መሞት በአዋጅ የተከለከለባት ቤልካስትሮ

0
134

በጣሊያን አንድ ሺህ ሁለት መቶ ኗሪዎች በሚገኙባት ቤልካስትሮ በተሰኘች መንደር የጤና አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ መታመምም ሆነ ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረግ በአዋጅ መከልከሉን ዩፒአይ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡

የቤልካስትሮ መንደር ከንቲባ አንቶኒዮ ቶሪቺያ አዋጁን ከጤና አጠባበቅ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ኗሪዎችን ለመጠበቅ የታለመ መሆኑን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡ ኗሪዎች ቢታመሙ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት 30 ማይል ወይም 48 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓጓዝ ግድ ይላቸዋል፡፡ ከአንድ ሺ ሁለት መቶ  የመንደሯ ኗሪዎች መካከልም ከግማሽ በላይ ማለትም ከስድስት መቶ የሚበልጡት ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው ናቸው፡፡

ከንቲባው የጤና አጠባበቅ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከመንደሯ በቅርበት ባለመገኘቱ የጤና አገልግሎት ለማግኘት  48 ኪሎ ሜትር ርቀትን በሰዓት ሃያስምንት ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት መጓጓዝ በራሱ ፈታኝ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው አዋጁን ያወጡት፡፡

የኗሪዎቹ ገቢም በእጅጉ አነስተኛ የሚባል መሆኑም “ታሞ ከመማቀቅ…” የሚለውን  አባባል ተግባራዊ ማድረግ ሌላው አስገዳጅ ምክንያት መሆኑም በድረ ገጹ ተጠቁሟል፡፡

እንደ ከንቲባው አገላለጽ ኗሪዎች ከማናቸውም ለከፋ አደጋ ከሚያጋልጥ ተግባር ከመሳተፍ ታቅበው ጊዜያቸውን በዋዛ ፈዛዛ በማረፍ ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለመንደሯ በቅርበት ካለ የጤና አልግሎት መስጫ ተቋም አንድ ሀኪም የሚመደብ ሲሆን ሃኪሙ በምሽት እና በሳምንቱ የረፍት ቀናት አገልግሎት አለመስጠቱ ለኗሪዎች ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸውም ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here