መሠረታዊ የሥራ ላይ መብቶች

0
61

ባለፈው ሳምንት ጽሑፋችን በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ዉስጥ  ያሉ ማስጠንቀቂያወች እና ከስራ  የሚያባርሩ ጉዳዮችን ተመልክተን ነበር። በዚህ ሳምንት ደግሞ በተለይም በግል ድርጅቶች በአሰሪ እና ሠራተኛ ግንኙነት ላይ የሠራተኛዉ መብቶች ምን ምን ናቸው ? የሚለውን የአማራ ሚዲያ ኮርፓሬሽን የሕግ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ፍቅር በለጠ የሰጡንን  ዝርዝር ማብራሪያ እናቀርብላችሀለን  መልካም ንባብ::

የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረታዊ የሥራ ላይ መብቶችንና ግዴታዎችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለኢንቨስትመንትና ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ግቦች መሳካት ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስችል የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አስተዳደር ሥርዓት መመስረት እንዲቻል፤ እንዲሁም የሥራ ሁኔታን፤ የሙያ ደህንነት፤ ጤንነትና የሥራ አካባቢ ጥበቃንና የሁለትዮሽ እና የሦስትዮሽ ማኅበራዊ ምክክር አሠራርን በማጠናከር በሕግ መሠረት የማማከርና የመቆጣጠር ተግባራትን እያመጣጠነ ሥራውን የሚያከናውን አካል ስልጣንና ተግባር መዘርዘርና መወሰን በማስፈለጉ ለሠራተኞች  እና አንድ ሠራተኛ የሥራ ውል  ስምምነት ከፈፀመና ሥራውን መሥራት ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የተለያዩ ፈቃዶችን የማግኘት ሕገ መንግስታዊ መብት አለው:: ይህም መብቱ በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 ተረጋግጧል:: እነዚህን መብቶች እና  አይነቶችን በዝርዘር እናያለን። የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ አዋጅ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ በተመሠረተ የሥራ ግንኙነት እና በምልመላ ሂደት ላይ ተፈጻሚ ይሆናል::

ባለሙያዋ ወ/ሮ ፍቅር እንደገለፁት የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ቢኖርም  ሥራቸውን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚያከናውኑ የውጭ ዲኘሎማቲክ ሚስዮኖች ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከኢትዮጵያዊያን ጋር በሚመሰርቱት የሥራ ግንኙነቶች ላይ አዋጁ ተፈጻሚ እንዳይሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ወይም ኢትዮጵያ በምትፈርማቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሊወሰን ይችላል::

የሃይማኖት ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚመሠርቱት የሥራ ግንኙነቶች ላይ አዋጁ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ሊወስን ይችላል:: ስለግል አገልግሎት ቅጥር የሥራ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ያወጣል::

በሕጉ መሠረት የግል እና ለመንግስት ልማት ድርጅት ሠራተኞች የሚኖራቸውን መብቶች ደግሞ በዝርዝር ስናይ፤

የህዝብ በአላት ቀን

ማንኛውም ሠራተኛ በሕዝብ በዓል፣ በመንግሥት ውሳኔ መሥሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው በሚውሉበት ቀን ባለመሥራቱ መደበኛ የደመወዝ ክፍያ አይቀነስበትም።ይህም በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 74 ላይ ተደንግጓል።

የሥራው ሁኔታ አስገድዶ በሕዝብ በዓል ወይም በመንግሥት ውሳኔ መሥሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው በሚውሉበት ቀን እንዲሠራ የታዘዘ  ሠራተኛ ምርጫውን መሠረት በማድረግ  የትርፍ  ሰዓት ክፍያ ወይም የማካካሻ ዕረፍት ይሰጠዋል::

በሕዝብ በዓላት ቀን ለሚሠራ ሥራ የሚከፈል ክፍያ

ሠራተኛው በሕዝብ በዓል ቀን ከሠራ በሰዓት የሚያገኘው ክፍያ በሁለት ጊዜ ተባዝቶ በበዓሉ ቀን ለሠራበት ለእያንዳንዱ ሰዓት ይከፈለዋል፣ እንዲሁም አንድ የሕዝብ በዓል ከሌላ የሕዝብ በዓል ጋር ቢደረብ ወይም በሕግ በተወሰነ የዕረፍት ቀን ላይ ቢውል በዚህ ቀን የሠራ ሠራተኛ ክፍያ የሚደረግለት በአንዱ የሕዝብ በዓል ብቻ ይሆናል በሚል በዚሁ አዋጅ በአንቀፅ 75 ላይ ተቀምጧል።

ሣምንታዊ የእረፍት ቀን

ማንኛውም ሠራተኛ በ7 ቀናት ጊዜ ውስጥ ያልተቆራረጠ ከ24 ሰዓት የማያንስ የሣምንት ዕረፍት ያገኛል:: የሣምንት ዕረፍት ጊዜ በኅብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ በሌላ አኳኋን ካልተወሰነ በስተቀር በተቻለ መጠን እሁድ ቀን ይውላል። በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው ቢኖርም በስራው ባህሪ ምክንያት ሠራተኛው የሳምንት ዕረፍቱን ለመጠቀም የማይችል እንደሆነ አሠሪው ለሠራተኛው በወር ውስጥ ለ4 ቀናት ዕረፍት እንዲያገኝ ማድረግ አለበት።

የአመት እረፍት ፈቃድ

አንድ ሠራተኛ በሥራ የደከመ አእምሮውን እረፍት በመውሰድ አድሶ በአዲስ መንፈስ በመነቃቃት ወደ ሥራ ገበታው መመለስ እና ሥራውን ማከናወን እንዲችል በአዋጁ በአንቀፅ 76 ላይ ሠራተኞች የአመት እረፍት እንዲወስዱ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል።

አንድ ሠራተኛ የዓመት ፈቃድ ለማግኘት ያለውን መብት በማናቸውም ሁኔታ ለመተው የሚያደርገው ስምምነት በህግ ፊት ተቀባይነት የለውም:: የዓመት ዕረፍት ፈቃድ በገንዘብ አይለወጥም፤

የአመት እረፍት ፈቃድ መጠን

አንድ ሠራተኛ በዚህ አንቀጽ መሠረት ሳይከፋፈል የሚሰጥ የዓመት ፈቃድ ከክፍያ ጋር ያገኛል:: የፈቃዱ ጊዜ በምንም ሁኔታ ከዚህ በታች ከተመለከተው ማነስ የለበትም:: ለመጀመሪያ የአንድ ዓመት አገልግሎት አስራ ስድስት (16) የሥራ ቀናት፤ ለአሠሪው ከአንድ ዓመት በላይ ለተበረከተ አገልግሎት ለእያንዳንዱ ሁለት የአገልግሎት ዓመታት አንድ የሥራ ቀን እየተጨመረ ይሰጣል::

በዓመት ፈቃድ ላይ የሚገኝ ሠራተኛ የሚከፈለው ደመወዝ ሥራ ላይ ቢሆን ኖሮ ሊከፈለው ከሚገባው ጋር እኩል ይሆናል:: ለዓመት ፈቃድ ብቁ የሚያደርገውን የአገልግሎት ጊዜ ለመወሰን ሲባል በድርጅቱ ለ26 ቀናት የሠራ ሠራተኛ ለ 1 ወር እንደሠራ ይቆጠራል::

በዚህ አዋጅ መሠረት የሥራ ውሉ የተቋረጠ ሠራተኛ ያልወሰደው የዓመት ፈቃድ ታስቦ በገንዘብ ይከፈለዋል:: አንድ ሠራተኛ ያገለገለበት ጊዜ ከ1 ዓመት በታች ከሆነ በአገልግሎት ዘመኑ ልክ ተመጣጣኝ የሆነ ዕረፍት በዚያው በአገለገለበት ዓመት ይሰጠዋል በማለት በአዋጅ በአንቀፅ 77 ይደነግጋል።

ለቤተሰብ ጉዳይ የሚሰጥ ፈቃድ

የሰው ልጅ በኑሮው የተለያዩ አጋጣሚዎች ይገጥማቸዋል ይህመ በሚፈጠርበት ጊዜ መደበኛ ስራቸውን ለማከናወን ስለማይችሉ በነፃነት ጉዳያቸውን ፈፅመው እንዲመለሱ በማለት አሰሪና ሰራተኛ አዋጁ በአንቀፅ 81 ላይ ለተለያዩ ጉዳዮች ፈቃድ ሰጥቷቸዋል ከእነሱ መካከልም ሠራተኛው ሕጋዊ ጋብቻ ሲፈጽም ወይም  የትዳር ጓደኛ፣ ወላጅ፣ ተወላጅ፣ ወንድም፣ እህት ወይም አጎት፣ አክስት የሆነ የሥጋ ወይም የጋብቻ ዘመድ ሲሞትበት፤ ከክፍያ ጋር ለ3 የሥራ ቀናት ፈቃድ ይሰጠዋል::

የሠራተኛው የትዳር ጓደኛ ስትወልድ ደመወዝ የሚከፈልበት ሶስት ተከታታይ ቀናት ፈቃድ ከክፍያ ጋር ይሰጠዋል:: ሠራተኛው ልዩና አሳሳቢ ሁኔታ ሲያጋጥመው እስከ 5 ተከታታይ ቀናት ያለክፍያ ፈቃድ የማግኘት መብት አለው:: ሆኖም በዚህ ረገድ የሚሰጠው ፈቃድ በበጀት ዓመቱ ከሁለት ጊዜ ሊበልጥ አይችልም::

ለማኅበር ሥራ የሚሰጥ ፈቃድ የሠራተኞች ማኅበር መሪዎች የሥራ ክርክር ለማቅረብ፣ የኅብረት ስምምነት ለመደራደር፣ በማኅበር ስብሰባ ለመገኘት፣ በሴሚናሮችና በሥልጠና ለመካፈል እንዲችሉ ከክፍያ ጋር ፈቃድ ይሰጣቸዋል:: ፈቃዱም የሚሰጥበት ሁኔታ በኅብረት ስምምነት ሊወሰን ይችላል::

ልዩ ተግባሮችን ለማከናወን ለሠራተኛ የሚሰጥ ፈቃድ

አንድ ሠራተኛ የሥራ ክርክር ለማሰማት ወይም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕጎችን ለማስፈጸም ሥልጣን ባላቸው አካሎች ዘንድ ጉዳዩን ሲያቀርብ ለዚሁ ዓላማ ለጠፋው ጊዜ ብቻ ከክፍያ ጋር ፈቃድ ይሰጠዋል::

አንድ ሠራተኛ የመምረጥ መብቱን ለማስጠበቅ ወይም ከፍርድ ቤትና ከሌሎች ሥልጣን ከተሰጣቸው የፍትህ አካላት ፊት ከምስክርነት ጋር በተያያዘ ላጠፋው ጊዜ ብቻ ከክፍያ ጋር ፈቃድ ይሰጠዋል::

ትምህርት ወይም ሥልጠና ለሚከታተል ሠራተኛ የትምህርት ፈቃድና የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታ፤ የድጋፉ ዓይነትና መጠን በኅብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ ይወሰናል በማለት በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ በአንቀፅ 83 ላይ ተቀምጧል።

የሕመም ፈቃድ

አንድ ሠራተኛ ሥራውን ማከናወን በማይችልበት ሁኔታ ህመም ከገጠመው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ በአንቀፅ 85 እና 86 ላይ በክፍያና ያለክፍ ፍቃድ እንደሚሰጥ አስቀምጧል :: አንድ ሠራተኛ የሙከራ ጊዜውን ከጨረሰ በኋላ በሥራ ላይ በሚደርስ ጉዳት ሳይሆን በሌላ ሕመም ምክንያት ሥራ መሥራት ካልቻለ በዚህ አዋጅ መሠረት የሕመም ፈቃድ ያገኛል::

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተው ፈቃድ ሕመሙ ከደረሰበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ ባለው የ12 ወር ጊዜ ውስጥ በተከታታይ ወይም በተለያዩ ጊዜያት እረፍቱን ቢወስድም በማንኛውም ሁኔታ ከ6 ወር አይበልጥም::

ማንኛውም ሠራተኛ በሕመም ምክንያት ከሥራ ሲቀር አሠሪው ስለሁኔታው ሊያውቅ የሚችል ወይም ሠራተኛው ለማስታወቅ የማይችል ካልሆነ በስተቀር ከሥራ ሲቀር እጅግ ቢዘገይ በማግስቱ ለአሠሪው ማሳወቅ ይኖርበታል::

በኅብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ በሌላ አኳኋን የሚወሰንበት አግባብ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም ሠራተኛ የሕመም ፈቃድ የሚያገኘው በመንግሥት ከታወቀ የሕክምና ድርጅት ተቀባይነት ያለው የሕክምና እረፍት የምስክር ወረቀት ሲያቀርብ ብቻ ነው::

ከላይ የተጠቀሰው የሕመም ፈቃድ ቀጥሎ በተመለከተው ሁኔታ ክፍያ  ይሰጣል:-

ለመጀመሪያው ወር ከሙሉ ደመወዝ ክፍያ ጋር፣ ለሚቀጥሉት 2 ወራት ከደመወዙ 50 በመቶ ክፍያ ጋር፣ ለሚቀጥሉት 3 ወራት ያለክፍያ ይሰጣል።

የወሊድ ፈቃድ

አንድ ሴት ሠራተኛ ነፍሰጡር በሆነች ጊዜ እና በወለደችም ጊዜ ፈቃዶች ይሰጧታል ይህም በአዋጁ በአንቀፅ 88 እና ተከታዮቹ ተቀምጧል።

ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ ከእርግዝናዋ ጋር የተያያዘ ምርመራ ለማድረግ አሠሪው ከደመወዝ ጋር ፈቃድ ይሰጣታል፤ ሆኖም ሠራተኛዋ ከምርመራ በኋላ የሐኪም ማስረጃ ማቅረብ አለባት::

ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ ከመውለዷ በፊት ሐኪም እንድታርፍ ካዘዘ አሠሪው ከክፍያ ጋር እረፍት ይሰጣታል::

ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችበት ቀን በፊት የ30 ተከታታይ ቀናት የቅድመ-ወሊድ ፈቃድ፣ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ ለ90 ተከታታይ ቀናት የድህረወሊድ ፈቃድ ከክፍያ ጋር ይሰጣታል::

ሠራተኛዋ ከመውለዷ በፊት የወሰደችው የ30 የሥራ ቀናት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ሲያልቅ ካልወለደች እስከምትወልድበት ቀን ድረስ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) መሠረት እረፍት ልታገኝ ትችላለች:: የ30 የሥራ ቀናት የቅድመ-ወሊድ ፈቃዷ ሳያልቅ ከወለደች 90 የሥራ ቀናት የድህረ-ወሊድ ፈቃዷ ይጀምራል::

ማንኛዋም ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ ፅንስ ማቋረጧ በሃኪም ማስረጃ ሲረጋገጥ በሚሰጣት የህክምና ፈቃድ ላይ  የደሞዝ  ቅነሳ  አይደረግም::

የሴት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ

ሴቶች በፆታቸው ምክንያት በማንኛውም ሁኔታ ልዩነት አይደረግባቸውም::

ሴት ሠራተኛ በቅጥር፣ በደረጃ ዕድገት ወይም በሌላ ማናቸውም የጥቅማ ጥቅም ውድድር ከወንድ ጋር እኩል የሆነች እንደሆነች ቅድሚያ ይሰጣታል።

ለሴቶች ከባድ ወይም ለጤናቸው ጎጂ ናቸው ተብለው ሚኒስቴሩ በሚዘረዝራቸው ሥራዎች ላይ ሴቶችን ማሠራት የተከለከለ ነው::

ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛን ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ እንዲሁም የትርፍ ሰዓት ማሰራት የተከለከለ ነው::

ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ የምትሠራው ሥራ ለራሷም ሆነ ለጽንሱ ጤንነት አደገኛ መሆኑ በሐኪም ሲረጋገጥ ወደ ሌላ የሥራ ቦታ መድቦ ማሰራት አለበት:: ማንኛውም አሠሪ ሠራተኛዋ ነፍሰጡር በሆነችበት ጊዜና ከወለደችበት ቀን ጀምሮ በ4 ወር ጊዜ ውስጥ ከሥራ ሊያሰናብት አይችልም በማለት በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ በአንቀፅ 87 ላይ ተደንግጓል።

ልዩ ልዩ መብቶች

የሥራ ውል በሚቋረጥበት ወይም ሠራተኛው በሚጠይቅበት ማናቸውም ጊዜ ሠራተኛው ሲሰራ የነበረውን የሥራ ዓይነት፣ የአገልግሎት ዘመኑንና ሲከፈለው የነበረውን ደመወዝ የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ለሠራተኛው ያለክፍያ መስጠት አለበት:: ለሠራተኞች ምቹ የሥራ ቦታ የማግኘት፣ ለሠሩበት ክፍያ የማግኘት ፣ በሥራ ላይ ወይም በሥራ ቦታ ስለሚደርስ ጉዳት በሥራ ላይ ጉዳት ማለት በአዋጁ በአንቀፅ 97 እንደተቀሰው ማንኛውም ሠራተኛ ሥራውን በማከናወን ላይ ሳለ ወይም ከሥራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ከራሱ ውጭ በሆነ ምክንያት ወይም ሥራውን ለማከናወን ባደረገው ጥረት ምክንያት በአካሉ ወይም በአካሉ ማንኛውም ክፍል ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ ላይ በድንገት የደረሰበት ጉዳት ሲሆን የሚከተሉትን ይጨምራል:: ሠራተኛው ከሥራ ቦታው ወይም ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጭም ቢሆን የአሠሪውን ትዕዛዝ ሥራ ላይ ያውል በነበረበት ጊዜ የደረሰበት ጉዳት ፣ ሠራተኛው ከሥራው ጋር በተያያዘ ግዴታ የተነሳ ከሥራው በፊት ወይም በኋላ ወይም ሥራው ለጊዜው ተቋርጦ በነበረበት ጊዜ በሥራው ቦታ ወይም በድርጅቱ ግቢ ውስጥ እያለ የደረሰበት ማንኛውም ጉዳት፣ ሠራተኛው ወደ ሥራ ቦታው ወይም ከሥራ ቦታው ወደ ድርጅቱ ለሠራተኞች አገልግሎት እንዲሰጥ በመደበው የመጓጓዣ አገልግሎት ወይም ድርጅቱ ለዚሁ ተግባር በተከራየውና በግልፅ በመደበው የመጓጓዣ አገልግሎት በመጓዝ ላይ በነበረበት ጊዜ የደረሰበት ማንኛውም ጉዳት፣  ሠራተኛው ሥራውን በማከናወን ላይ ባለበት ጊዜ በአሠሪው ወይም በሦስተኛ ወገን ድርጊት ምክንያት የደረሰበት ጉዳት ናቸው::

የሕግ ባሙያዋ እንደሚሉት ሠራተኛው በሥራ ላይ እያለ ጉዳት ቢደርስበት  አሠሪው የሚከተሉትን  ግዴታዎች ለተጎጂው መፈፀም አለበት::

የመጀመሪያው ጉዳት ለደረሰበት ሠራተኛ የመጀመሪያ ሕክምና ዕርዳታ በጊዜው የመስጠት፣ ጉዳት የደረሰበትን ሠራተኛ ተስማሚ በሆነ የመጓጓዣ ዘዴ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የሕክምና ጣቢያ የማድረስ፣ በሥራ ላይ የሚመጣ ጉዳት መድረሱን አግባብ ላለው አካል የማስታወቅ ፤ እንዲሁም ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ ሞቶ ከሆነ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወጭ መክፈል የአሠሪው ግዴታ ይሆናል። በተጨማሪም የጠቅላላና የልዩ ሕክምና እንዲሁም የቀዶ ሕክምና ወጪዎች፣ የሆስፒታልና የመድሃኒት ወጪዎች፣ የማንኛውም አስፈላጊ ሰው ሰራሽ ምትክ ወይም ተጨማሪ አካሎችና የአጥንት ጥገና ወጪዎች  አሠሪው ይከፍላል ። ህክምናውም የሚቋረጠው የሕክምና ቦርድ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ይሆናል:: የክፍያው ሁኔታም እንደ ጉዳቱ መጠን እየታየ በየጊዜው የሚከፈል ፣ ለየጉዳት ጡረታ ወይም ዳረጎት ወይም ካሣ ክፍያ ፣ የሞተ እንደሆነ ለቤተሰብ የጡረታ አበል ወይም ዳረጎት ወይም ካሣ የማግኘት መብት ይኖረዋል:: በሚል   በአዋጁ በአንቀፅ 108 ፣ 109 እና 110 በዝርዝር አስቀምጦታል።

በመጨረሻም ይላሉ ወ/ሮ ፍቅር  የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ለሠራተኞቹ የተለያዩ መብቶችን ሰጥቷል። ይህም የሆነበት ምክንያት አሠሪው ሠራተኞቹን አላግባብ የሥራ ጫና እንዳያደርስባቸው የሥራ ሰአት መደንገጉ ፣ ሠራተኞች አእምሮአቸውን እንዲያድሱ የአመት እረፍት ማመቻቸቱ ፣ በሥራ ቦታ ምቹ እንዲሆን መደንገጉ ፣ ህገ ወጥ የሥራ ስንብትና የሠራተኛ ቅነሳ እንዳይኖር አሠራሮችን መዘርጋቱ ፣ ለሠራተኞች ልዩ ልዩ ፈቃዶችን ማመቻቸቱ እና ሠራተኛው በሥራ ላይ እያለ ጉዳት ቢደርስበት አሠሪው ሀላፊነት እንደሚወስድ ሽፋን የሚሰጥ በመሆኑ ለሠራተኞች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርና በሙሉ አቅምና ተነሳሽነት ሥራቸውን እየሠሩ መብታቸውን እንዲያስከብሩ የሕግ ተጠያቂነት ጭምር አካቶ የያዘ አዋጅ ነው ። ብለዋል።

የህግ አንቀጽ

የሥራ ስንብት ክፍያ እና ካሳ የሚከፈልባቸው ሁኔታች በአሠሪና ሠራተኛ ሕግ
• የሥራ ውል የሚቋረጠው በአሠሪው ወይም በሠራተኛው አነሳሽነት ወይም በሕግ በተደነገገው መሰረት ወይም በኅብረት ስምምነት ወይም በተዋዋይ ወገኖች በሚደረግ ስምምነት እንደሚሆን በአዋጁ አንቀፅ 23 ንኡስ ቁጥር 1 ስር ተደንግጎ ይገኛል።
• የሥራ ውል ሲቋረጥ ያለማስጠንቀቂ አንቀፅ 27 እና በማስጠንቀቂያ አንቀጽ 28 ሊሆን እንደሚችል ከአዋጁ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል።
• በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 39 ስር የሥራ ስንብት ክፍያ የሚከፈልባቸው ሁኔታዎች ተዘርዝረው ይገኛሉ።
• ድርጅቱ በመክሰሩ ወይም በሌላ ምክንያት ለዘለቄታው በመዘጋቱ የሥራ ውሉ ሲቋረጥ በአዋጁ አንቀፅ 24 ንኡስ ቁጥር 4 ተመልክቷል ፡፡
• በሕግ ከተደነገገው ምክንያት ውጪ በአሠሪው አነሳሽነት የሥራ ውሉ ሲቋረጥ የሥራ ውል በአሠሪ አነሳሽነት ሊቋረጥ የሚችልባቸው ሕጋዊ አግባቦች በአዋጁ አንቀፅ 26 ተመልክተዋል፡፡
ምንጭ – ፍትሕ ሚኒስትር

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ 12  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here