::
በብላቴ ማሰልጠኛ የነበሩት ምኒችል እና ጓደኞቹ በመንግሥት ዘግናኝ የሆነ ግዳጅ ሊሰጣቸው ነበር:: ጉዳዩ አንዲህ ነው፤ የሻቢያ ጦር አሰብን ተቆጣጥሮ ከፍተኛ ጫና በፈጠረበት ወቅት ማለትም ግንቦት 12 (ግንቦት 13 ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ዚምባብዌ የሄዱበት ቀን ነው) የብላቴ ሰልጣኝ ተማሪዎች በአሰብ ቀጣና ሄደው እንዲዋጉ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር፤ ይህንን “በወጉ ስልጠና ያልወሰዱ ተማሪዎችን አስገብቼ አልማግድም” ብለው ውሳኔውን ሌተናል ጄነራል አዲስ ተድላ በመቃወማቸው መቅረቱን ራሳቸው ጀኔራሉ ጽፈዋል::
ከቤተሰብ ጋር ትንሽ እንደቆየ በቀድሞው ጦር ተሃድሶ ተቋም ብር ይሰጣል ተብሎ 137 ብር የመጓጓዣ መቀበሉን ምኒችል በፈገግታ ያስታውሳል፤ በወቅቱ የነበረው መንግሥት የተማሪ ዘማቾች ላይ ብዙም ነገር አላከረረባቸውም::
“ለፍዳ የተፈጠረው ትውልድ” የሚባለው አካል የሆነው ምኒችል ትምህርቱን እንደገና ከሁለተኛ ዓመት ጀመረ:: በ1981 ከተከሰተው መፈንቅለ መንግሥት ጀምሮ ትምህርት የሚቆራረጥበት፣ በሚደረጉ ሰልፎች ዱላ እና ሌሎች ግፎች የሚፈጸምበት ነበር፤ “አስጨናቂ እና አስፈሪ ወቅት ነበር” ይለዋል ምኒችል:: የሽግግር መንግሥት ሲመጣ ተቃውሞ ነበር፤ ኤርትራ ስትገነጠል ተቃውሞ ነበር፤ በዚህ ውስጥ የተደበደበ እና የተገደለ አለ:: ተማሪ ሰልፍ ወጥቶ ባለበት ወቅት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ በሮች በሙሉ ተዘግተው ተማሪው በወታደር ተኩስ እና ድብደባ ደርሶበታል:: መምህራንን አካቶ በተነሳ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መንግሥት ያልተመጣጠነ ኀይል መጠቀሙን አምኗል፤ በኋላ ግን 42 መምህራን ከሥራቸው ተባረዋል:: ምኒችል ተመራቂ በነበረበት ወቅት ለሦስት ወር ዩኒቨርሲቲው ተዘግቷል:: አንድ ዓመት አሳልፎ በ1986 ተመርቋል::
ምኒችል ወደ ጋዜጠኝነት የገባበትን ምክንያት ሲናገር ከልጅነቱ ጀምሮ በክበባት የግጥም፣ ልቦለድ፣ ታሪክ፤ ድራማ እና ሌሎች የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶችን መጻፍ እና መተወን ይወድ ስለነበር እንደሆነ ይናገራል:: የንባብ ማብቂያ የሚባል ክፍለ ጊዜም ነበራቸው፤ በዚህ ክፍለ ጊዜ ከሩሲያኛ የተተረጎሙ ተረቶች፣ አጭር ልብወለዶች እንደነበሩ ያስታውሳል፤ እናቱ የኢትዮጵያ አብዮታዊ ሴቶች ማኅበር (አኢሴማ) ምክትል ሊቀ መንበር ነበሩ፤ “አዲስ ህይወት” የሚል መጽሔት ላይ ያሉትን ዜናዎች በሬዲዮ እንደሰማቸው ጋዜጠኞች አድርጎ ለእናቱ ያነብላቸው ነበር፤ እናቱ ይስቃሉ፤ ያደንቁታል::
እሱ ከመወለዱ በፊት የተገዛው ፊሊፕስ ሬዲዯቸውም ለጋዜጠኝነት ሙያ ፍላጎት እንዲያድርበት አድርጓል:: በተለይ ወላጅ አባቱ ዜና በደንብ ይከታተሉ ነበር፤ እሱም ከእሳቸው ስር ቁጭ ብሎ ይኮመኩማል፤ በልጅነት አዕምሮው ይህ ተቀርጾበታል:: እነ ዳሪዮስ ሞዲ፣ ሙሉጌታ ወልደ ሚካኤል፣ ታምራት አሰፋ፣ ነጋሽ መሀመድ እና አለምነህ ዋሴ “በጎ ተጽእኖ የፈጠሩብኝ ናቸው” ይላቸዋል፤ አዲስ አበባ ገብቶ ቴሌቪዥን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከት በሬዲዮ የሚያውቃቸውን ጋዜጠኞች በቴሌቪዥንም ይኖራሉ ብሎ በማሰብ “የታል ታዲዮስ? የታል ሙሉጌታ ወልደ ሚካኤል?” እያለ ይፈልግ ነበር:: በተለይ ጋዜጠኛ ታምራት አሰፋ አርአያዬ ነው ይላል::
ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ እንደወጣ መንግሥት ራሱ መቅጠር ያቆመበት ጊዜ ነበር፤ ሆኖም ክልሎች ተመስርተው የራሳቸውን መዋቅር መዘርጋት ሲጀምሩ ምኒችል ወደ ደቡብ ክልል ከምባታ እና አላባ ጠንባሮ ዞን ተመደበ፤ ደመወዙ 500 ብር ነበር፤ በወቅቱ ይህ ገንዘብ ብዙ ነበር፤ “ተንቀባሮ መኖር የሚያስችል፣ ለቤተሰብ ሁሉ የሚተርፍ ነበር” ይላል ምኒችል:: አንድ ክትፎ በአራት ብር ይበላ ነበር::
በባሕል ኪነት ቡድን ሥራውን ጀምሮ የኪነት ቡድን መሠረተ፣ ባሕሉን አጠና፣ አስተዋወቀ:: የደቡብ ክልል ቆይታው እጅግ አስደሳች ነበር:: ለዚህ ደግሞ አስተዳደጉ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በመሆኑ በቀላሉ እንግዳ ከሆነ ባሕል እና እሴት ጋር የመላመድ እድልን ሰጥቶታል:: በደቡብ ቆይታው የባሕል ቡድን አቋቁሞ፤ ባንድ መሥርቶ፣ ራሱም ክራር ተለማምዶ፤ ባዛር ላይ ጥሩ የሆነ ትዕይንት አቅርቧል:: በዚህ ሁኔታ የተሳካ ቆይታን በደቡብ ክልል አሳለፈ::
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እሱ ባለበት መደብ የሰው ኃይል እንደሚፈልግ በቤተሰቦቹ በኩል ተነገረው:: አመለከተ፤ በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ “ልቀቋቸው” የሚል ደብዳቤ ተልኮ ወደ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ተዘዋወረ:: በዚህም ወደ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር መጥቶ ባሕል ቡድን በማቋቋም፣ ባሕልን በማጥናት፤ የተለያዩ የኪነ ጥበብ መድረኮችን በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል:: “የአማራ ክልል ዜና ማዕከል ወደ ባሕል ቱሪዝም እና ማስታወቂያ (ባቱማ) ሲቀየር የአማራ ክልል ዜና ማዕከል ሪፖርተሩ አንድ ላይ ሆንን፡፡ ከዛም ዜና እንዴት እንደሚሰራ ያሳየኝ ነበር፡፡ ፈቃድ ሲወጣ ወክሎ ለማዕከሉ ኃላፊዎች እያሳወቀ እኔ እርሱን ተክቸ ዜና እየሠራሁ በስልክ ለዜና ማዕከሉ እሰጥ ነበር” ይላል፡፡ ዜና አጻጻፍ እና ሌሎች የጋዜጠኝነት ክህሎቶችን ከአንድ ባልንጀራው መማሩን ምኒችል ይናገራል:: ከዚህ ተነስቶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጽሑፍ ይልክ ነበር::
ለምኒችል ወደ ጋዜጠኝነቱ እንዲገባ በር የከፈተለት አጋጣሚ መጣ፤ የአዊኛ ቋንቋ ፊደል ቀረጻን እና የመማሪያ መጽሐፍ ዝግጅትን የተመለከተ ሲምፖዚየም ተዘጋጀ:: በሲምፖዚየሙ በአማርኛ እና በአዊኛ ድራማውን፣ ግጥሙን፣ ውዝዋዜውን አቀለጠው፤ የሁሉም ሰው ዐይን ውስጥ ገባ:: ጋዜጠኛ አባትሁን ዘገየ ከባቱማ የባሕል ቡድኑን እንቅስቃሴ በተመለከተ ቃለ ምልልስ አደረገለት፤ የባሕል ቡድኑ የአዊን ቱባ ባሕል በደንብ ያስተዋወቀ ነበር፤ ዘገባው በበኲር ጋዜጣ ታተመ:: ጊዜው ለምኒችል የስኬት ዘመን ነበር::
የአማራ ራዲዮ ከተቋቋመ በኋላ በክራሩ የተለያዩ ዜማዎችን እና መልዕክታቸውን በሬዲዮ ቀርቦ እየተጫወተ አዝናኝ እና አስተማሪ ፕሮግራም ላይ በእንግድነት በተለይ በበዓላት ጊዜ በተከታታይ ይቀርብ ነበር::
በ1991 ዓ.ም ተወዳድሮ በኲር ጋዜጣን ተቀላቀለ:: በኩር ጋዜጣን በዘጋቢነት ሳይሆን በማኅበራዊ እና ሴቶች አምድ በአርታኢነት ነበር የተቀላለቀለው:: የሥነ ጽሑፍ ትምህርቱ እና ልምዱ በሥራው እንዳይቸገር አስተዋጽኦ እንዳደረጉለት ይናገራል፤ ከዚህ ባሻገር ግን አስተማሪ እና ደጋፊ (ሜንቶሮቼ) ናቸው የሚላቸው ጋዜጠኛ አባትሁን ዘገየን እና ደራሲ አበረ አዳሙን ነው፤ እሱን በማብቃት ረገድ ዛሬም ያመሰግናቸዋል::
በመጀመሪያ ዘገባው እንዳይቸገር በበኲር የሚወጡ ጽሑፎችን በደንብ አስቀድሞ ያያል፤ “ከመጣጥፍ ይልቅ ዜና መጻፍ ይከብደኝ ነበር፤ ዜና ለመጻፍ ሁለት ሶስት ጊዜ ወረቀት እቀድ ነበር፤
በአርታኢነት ዘመኑ ከማይረሳቸው ገጠመኞቹ አንዱ ይህ ነው፡- አንድ አዲስ ጋዜጠኛ በኲር ተመድቦ በመጀመሪያው ጊዜ ሦስት ገጽ አጭር ዜና ሰርቶ መጣ፤ የተደረተ ነገር ይበዛዋል፤ በዚህ ጊዜ ሁለት ቀይ እስክርቢቶዎችን ይዤ እንደ ቢለዋ እያፋጨሁ እና እየሳልኩ ቁርጥ መጣልኝ ልቆርጥ ነው አልኩ፤ ልጁ ደነገጠ፤ ከዚያ ያንን ሦስት ገጽ አክብቤ ሰረዝኩት፤ “ልጁ የለፋሁበትን” ብሎ ጮኸ፤ ምኒችል ስቆ ለልጁ ጉዳዩን አስረዳው:: በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ምኒችል እና ባልደረቦቹ ለዘገባ ሄደው በስህተት የጠላት የጦር ቀጣና ሊገቡ ለትንሽ ተርፈዋል::
በበኲር ጋዜጣ ጥሩ ቆይታ የነበረው ምኒችል የበኲር መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነ:: በበኲር መጽሔት ባሳየው ብቃት የአማራ ሬዲዮ ኃላፊ መሆን ቻለ:: ከዚያም በ1997 ዓ.ም በአዊኛ ቋንቋ የ15 ደቂቃ የሬዲዮ ዝግጅት አስጀመረ፤ ለዚህ አቶ ጌታቸው ኃይሉን ያመሰግናል:: በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በይዘት እና ዝግጅት ረቂቅ ላይ ተሳታፊ ነበር:: ምኒችል በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከኦንላይን (በይነ መረብ መገናኛ) ውጪ በሁሉም ማሰራጫዎች ሠርቷል::
ጋዜጠኛ ምንቺል እንግዳ ከጋዜጠኝነት ሙያው በተጨማሪ በአዊኛ ቋንቋ ግጥሞችን በመጻፍ፣የሙዚቃ ግጥሞችን በመድረስ እና የአዊኛ ሙዚቃዎችን በማቀንቀን ጭምር ይታወቃል::ምኒችል በአዊኛ ያሳተመው የግጥም መድብል በሀገሪቱ ሁለተኛ ሥራ እንደሆነ እና ለአዊኛ ቋንቋ ማስተማሪያነት እያገለገለ ስለመሆኑ ገልጾልናል::
ጋዜጠኛ ምኒችል ምንም እንኳን ጋዜጠኛ የመሆን ጽኑ ፍላጎት የነበረው ቢሆንም፣ በአንጻሩ ደግሞ “መምህር አለመሆኔ ይቆጨኛል” የሚልም ሰው ነው:: ቲያትሪካል አርት በማጥናቱ በጋዜጠኝነት ሙያ ብዙም ያልተፈተነው ምኒችል መምህር የመሆን ምኞቱ ባለመሳካቱ ግን መጠነኛ ቁጭት አድሮበታል፤ መጽናኛው በጋዜጠኝነት ሙያውም ኅብረተሰብን ማስተማር መቻሉ እንደሆነም ይናገራል::
ምኒችል አሁን ላይ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአዊኛ ዴስክ ምክትል አዘጋጅ ሆኖ በጋዜጠኝነት ሙያው ቀጥሎበታል::
ጋዜጠኛ ምኒችል እንግዳ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነው:: “ቀለል ያለ ሕይወት መኖር የምፈልግ ሰው ነኝ” ሲል ስለ ባሕሪው ይናገራል:: ምኒችልን በዘገባ ወቅት በገጠመው ነገር የኛ ገጽ ጽሑፋችን እንደምድም::
አንድ ጊዜ ምኒችል ስለ ወባ ወረርሽኝ ለመዘገብ ወደተለያዩ ዞኖች ያቀናል፤ ከአንድ ወረዳ በበሽታው የሞቱ ሰዎች 20 መሆናቸው ይነገረዋል፤ በዞን ደረጃ ሲጠይቅ ደግሞ ሰባት አድርገው ይነግሩታል፤ ወደ ክልል ሲመጣ ጭራሹን አንድ ሰው ብቻ እንደሞተ ሪፖርት መደረጉ ይነገረዋል::የዚህ ዓይነቱን የተዛባ ዘገባ “ድንቄም ሪፖርት” ሲል ይተቸዋል -ምኒችል::
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ውስጥ በርከት ያለ ልምድ ካላቸው ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ምኒችል እንግዳ በብዙ ወጣት ጋዜጠኞች ዘንድ በአርዓያነት የሚጠቀስ ባለሙያ ነው::ሙያውን ሳይሰስት ለሌሎች በማሻገሩ የሚወደሰው አንጋፋው ጋዜጠኛ ምኒችል በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ አሻራቸውን ካሳረፉ ጋዜጠኞች ውስጥም አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ ነው::

(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here